Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ብክነትን ለመቀነስና አላስፈላጊ ወጪን ለማስቀረት ለወሰን ማስከበርና ለካሳ ክፍያ ችግሮች ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ያስፈልጋል›› አቶ ደረጀ አየለ፣ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ወሰን ማኔጅመንት ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ውስጥ መፈታት ያልቻለ ችግር ሆኖ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው፣ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ አተገባበር ነው፡፡ የመንገድ መሠረተ ልማት ሲስፋፋ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱም ይጠቀሳል፡፡ ወሰን ለማስከበር ያለው ፈተና እጅግ ውስብስብ ከመሆኑም በላይ፣ የካሳ ክፍያ ግመታውም በችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ ከመንገድ ፕሮጀክቶቹ ወጪ በላይ የካሳ ጥያቄ የሚቀርብባቸው አጋጣሚዎች እየተከሰቱ መምጣታቸው በራሱ የችግሩን ጥልቀት አመላካች ሆኗል፡፡ ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በየዓመቱ የሚቀርቡ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች በአሥር ቢሊዮኖች ብር የሚቆጠሩ መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ መንገድ ይገነባል በተባለበት መስመር የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች ሳይቀሩ ሕገወጥ ግንባታ በማካሄድ ካሳ ይክፈለን ጥያቄ በማቅረብ የሚፈጸሙት ድርጊቶች ለመንገድ መሠረተ ልማት እንቅፋት መሆኑ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ያልተገባ የካሳ ክፍያ ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ደግሞ ጠንከር ያለ አሠራርና ሥርዓት አለመዘርጋቱም ሌላው ችግር ሆኖ ይቀርባል፡፡ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ባሉበት የወሰን ማስከበር ሥራ፣ በካሳ ክፍያዎችና በተግዳሮቶች ላይ ዳዊት ታዬ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ወሰን ማኔጅመንት ዳይሬክተር ከአቶ ደረጀ አየለ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ከሚነሱ በርካታ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ከወሰን ማስከበርና ከካሳ ክፍያ ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ ችግሩ ለዓመታት የቆየ ስለሆነና ሁነኛ መፍትሔ ባለማግኘቱ ያጋጠመው ችግር ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- የመንገድ ግንባታዎች በፍጥነት እንዳይፈጸሙ የሚያደርጉ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ የተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የፋይናንስ ችግርና የመሳሰሉ ችግሮች ይታያሉ፡፡ እኛ ባካሄድነው ጥናትና በተግባርም ካየነው ነገር፣ የመንገድ ፕሮጀክቶቻችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዳይፈጸሙ እንደ ዋና ተግዳሮት ከለየናቸውና ተቋሙን እየፈተኑ ካሉ ጉዳቶች አንዱ፣ ከመንገድ ወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮቹ በርካታና ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ክልሉን ከተለያዩ ንብረቶች ነፃ አድርጎ ለሥራ ተቋራጮች የማስረከብ የውል ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነትን ለመወጣት ግን በእጅጉ የሚቸገርባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው፡፡ አስተዳደሩ የመንገድ ሥራውን ለማከናወን መሬት ይጠይቃል፡፡ መሬት በሁለት መንገድ ይጠየቃል፡፡ አንዱ መንገድ የሚገነባበት ቋሚ ቦታ ነው፡፡ መሬቱ የመንገዱ አካል ስለሚሆን በቋሚነት የሚፈለግ መሬት አለ፡፡ በጊዜያዊነት የምንፈልገውም መሬት አለ፡፡ በጊዜያዊነት የምንፈልገው መሬት ለስቶር፣ ለካምፕ፣ ለምርጥ አፈር ማውጫ፣ ለኳሪና ለመሳሰሉት ነው፡፡ ይህንን በጊዜያዊነት የምንረከበውን ቦታ ደግሞ አስተካክለን የምንመልሰው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቋሚነትና በጊዜያዊነት የምትወስዱትን መሬት ካሳ ከፍላችሁ የምትረከቡት እንዴት ነው? ይህንን በምታደርጉበት ጊዜ የሚያጋጥሟችሁ ችግሮች ምንድናቸው?

አቶ ደረጀ፡- አዎ፣ ካሳ ከፍለን የምንረከባቸው ሲሆን፣ የመንገድ ክፍሉን ከንብረት ነፃ አድርገን ለሥራ ተቋራጩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህ አኳያ በመንገድ ክፍሉ ያሉትን ንብረቶች እንዲህ በቀላሉ ለማንሳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህንን ለመፈጸም በጣም ብዙ ችግር ነው ያለው፡፡ መሬቱ ከከተማ ውጪ ገጠር አካባቢ ከሆነ፣ የሥራ ተቋራጩ ንብረት እንዲነሳለት በጠየቀ በ90 ቀናት ወይም በሦስት ወራት ውስጥ ንብረቱን አንስተን ለሥራ ተቋራጩ የመስጠት ግዴታ አለብን፡፡ በከተማ አካባቢ ከሆነ ደግሞ በ120 ቀናት ተገምቶ ካሳ ተከፍሎና ንብረት ተነስቶ ከንብረት ነፃ የሆነ ቦታ ለሥራ ተቋራጩ ማስረከብ ግዴታችን ነው፡፡ በኮንትራት ውላችንም ይህ እንደ ግዴታ ተቀምጧል፡፡

ሪፖርተር፡- ንብረቱን ለማንሳት በከተማና በገጠር ያለው የጊዜ ልዩነት ለምን ተፈጠረ?

