Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበመልካ ዋካና የተገኘው ከአንድ ሚሊዮን ዓመት በላይ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል

በመልካ ዋካና የተገኘው ከአንድ ሚሊዮን ዓመት በላይ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ቅሪተ አካል

ቀን:

በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና 1.5 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ዝርያ ቅሪተ አካል፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ በሚገኘው የመልካ ዋከና መካነ ቅርስ መገኘቱን የቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 በመልካ ዋከና ከባህር ጠለል በላይ 2,300 ሜትሮች (7,546 ጫማ) ከፍታ የተገኘው ቅሪተ አካሉ፣ የቀኝ መንጋጋ አጥንት መሆኑን ጥናቱ በታተመበት ኮሙዩኒኬሽን ባዮሎጂ ላይ ተመልክቷል፡፡

አዲሱ ግኝት የዚህን ዝርያ የመጀመርያና ብቸኛውን የፕሌይስቶሴኔ (Late Pleistocene Period) ቅሪተ አካልን የሚያመለክት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የቀይ ቀበሮ ዝርያ በኢትዮጵያ የተገኘበት ጊዜ ከሃያ ሺሕ እስከ መቶ ሺሕ ዓመት ባለው ውስጥ ነው የሚለውን መላምት ይቀይራል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የቅርስ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው፣ የተገኘው ቅሪተ አካል የታችኛው መንጋጋ የቀኝ ክፋይ ሲሆን፣ የተገኘውም በ2009 ዓ.ም. በመካነ ቅርሱ በተደረገው የአርኪዮሎጂ አሰሳ የጥናት ቡድኑ መሪ በሆኑት በተገኑ ጎሳ (ዶ/ር) ነው፡፡ ግኝቱም ረዘም ላለ ጊዜ የተለያዩ የላብራቶሪ ጥናቶች ሲደረግበት ቆይቶ በኔቸር ኮሙዩኒኬሽንስ ባዮሎጂ በተባለው ዓለም አቀፍ መጽሔት ሜይ 16 ቀን 2023 ታትሟል፡፡

ዝርያዎቹ መቼና እንዴት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ሠፍረው መኖር እንደጀመሩ ሳይታወቅ የቆየ ቢሆንም፣ ቀይ ቀበሮን ጨምሮ በዓለም የሚገኙ በቀበሮ ዝርያዎች ላይ የተደረገው የዘረመል (ጄኔቲክ) ጥናት እንዳመለከተው፣ የቀይ ቀበሮ ዝርያ ወደ ኢትዮጵያ የገባበትን ጊዜ ከአንድ መቶ ሺሕ ዓመት የማይበልጥ ነው የሚል ድምዳሜ አስቀምጦ ቆይቷል፡፡

 በዓለም የዚህ ዝርያ ቅሪት አካል ሳይገኝ የቆየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ድምዳሜው እስካሁን ተቀባይነት አግኝቶ ቢቆይም፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ በሚገኘው የመልካ ዋከና መካነ ቅርስ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት የተውጣጣው መሥራት የጀመረው የተመራማሪዎች ቡድን፣ ይህንን ድምዳሜ በመሠረታዊነቱ የሚቀይርና በዓይነቱ በዓለም የመጀመርያ የሆነ 1.5 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ የቀይ ቀበሮ ዝርያ ቅሪተ አካል ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የባለሥልጣኑ መግለጫ እንደሚያብራራው፣ ይህ ግኝት ስለዝርያው አመጣጥና ልዩ ባህሪያት ጥናት ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ በተጓዳኝ አሁን በአገሪቱ በሚገኙ የቀበሮዎች ህልውና ላይ ከተጋረጠው አደጋ አንፃር ከፍተኛ ትርጉም ያለው መሆኑን ተመራማሪዎች አሳውቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የዚህ የዱር እንስሳ ዝርያ ልዩ ባህሪያትና ልዩ የመኖሪያ ከባቢውን መሠረት ያደረጉ ሥነ ምህዳራዊ ሞዴሎችን (ኢኮክሊማቲክ ሞዴልስ) በመጠቀም እስካሁን በቆየበት ረዥም ዕድሜ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶችንና በመጪው ጊዜያት የሚያጋጥሙትን ተጠባቂ ፈተናዎችን ለመተንተን የሚያስችል ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ብርቅዬ የስሜን ቀይ ቀበሮ (Canis Simensis) ዝርያ፣ በተወሰኑ ደጋማና ከፍተኛ ተራራማ አካባቢዎች ብቻ የሚኖር ብርቅዬ የዱር እንስሳ ሲሆን፣ ከሌሎች የቀበሮ ዝርያዎች ጋር ሲነፃፀር መካከለኛ ተክለ ሰውነት ያለውና በአማካይ ከ12 እስከ 18 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነው፡፡

 እንደ ባለሥልጣኑ መግለጫ፣ ቀይ ቀበሮ በአሁኑ ወቅት ከስድስት የማይበልጡ ሥፍራዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ብዛቱ 500 እና ከዚያ በታች የሆኑ ዝርያዎች ውስጥ የመራባት ዕድሜ ላይ የደረሱ ቀበሮዎች ብዛት ከ200 አይበልጡም፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ብርቅዬ የዱር እንስሳ ዝርያዎች የሚኖሩባቸው ሥፍራዎች በጣም ውስን የሆኑና የተመናመኑ በመሆናቸው ከፍተኛ የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው የዱር እንስሳ ዝርያዎች መካከል ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡

ጥናቱ፣ በመጪዎቹ ምዕት ዓመታት ይህንን ብርቅዬ የዱር እንስሳ ሊገጥሙት የሚችሉ ፈተናዎችን በተመለከተም ከሰው ሠራሽ ተግዳሮት በተጨማሪ ከዓለም ሙቀት መጨመር ጋር የተያያዘው ምቹ መኖሪያ ሥፍራ መመናመን፣ ከዚህ በፊት ያልታዩና ከፍተኛ አደጋን የሚያስከትሉ ምክንያቶች መሆናቸውን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘም በእነዚሁ ዓመታት ለቀይ ቀበሮ መኖሪያነት ምቹ ሥፍራዎች በአማካይ እስከ 80 በመቶው የሚደርሰው ሊጠፋ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በመኖሪያ ሥፍራዎች ውስጥ እየተስፋፋ ከመጣው የሰዎች ሠፈራ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን ለመቀነስና ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባም ተመራማሪዎች አስገንዝበዋል፡፡

የጥናት ቡድኑ ይህን ድንቅ የአፍሪካ ዝርያ ለመጠበቅ ሊሠሩ የሚችሉ የጥበቃ መፍትሔዎችን ማፈላለግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥቶበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...