አቶ ደረጀ፡- በከተማ ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ የተሰጠው የአገልግሎት መስመሮች፣ ቤቶችና የመሳሰሉት ግንባታዎች ስላሉና ሥራውም ሰፋ ስለሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሠራራችሁ እንዲህ ቢሆንም በርካታ መንገዶች ግንባታቸው ሳይጀመር የሚቀሩት ወይም የሚጓተቱት፣ እናንተ በገባችሁት ውል መሠረት በ90 እና በ120 ቀናት ቦታውን ከንብረት ነፃ አድርጋችሁ ለኮንትራክተሩ እያስረከባችሁ ባለመሆኑ፣ እንዲያውም በአንዳንድ ቦታዎች ወሰን ማስከበሩ ተፈጻሚ ሳይሆን ዓመታት ይፈጃል ይባላል፡፡ ይህ ደግሞ የመንገድ ዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ በመቀጠሉ፣ ለከፍተኛ ብክነትና ምዝበራም ምንጭ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ የእናንተ አስተያየት ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- ይህንን ለማስፈጸም ዓመታት ይፈጃል፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ወሰን ለማስከበር ሦስትና አራት ዓመታት ይስፈልጋሉ፡፡ የወሰን ማስከበር ሥራው ረዥም ጊዜ ወሰደ ማለት ደግሞ ሥራ ተቋራጩ ሥራውን በወቅቱ እንዳያከናውን ተደረገ ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሥራ ተቋራጩ ለእያንዳንዱ ሥራ ያዘጋጀው ማሽን ለሚቆምበትና ያለ ሥራ ለቆየበት ጊዜ የኪሳራ ማካካሻ ክፍያ ይጠይቀናል፡፡ እሱን የመክፈል ግዴታ ይኖርብናል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ገንብቶ ለማስረከብ የጊዜ ይራዘምልን ጥያቄ ይቀርባል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ በሦስት ዓመታት ያልቃል የተባለው ፕሮጀክት አራትና አምስት ዓመታት ይዘገያል፡፡ ከዚህም በላይ ጊዜ ሊፈጅ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እኛ ዘንድ አሁን በርካታ ሽማግሌ ፕሮጀክቶች ያጋጥሙናል፡፡ ከአብዛኞቹ ሽማግሌ ፕሮጀክቶች አንዳንዶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ሊዘገዩ ቢችሉም፣ ከካሳ ክፍያ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ረዥም ጊዜ የቆዩም አሉ፡፡ ስለዚህ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ጉዳዮች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ትልቅ እንቅፋት ሆነዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የችግሩ ምንጭ ምንድነው? ለምንድነው ይህንን ያህል ፈታኝ ሆኖ ሊቆይ የቻለው?

አቶ ደረጀ፡- ችግሮቹ ምንድናቸው ብለን ዘርዘር አድርገን ስናይ፣ አንደኛ እኛ መንገድ እንሠራለን ብለን ስንጀምር የመንገዱ ፕሮጀክት በይፋ ይነገራል፡፡ ይህ መረጃ የደረሳቸው አንዳንድ ወገኖች የመንገድ ክልል ውስጥ ገብተው ግንባታ ማካሄድ ይጀምራሉ፡፡ እኛ ካሳ መክፈል የሚገባን የመንገድ ዲዛይኑ ተሠርቶ ኮንትራቱ ከተሰጠበት ጊዜ በፊት የነበሩ ንብረቶችን ለማስነሳት ነው፡፡ ነገር ግን ዲዛይኑ በተሠራበት ወቅት ያልነበሩ ግንባታዎች መንገድ ክልል ውስጥ ገብተው እናገኛቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፕላኑ ከወጣ በኋላ የተገነቡ መሆናቸውን የምታውቁበት መንገድ አለ?

አቶ ደረጀ፡- መረጃ አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዲዛይኑ ከተሠራ በኋላ መንገዱ በሚያልፍበት ቦታ ያልነበሩ ግንባታዎች ናቸው ማለት የምትችሉበት መረጃ አለን እያሉ ነው?

አቶ ደረጀ፡- አዎ፣ ዲዛይኑ በሚሠራበት ጊዜ መረጃ ይለቀማል፡፡ መረጃ ከመጀመርያው ጀምሮ ይያዛል፡፡ በመንገድ ክልል የገቡ ንብረቶች በሙሉ ተለይተው ይሰናዳሉ፣ በዝርዝር ይቀርባሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከእነዚህ ዝርዝር ውጪ ግንባታ ማካሄድ ይጀመራል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ መንገዱን እንደሰጠን የሞብላይዜሽን ጊዜ አለ፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ ግንባታ ለመጀመር እንዳንችል እንቅፋት ይሆንብናል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደጠቀሱት አንድ የመንገድ ፕሮጀክት የሚያልፍበት ቦታ እንደታወቀ የካሳ ክፍያ ለማግኘት ሲባል በወረዳና በከተማ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ጭምር እጃቸውን ያስገባሉ፡፡ ይህ በግልጽ ከታወቀ እንዲህ ያሉ ያልተገቡ ድርጊቶችን እንዴት ትከላከላላችሁ?

አቶ ደረጀ፡- የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች ይገቡበታል፡፡ እንዲህ ያለውን ሕገወጥ ድርጊት የመከላከል ኃላፊነት ግን የእነሱ ነበር፡፡ በድርጊቱ ውስጥ አሉበት ብለን ደፍረን የምንናገረው ሕገወጥ ግንባታ ሲፈጸም መከላከል ባለመቻላቸው ነው፡፡ ምክንያቱም የወረዳና የከተማ አስተዳደር በዚያ መስመር ላይ ሕገወጥ ግንባታ መካሄድ የለበትም፡፡ አንድ ጊዜ ንብረት ከተለየና ለኮንትራክተር ከተሰጠ በኋላም ምንም ዓይነት ንብረት መሥፈር የለበትም፣ ይህንን ያውቃሉ፣ ሕጉንም ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የመከላከል ሥራ አይሠሩም፡፡ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን በአካል ሄዳችሁ ብታዩ አዳዲስ ግንባታዎች ለመሆናቸው በግልጽ ማወቅ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ የሚደረገው ያልተገባ የካሳ ክፍያ ለማግኘት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በሕገወጥ መንገድ በክልሉ ውስጥ የተገነቡ በመጨረሻ የካሳ ክፍያ የሚጠየቅባቸው ናቸው ማለት ነው? ይህንን ካወቃችሁ እናንተ እንዴት ነው የምታስተናግዷቸው? ትከፍሏቸዋላችሁ?

አቶ ደረጀ፡- የንብረት ማስነሻ ካሳ ክፈሉን የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ እኛ ግን በፍፁም አናደርግም፡፡ መሥሪያ ቤታችን ጠንካራ ነው፡፡ እኛ እንዲህ ላለው ሕገወጥ ግንባታ አንከፍልም እንላለን፡፡ እነሱ ደግሞ ክፈሉን ይላሉ፡፡ በዚህ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ሥራ ይቆማል ማለት ነው፡፡ አሁን ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ መንግሥት ተጠቃሚ አይደለም፡፡ አሁንም ክፈሉን፣ አንከፍልም በሚለው ክርክር ጊዜ ይባክናል፡፡ በዚህም ምክንያት ንብረቱ ባለመነሳቱና ሥራ በመቆሙ ኮንትራክተሩ ሥራ አይሠራም፡፡ ኮንትራክተሩ ሥራ ካልሠራ ፕሮጀክቱ በጊዜ አይጠናቀቅም፡፡ በጊዜ አለመጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ወጪና ተጨማሪ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም ኮንትራክተሩ ሥራ መጀመር በሚገባው ጊዜ ባለመጀመሩ ካሳ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሁለት መንገዶች ይከስራል፡፡ አንደኛው ግንባታው በተጓተተ ቁጥር የግንባታው ወጪ ይጨምርብናል፡፡ ሁለተኛ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ኅብረተሰቡ ከልማቱ ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ የበጀት ጫና ያመጣል፡፡ ተጨማሪ በጀት በየዓመቱ እየተንከባለለ በተቋሙና በመንግሥት ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ በወሰን ማስከበር ላይ ያለው አንዱ ችግር ከሕገወጥ ግንባታዎች ጋር የተያዘ ነው፡፡ ከሕገወጥ ግንባታዎች ባሻገር የካሳ ክፍያ ለማግኘት ሲባል የተጋነነ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታ በብዛት ይታያል፡፡ ዋጋ ለማናር ነው ጥረት የሚያደርጉት፡፡ ንብረቶቹ ከሚያወጡት ዋጋ በላይ ከፍ አድርጎ ለመገመት ይሞከራል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት በሁለት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛው በግብርና አካባቢዎች የሚያጋጥመን ነው፡፡ በተለያዩ የምርት ዓይነቶች አንድ ማሳ የሚሰጠው የምርት መጠን ይታወቃል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ አለ፡፡ በደንብ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ማሳው ከሚሰጠው ምርት በላይ ከፍ አድርገው ዋጋውን ገምተው ያቀርባሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ጉዳይ በምሳሌ ቢያስረዱን?

አቶ ደረጀ፡- እንደ ምሳሌ የምናቀርባቸው የተለያዩ ገጠመኞች አሉን፡፡ ለምሳሌ የስንዴ ምርትን እንውሰድ፡፡ በምርጥ ዘር ከተመረተ ስንዴ ከ30 እስከ 35 በሔክታር ይገኛል ተብሎ ነው እየተሠራበት ያለው፡፡ ይህ ከፍተኛው የምርት መጠን ነው፡፡ የስንዴ ማሳው ለመንገድ ሥራ የተወሰደበት አካል ግን ከማሳው የሚያገኘው በሔክታር 90 ኩንታል ነው ተብሎ ተጽፎ ያመጣል፡፡ ይታይህ እንግዲህ በትክክል ከአንድ ማሳ ላይ ይገኛል ከተባለው ሦስት እጥፍ ማለት ነው፡፡ ምርጥ ዘር ተደርጎ እንኳን በሔክታር 35 ኩንታል አይገኝም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥመን እኛ ግብርና ቢሮዎችንና የሚመለከታቸውን ሁሉ እናነጋግራለን፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ተጋንኖ የመጣውን ጥያቄ አንቀበልም፡፡ በዚህ ምክንያት በጭቅጭት ጊዜ ይባክናል፡፡ ሌላው ንብረቱን ከፍ አድርጎ መገመት ነው፡፡ ሰሞኑን አንድ ጉዳይ እያየን ነበር፡፡ የአንድ በመንገድ ፕሮጀክት ላለ ተረፈ ምርት የተጠየቀ ካሳ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ለተረፈ ምርቱ (ጭድ፣ ገለባ) በሔክታር 76 ብር ብለውን ነበር፡፡ አሁን ሲያመጡ ግን 560 ብር ነው ብለው አቀረቡ፡፡ ይህ ማለት 714 በመቶ ጭማሪ ይዘው መጡ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር አንቀበልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አለመቀበሉም ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም ካሳ ከፍለን ንብረቱ መነሳት አለበት፡፡ ስለዚህ ችግሩ በጣም ውስብስብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካሳውን ለመክፈልም ሆነ ላለመክፈል ችግር ካለ እንደ መፍትሔ እየወሰዳችሁት ያለው ነገር ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- በዚህ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ስታንዳርድ የለንም፡፡ እኛ እንደ ተቋም ነጠላ ዋጋ በማፅደቅ ካሳ የመሥራት መብት የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የመሥራት ኃላፊነት የተሰጠው ማነው ታዲያ?

አቶ ደረጀ፡- ይኼ ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ለከተማና ለወረዳ አስተዳደሮች ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ከፋዮችና የምናወጣውም ገንዘብ የመንግሥት ስለሆነ ዓይናችን እያየ አንከፍልም እያልን ነው፡፡ ዓይናችን እያየ ያልተገባ ግመታ ለተሰጠው ንብረት ለመፈረም እጃችን እሺ አይልም፡፡ እኛ ግምቱ ሲመጣ የመክፈል ግዴታ ያለብን ቢሆንም፣ በግልጽ የሚታይ የተጋነነ ዋጋ ላለመክፈል የቻልነውን ያህል እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ግምቱ ሲመጣ የተጋነነ ከሆነና አንከፍልም ካላችሁ የመንገድ ፕሮጀክቱ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? በመጨረሻ እንደ አማራጭ የምትወስዱት ዕርምጃ ምንድነው? በዋጋ ግመታው ላይ ያለውስ ችግር ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- ለዚሁ ነው ትክክል አይደለም ብለን ስናምን አንከፍልም የምንለው፡፡ እዚያ ላይ ብዙ ጊዜ ይባክናል፡፡ የካሳ ግመታውን ሕጉ የሚሰጠው ለከተማና ለወረዳ አስተዳደሮች ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ችግር ያለው ከምርታማነትና ነጠላ ዋጋን ከፍ አድርጎ ያላግባብ ለመጠቀም ከመሞከር ነው፡፡ ሌላው ደረጃ ማሻሻል ነው፡፡ ለምሳሌ በከተማ አካባቢዎች ቤቶች ደረጃ አላቸው፡፡ አንደኛ ደረጃ የጭቃ ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ የጭቃ ቤት፣ በአሸዋ የተገረፈ እየተባለ ደረጃ አላቸው፡፡ የብሎኬት ቤቶችም ደረጃ ስላላቸው እንደ ደረጃቸው ይስተናገዳሉ፡፡ ሕንፃም ከሆነ እንዲሁ ነው፡፡ በዚህ አካባቢም ያለው ችግር ቤቱ ሊሰጠው ከሚችው ደረጃ በላይ ከፍ አድርገው ይሰጡታል፡፡ ይህ ያላግባብ ጥቅም ለማግኘት  ሲባል የሚደረግ ነው፡፡ እኛ በምንመድባቸው ሠራተኞች በኩል መረጃ አሰባስበን ያላግባብ ነው ብለን ስናምን እንከራከራለን፡፡ የነጠላ ዋጋ ስታንዳርድ ስለሌለ ግን ብዙ ጊዜ ችግር ያጋጥመናል፡፡ ለዚህ ሁሉ መፍትሔ የሚሆነው ግን እንደ አገር የነጠላ ዋጋ ስታንዳርድ በማውጣት መተግበር ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የመሠረተ ልማት ሚኒስቴር አንዳንድ ነገሮችን እየሠራ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ለብዙ ዓመታት ይዞት የቆየ ነው፡፡ እንደ አገር መፍትሔ ሊሆን የሚችለው አገር አቀፍ የወቅቱን ገበያ እያየ ሊካካስ የሚችል የነጠላ ዋጋ ስታንዳርድ ማዘጋጀት ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ባወቅነው ነው የምንከፍለው፡፡ ሾልኮ የሚወጣ ነገር የለም ማለት ግን አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ መንግሥትንም ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣና ውስብስብ ችግሮች የሚታዩበት ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ፣ የንብረት ግምትን ታች ላሉ ለወረዳና ለከተማ አስተዳደሮች መሰጠቱ አግባብ ነው ተብሎ ይታመናል? እንደምንሰማውና እርስዎም እንደጠቀሱልኝ ያልተገባ ግምት የሚሰጡት እነሱ ከሆኑ ለምን ሌላ መፍትሔ እንዲቀመጥ አልተደረገም? የንብረት ግመታን ለማስፈጸም የወጡ ሕግጋትስ ምን ይላሉ?

አቶ ደረጀ፡- አዋጁ ያስቀመጠው በሦስት ደረጃ ነው፡፡ የካሳ ግምት እንዲሰጥ የተቀመጡት ሦስት ጉዳዮች ናቸው፡፡ የንብረቱ ግመታው የሚካሄደው አስተዳደሮች አንደኛ በወረዳና በከተማ በሚቋቋሙ ኮሚቴዎች፣ ሁለተኛ በተቋማት የካሳ ግምት ሊሰጡ በሚችሉ ተቋማት እንዲገመት የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው በተወሰነላቸው ገለልተኛ ባለሙያዎች የካሳ ግምት እንዲሠራ በሚል አዋጁ ደንግጓል፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ አማራጮች በአዋጁ ከተቀመጡ የግምት ሥራው በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች ብቻ የሚከናወነው ለምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- እስካሁን ድሮ የነበረውን አሠራር ነው ተከትለው እየሠሩ ያሉት፡፡ ከዚያ አልወጡም፡፡ መደረግም ያለበትና አዋጁም እንደሚለው የአቅም ትስስር ያላቸው አካላት ካሳውን ባይገምቱት ይሻላል ነው፡፡ ይህ ማለት አልሚው ካሳ ከፋይ ስለሚሆን የካሳ ክፍያው መጠን እንዲቀንስለት ነው የሚፈልገው፡፡ ከባለንብረቱ ወገን ደግሞ በተቻለ መጠን ዋጋው ከፍ እንዲልለት ነው የሚፈልገው፡፡ ስለዚህ ከሁለቱም ገልተኛ የሆነ አካል ግምቱን ቢሠራው ይሻላል በሚል እነዚህን አማራጮች አስቀምጦ ነበር፡፡ ግን ተፈጻሚ አልሆነም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ አዋጁ እንዲህ ያለውን መፍትሔ ሊሆን የሚችል ድንጋጌ ካስቀመጠ፣ ችግሩ አዋጁን በአግባቡ ካለመተግበር የመጣ ነው ወደ የሚል መደምደሚያ ይወስዳል ማለት ነው?

አቶ ደረጀ፡- አዎ፣ አለመፈጸሙ እንጂ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች አስቀምጧል፡፡ እንዲህ ሲደረግ መፍትሔ ይኖራል፡፡ ምክንያቱም ግምት የሚሠራው አካል ገለልተኛ መሆን መቻል አለበት፡፡ አሁን በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች አካባቢ ያለው ችግር ከኅበረተሰቡ ጋር በቅርብ ያሉ ናቸው፡፡ ካሳ ይከፈልበት ተብሎ የሚቀርበው ንብረት በአንድም በሌላ የራሳቸው ንብረት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እነሱ ዋጋውን በማጋነን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በነገርህ ላይ አንዳንድ ክልሎች በክልል ደረጃ ለሚያካሂዱት ልማት ለተነሺዎች የሚከፍሉት ካሳና ፌዴራል መንግሥት ይክፈል ብለው የሚጠይቁት የተለያየ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው እነሱ ዝቅ ያለ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ የፌዴራል ሲሆን ደግሞ ሦስትና አራት እጥፍ ያደርጉታል፡፡ ስለዚህ ይህንን መቁረጫ አንዱ መንገድ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደሮች አውጥቶ ገለልተኛ በሆነ አካል ግምት እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት እያዘጋጃቸው ያሉ ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ የአዋጅ ማሻሻያም ይጠበቃል፡፡ በተለይ የካሳ አከፋፈሉ በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች ይሁን የሚባል ነገርም አለ፡፡   

ሪፖርተር፡- ስለችግሩ ይህንን ያህል ካልን ከመንገድ ልማት ጋር ተያይዞ ለካሳ በአማካይ በዓመት ምን ያህል ይወጣል? እንደምንሰማው በተጨባጭ እየታየ ካለው ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ከሚጠይቀው ወጪ በላይ ለካሳ ክፍያው የሚወጣው ይበልጣል ይባላል፡፡ ይህ የሚሆነው ለምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- አዎ ይወጣል፣ ውሸት አይደለም፡፡ የአንዳንድ ፕሮጀክቶች ወጪ ከግንባታቸው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ተቋሙ እየተቸገረበት ያለው አንድ ነገር ይህ ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ ምክንያት ወደፊት ፕሮጀክቶቹን ማካሄድ ከማንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ለካሳ ክፍያ የሚጠየቀው ገንዘብ እጅግ ከአቅም በላይ የሆነና ለመገመትም የሚያቅት ነው፡፡ ይህንን በማስረጃ ለማሳየት በአንድ ፕሮጀክት ያጋጠመንን ልጥቀስልህ፡፡ አፋር ውስጥ ነው፡፡ የቴምር ዛፍ ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ከአንድ የቴምር ዛፍ ስምንት ኩንታል እናገኛለን ተብሎ በዚህ ሥሌት ካሳ እንዲከፈል ተጠየቀ፡፡ በዚህ ረገድ ልምዱ ስለሌለን እስኪ ጎግል እናድርግና ከአንድ ቴምር ዛፍ ምን ያህል ኩንታል ይገኛል በማለት የሌሎች አገሮችን ልምድ ለመውሰድ ሞከርን፡፡ ቴምር አምራች የሚባሉ ሞሮኮ፣ ሱዳንና የመሳሰሉ አገሮችን መረጃ ሰበሰብን፡፡ በቴምር ምርት ከፍተኛ የሆኑ አምራቾች ከአንድ ቴምር ዛፍ የሚያገኙት ሁለት ኩንታል መሆኑን ማረጋገጥ ቻልን፡፡ በእኛ አገር ግን ከአንድ የቴምር ዛፍ እናገኛለን ተብሎ የቀረበው  ስምንት ኩንታል ነው፡፡ እንግዲህ ይታይህ ዛፉ ራሱ ስምንት ኩንል የመሸከም አቅም አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን ላቀረቡት ወገኞች ዓለም አቀፍ መረጃው እንኳን ይህንን ነው የሚያሳየው፣ ያቀረባችሁት ነጠላ ዋጋ ትክክል አይደለም ብለን መረጃውን አያይዘን ለወረዳው ላክን፡፡ እነሱም ከተነቃ እንግዲህ ምን ይደረጋል ብለው ነው መሰለኝ ስድስቱን አስቀርተው በሁለቱ ኩንታል ተስማሙ፡፡ እኛ ስድስቱን ከተውልን ብለን ሁለቱን ተቀበልናቸው፡፡ ስለዚህ አንዳንዱ ነገር ለመከራከር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ተቋሙ ይህንን ሁሉ ነገር የሚያደርገው አላግባብ ላለመክፈል ነው፡፡ የመንግሥትን ገንዘብ ያላግባብ እንዳይወጣ ለማድረግ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግን ከዚህ ውጪ ብናድነው እንኳን፣ በክርክር በሚፈጀው ጊዜ ለሚዘገየው ሥራ በሌላ በኩል በካሳ ያወጣዋል፡፡ ይህ እየጎዳን ነው፡፡ በበጀት ላይም የሚመጣ ጫና አለ፡፡ ስለዚህ ሕጉ እኛን ሊያግዝ ይገባል፡፡ አልሚን የሚያግዝ ሕግ መኖር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከወሰን ማስከበርና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ሌላው እንደ ትልቅ ተግዳሮት የሚነሳው ጉዳይ ደግሞ ሕገወጦች ሳይቀሩ ተገቢው ካሳ አልተከፈልንም በማለት ፍርድ ቤት በመሄድ የሚያቀርቡት አቤቱታ፣ የተቋሙን ሥራ እየፈተነ መሆኑም ይነገራል፡፡

አቶ ደረጀ፡- አዎ፣ አዎ፣ በዚህ ረገድ በጣም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ አንዱ ችግራችን ከፍርድ ቤት ጋር ይያያዛል፡፡ በርካታ የካሳ ክፍያ ፋይሎች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ከ4.4 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ክሶች አሉበት፡፡ እነዚህ ክሶች በእኛ በኩል አግባብነት ያላቸው አይደሉም፡፡ እንዲያውም ከሙስና ጋር የተያያዙ ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ተፅዕኖዎች ናቸው ያሉብን፡፡ ፍርድ ቤቶቹ ራሳቸው ጫና ያሳድሩብናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሲፈርዱብን እንኳን ይግባኝ እንዳንል በተለያዩ መንገዶች የሚፈጥሩብን ጫና አለ፡፡ የተፈረደብንን ፋይል ኮፒ አድርጎ ለመስጠት እንኳን ቢሮክራሲው ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ መካከል አፈጻጸም ተልኮ ከባንክ የተቋሙ ገንዘብ እየተወሰደ ነው ያለው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አካውንት ነው ገንዘቡ እየተወሰደ ያለው፡፡ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ኃላፊዎችን እያሰሩ ጭምር ነው ገንዘብ እየተወሰደ ያለው፡፡ ይህንን ጉዳይ በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ለመንግሥት አስረድተናል፡፡ ፍርድ ቤቶችን በሚመለከት እየሆነ ያለውን ነገር መንግሥት ሊያየው ይገባል፡፡ ከሥነ ምግባር አንፃር ሳይቀር መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የካሳ ጥያቄ አለ ብለው ክስ የሚመሠረቱ ወገኖች ክስ የሚመሠርቱት ጥያቄው በተነሳበት አካባቢ ባሉ የወረዳና የከተማ ፍርድ ቤቶች ማለት ነው?

አቶ ደረጀ፡- አዎ፣ የመንገድ ልማቱ በሚካሄድበት አካባቢ ባሉ ፍርድ ቤቶች ነው፡፡ ይህም ተፅዕኖ አለው፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት ይህንንም መቆጣጠር አለበት የምንለው፡፡ ይህንን ሁሉ ለመንግሥት በሚገባ አሳውቀናል፣ ማብራሪያ ሁሉ የሰጠንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከ4.4 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የክስ መዝገብ የተከፈተበት ዋነኛ የክስ ጭብጥ ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- ክሶቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ የካሳ ክፍያ ግምት አነሰኝ የሚል አለ፡፡ ሙሉውን ሊገመትልኝ ሲገባ ግማሹ ነው የተገመተልኝ የሚሉና ሌሎችም ተያያዥ ክሶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፕሮጀክት ላይ ያጋጠመንን ልጥቀስልህ፡፡ እኛ ካሳ የምንከፍለው ለወሰድነው መሬት ነው፡፡ ያልወሰድነው ትርፍ መሬት ለእኛ ምንም አያደርግልንም፣ ለእርሻ አይሆንም፣ ለአትክልት አይሆንም፡፡ ስለዚህ ላልተጠቀማችሁበት መሬት ካሳ ክፈሉን የሚል ክስ ሳይቀር አለ፡፡ ይህ በፍፁም ከአሠራር ውጪ የሆነ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠሩ ክሶች አሉ፡፡ ስለዚህ ከፍርድ ቤቶች ጋር የተያያዘው ነገር በጣም ውስብስብ ሆኗል፡፡ ይህንን ሁሉ የሚፈታ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮች ባሉባቸው ፕሮጀክቶች ላይም ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ስለሚችል፣ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ የመንገድ ሥራው ይቆማል? ወይስ ክርክር እየተደረገበት ይቀጥላል?

አቶ ደረጀ፡- በአንዳንድ ቦታዎች የመንገድ ግንባታ ሊቆም ይችላል፣ ሊያግዱትም ይችላሉ፡፡ አዋጁ የሚያዘው በማንኛውም በሚነሳ ንብረት ላይ ቅሬታና ክርክር ካለ መረጃዎች ተይዘው የባንክ ሒሳብ ብሎክ ተደርጎ ክርክሩ ይቀጥላል፡፡ ንብረቱ ተነስቶ የግንባታ ሥራው ይካሄዳል ነው የሚለው፣ ሕጉ ይህንን ይላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ክርክር ያጋጠመበትን ቦታ ትተን ግንባታው ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ አስቁመውን የምንከራከርበት ጊዜም አለ፡፡ በፍርድ ቤቶች አንዳንድ ጊዜ እኩል አለማየት ነገር አለ፡፡ አንደኛ አልሚውን እንደ ጨቋኝ የማየትና ለሌላው የመወገን ነገር ይታያል፡፡ ሕግ ለሁሉም እኩል ነው፡፡ ለከሳሹም ለተከሳሹም እኩል ነው፡፡ እኛ እንደ አልሚ ወደ እኛ የሚመጣ ክስ ቢኖርም፣ እስከ መጨረሻው ድረስ በቂ ክርክር አድርገንበት ፍትሕ ማግኘት ነው የምንፈልገው፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች በተፅዕኖና አስቀድሞ በሚሠሩ ተንኮሎች ገንዘቡን ከሳሾች እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በቂ ክርክር ሳይደረግና በይግባኝ ወደ ሌላው ፍርድ ቤት እንዳንሄድ የሚደረጉ ያልተገቡ ድርጊቶች ተቋማችንን ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡ በተለይ ይግባኝ እንዳንል ከተደረገ በኋላ አፈጻጸም በመያዝ አስቀድሞ ገንዘብ መውሰድ የተለመደ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡     

ሪፖርተር፡- እስከ መጨረሻው ሄዳችሁ ውሳኔ ሳታገኙ ከባንክ ሒሳባችሁ እንዴት ገንዘብ ማውጣት ይቻላል?

አቶ ደረጀ፡- አይፈቀድም፣ ይህ እኮ ትክክል አይደለም፡፡ ሕጉማ የሚፈቅደው እስከ መጨረሻው ድረስ ሄደን እንድንከራከር ነው፡፡ እስከ ሰበር ችሎት መሄድ ነበረብን፡፡ ነገር ግን እኛ ወደ ላይ ፍርድ ቤት ሳንሄድ በሥር ፍርድ ቤት የተወሰነውን አስቀድመው ያስፈጽሙታል፡፡ ታች የተወሰነብንን ውሳኔ ተገቢውን ክርክር ሳናደርግበትና ይግባኝ ሳንጠይቅበት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኛ በሌለንበት ቀኑን በማዛባትና በመሳሰሉ ድርጊቶች ይፈጸማል፡፡ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚደረገው ነገር ይህንን ተቋም ይዞት ሊወድቅ ደርሷል፡፡ አሁን ከሁሉም በላይ በእጅጉ የሚያስፈራው ይህ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብሎ ያነሳሁትን ጥያቄ ልደግም ነው፡፡ ለካሳ በዓመት ምን ያህል ታወጣላችሁ?

አቶ ደረጀ፡- የካሳ ክፍያዎች መጠን ከዓመት ዓመት ይለያያል፡፡ በዚህ ዓመት ካሳ አልከፈልንም እንጂ ከዚያ በፊት በየዓመቱ ከ10 እስከ 12 ቢሊዮን ብር እናወጣለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የካሳ ክፍያ አፈጻጸም እንዴት ነው የሚከናወነው? በአንድ ፕሮጀክት ላይ ምን ያህል የካሳ ተከፋዮች ይቀርባሉ?

አቶ ደረጀ፡- የገንዘብ መጠኑ የሚወሰነው እንደ ንብረቱ ዓይነት ነው፡፡ በአንድ ፕሮጀክትና በአንድ ሰነድ አራት መቶና አምስት መቶ ካሳ ተከፋዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በየዓመቱ የግምት ሥራ እንሠራለን፡፡ በ2015 በጀት ዓመት በ196 ፕሮጀክቶች ላይ የካሳ ግምት ሥራ ሠርተናል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በጨመሩ ቁጥር የካሳ ክፍያውም እየናረ ነው የሚሄደው፡፡ በዚህ ዓመት በበጀት እጥረት ምክንያት ብዙ ግዥ አልተደረገም እንጂ፣ በዓመት ከ60 እስከ 70 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በነባሩ ላይ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ሁለተኛ የካሳ ክፍያ ሥራ በአንዴ ተሠርቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በጊዜያዊነት የወሰድነው ካምፕ ኳሪ (ካባ) ቦታ አለ፡፡ ለተለዋጭ መንገዶች ተብሎ የሚወሰድ ቦታ አለ፡፡ እንዲህ ያሉትን በጊዜያዊነት የወሰድናቸውን ቦታዎች አስተካክለን መመለስ አለብን፡፡ ወደ ነበሩበት ይዞታ ለመመለስ የሚያዳግት ከሆነ ዘላቂ ክፍያ ይጠይቀናል፡፡ ስለዚህ የመንገዱ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላም የካሳ ክፍያ አለብን፡፡ ምክንያቱም ያንን ቦታ ወደ ትክክለኛ ቦታው መመለስ አለብን፡፡ ለሥራ ምቹ እንዲሆን አድርገን ነው መመለስ ያለብን፡፡ ለምሳሌ በጊዜያዊነት ወስደነው የነበረው የእርሻ መሬት ከሆነ፣ ለእርሻ ሥራ ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መሬቱ የማገገሚያ ጊዜ የሚጠይቅ ከሆነም ይህንን እናደርጋለን፡፡ አንድም ሁለት ዓመትም የማገገሚያ ጊዜ ሊፈልግ ይችላል፡፡ አዋጁ ስለሚፈቅድ የማገገሚያ ጊዜ ካሳ ከፍለን እናቆየዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ባያገግምስ?

አቶ ደረጀ፡- የማያገግም ከሆነ ዘላቂ ክፍያ ይከፈላል፡፡ ስለዚህ የፕሮጀክቱ ሥራ ቢጠናቀቅም የካሳ ክፍያው ጉዳይ ሊቀጥል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከካሳ ክፍያ ጋር ያለው አሠራር ይህንን ያህል የተወሳሰበና ፈታኝ መሆኑ እርግጥ መሆኑ ከታወቀና እናንተም እየተቸገራችሁበት ከሆነ፣ እንደ ተቋም መፍትሔ ያቀረባችሁት ነገር አለ? እየወሰዳችሁት ያለውስ ዕርምጃ ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- ችግሩ በርካታ ቢሆንም፣ እኛ እንደ ተቋም ብዙ ነገር ሠርተናል፣ እየሠራንም ነው፡፡ መፍትሔ ይሆናሉ ያልናቸውን ነገሮች በየጊዜው እያስጠናን ለመተግበር ሞክረናል፡፡ ‹‹ከአሠራር አኳያ ምን ማድረግ ይገባናል?›› በማለት መፍትሔ ያልናቸውን ለመተግበር እንሞክራለን፡፡ ለምሳሌ አሠራሩን ዲጂታላይዝ ማድረግ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ንብረት የመለየት ሥራ ሁለት ጊዜ ነው የምንሠራው፡፡ መጀመርያ ዲዛይኑ ሲሠራ በመንገድ ክልሉ ውስጥ ያሉ ንብረቶችን እንለቅማለን፡፡ እነዚህን በመንገድ ክልል ውስጥ የለቀምናቸውን ንብረቶች በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች በአግባቡ ተመዝግበው መቀመጥ መቻል አለባቸው፡፡ እሱን ለማድረግ ‹‹ፕሮፐርቲ አይደንቲፊኬሽን›› በቴክሎጂ መታገዝ አለበት ብለን የድሮን ግዥ አካሂደናል፡፡

ሪፖርተር፡- የድሮን ግዥው ዓላማው ምንድነው?

አቶ ደረጀ፡- የድሮን ግዥው ዋናው ዓላማ አሠራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ነው፡፡ በመንገድ ክልል ውስጥ ያሉ ንብረቶችን አስቀድሞ በፎቶና በተንቀሳቃሽ ምሥል ለመያዝ ነው፡፡ እስካሁን በነበረን አሠራር መረጃው አለን፡፡ ምን ዓይነት ቤት ነው የሚለውን በሙሉ ለቅመን ዶክመንታችን ውስጥ አለ፡፡ ይህ ሰነድ ግን እኛ ጋ ነው እንጂ ያለው በፎቶና በምሥል የተደገፈ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በምሥል ሲደገፍ ምን ዓይነት ንብረት እንደሆነ ስለሚያሳውቅ፣ ሁለቱንም ሰነድ ለወረዳና ለከተማ አስተዳደሮች እንሰጣለን፡፡ ሕገወጥ ግንባታ የሚያካሂዱት እነሱ ስለሆኑ፡፡ እነሱ ካወቁት ከዚያ በኋላ የሚመጣ ንብረት ዋጋ የሌለው መሆኑን ለማሳየት ስለሚረዳን፣ በድሮን ምሥል ለመያዝ እንድንችል ድሮኑ ተገዝቷል፡፡ ይህንን በማድረጋችን ደግሞ በሕግ ፊትም መከራከሪያ ይሆናል፡፡ ሌላው ተቋማችን በጣም እየተፈተነ ያለው ነገር ከመሬት በታች ያሉ ንብረቶችን የሚመለከት ነው፡፡ ጉዳዩ በተለይ ከውኃ ጋር ይያያዛል፡፡ በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች አካባቢ የውኃ መስመሮችን ለማስነሳት የሚጠየቀው የካሳ ክፍያ፣ ምናልባትም የሙሉ ከተማውን የውኃ መስመር ለመዘርጋት ከሚፈጀው ወጪ በላይ ነው የሚሆነው፡፡ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የካሳ ጥያቄ የሚቀርብበትም ነው፡፡ ይህ ትክክኛ ዋጋ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች በቂ በጀት ስለማይኖራቸው፣ በአጋጣሚ ከተቋሙ ሌላ ልማት ለመሥራት እስከ ማቀድ ይደርሳሉ፡፡ ስለዚህ የሌለ ካሳ ይጠይቃሉ፡፡ የውኃ መስመር ለማስነሳት ሦስትና አራት መቶ ሚሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ በአንድ ከተማ ውስጥ ግን ያን ያህል የተዘረጋ መስመር የለም፡፡ በዚህ ጉዳይ እነሱ ለመከራከር የሚሆናቸው መሬት ውስጥ ያለውን መስመር እኛ ስለማናውቀው ነው፡፡ ይህንን ለመከላከል ደግሞ ከመሬት ውስጥ ያሉ ንብረቶችን ፎቶ ሊያነሳ የሚችል መሣሪያ ግዥ እየተካሄደ ነው፡፡ ሌሎች መፍትሔ የሚሆኑ ያልናቸው ሥራዎችንም እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ቴሌ ካሉት ተቋማት ጋርም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ አካላት ጋር እንዴት እየሠራችሁ ነው?

አቶ ደረጀ፡- መሠረታዊ አገልግሎቶች (ዩቲሊቲ) የምንላቸው እንደ ቴሌ፣ መብራትና የመሳሰሉት ተቋማት ተጨማሪ ተግዳሮቶቻችን ናቸው፡፡ እነሱ ቢያንስ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ስለሆኑ ከእኛ ጋር ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው፡፡ ተናበን ለመሥራት እየጣርን ነው፡፡ የእኛን መስመር ነው ተከትለው መሄድ ያለባቸው፡፡ ለእነዚህም ተቋማት የሚከፈለው ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ ለምሳሌ እጃችን ላይ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ያልከፈልነው 1.2 ቢሊዮን ብር አለ፡፡ መሠረተ ልማት እያጠፋን መሠረተ ልማት መገንባት የለብንም፡፡ ምክንያቱም የአገር ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ የእኛን ዲዛይን እንዲያውቁ፣ በእኛ መስመር ውስጥ አስቀድመው መስመር እንዲዘረጉ የማድረግ ሥራ እንሠራለን፡፡ አሁን ሥራ ባለበትና የእነሱ ንብረቶች ባሉባቸው ፕሮጀክቶች እኛ በምንፈልገው ጊዜና ፍጥነት ንብረት እንዲያነሱ በጋራ እንሠራለን፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም የተሻለ ነው፡፡ የሥራ ተቋራጮች ከገቡ በኋላ ብዙ ቦታ የዲዛይን ለውጥ በሚያጋጥምበት ጊዜ ግን የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ እኛ ንብረት ካነሳን በኋላ መንገዱ እንዲህ ተደርጎ ቢሠራ በሚል በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች የሚቀርብ አለ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የዲዛይን ለውጥ ሲደረግ እኛ ላይም ጫና ይፈጥራል፣ ገንዘብም ያባክናል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲዛይን ለውጥ የመንገድ ሥራዎችን ከማስተጓጎልና ከማራዘም በላይ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ ነው፡፡ የዲዛይን ለውጥ ሲደረግ ሁለት ጊዜ የካሳ ክፍያ እንድትፈጽሙ ያደርጋል ማለት ነው?

አቶ ደረጀ፡- አዎ፣ የሚያጋጥምበት ጊዜ አለ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንዳያጋጥም ደግሞ መፍትሔ የምንለውን እያደረግን ነው፡፡ የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመንደፍ ችግሩን ለመቅረፍ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ነገር ከእኛ አሠራር ውጪ ስለሆነ ልንቆጣጠረው በማንችለው ከባቢ ውስጥ ነው፡፡ የወረዳና የከተማ አስተዳደሮችን የማዘዝ ሥልጣን የለንም፡፡ ዩቲሊቲ ተቋማትንም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ያለውን ንብረት ቀድመን እናንሳ ብለን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የካሳ ክፍያውን የምትፈጽሙበት እናንተ ናችሁ፡፡ ስለዚህ በሥራችሁ ላይ ጣልቃ የሚገባና ያልተገባ ተግባር ፈጽመሟል ያላችሁትን አካል በሕግ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ይህ መብትስ የላችሁም?

አቶ ደረጀ፡- እስካሁን ድረስ ጠይቀን አናውቅም፡፡ በሕግ የምንጠይቅበት አግባብ የለም፡፡ እኛ አልሚ ነን፡፡ የጠየቅነው መሬት ላይ ላረፈው ንብረት ካሳ ክፈሉ ነው የምንባለው፡፡ ንብረቶቹ በትክክል በመንገድ ክፍሉ ውስጥ የገቡ መሆናቸውን የእኛ ባለሙያዎች ማረጋገጥ አለባቸው ብለን በመወሰን እየሠራን ነው፡፡ ምክንያቱም የከተማ ወይም የወረዳ አስተዳደሮች እንደፈለጉ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ነው፡፡ መንገዱ የማይነካውንም ንብረት ገምተው ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ የንብረቱን ትክክለኛነት የእኛ ባለሙያዎችና ለዚህ ሥራ የተመደቡ ሁሉ እንዲያረጋግጡ ማድረግ ጀመርን፡፡ በትክክል በመሬቱ ላይ ቡና ነበር ወይ? ጤፍ ነበር ወይ? የሚለውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ ጀምረናል፡፡ ምክንያቱም የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች ብዙውን ጊዜ መሬቱ ላይ ይለማ የነበረውን ሰብል ትተው፣ የካሳ ክፍያውን ከፍ የሚያደርግ ምርት እየመረጡ ስላስቸገሩ እንዲህ ያለውን አሠራር ሁሉ ለመተግበር ተገደናል፡፡ የእኛን ባለሙያዎች በቀጥታ ተሳታፊ በማድረጋችን የሌለ ሰብል ነበር የሚመረትበት እየተባለ ይቀርብ የነበረውን የካሳ ጥያቄ ለማስወገድ ችለናል፡፡ መፈናፈኛ እንዳይኖራቸው አድርገናል፡፡ እስካሁን መከልከል ያልቻልነው የንብረቶችን ነጠላ ዋጋና ለግንባታዎች የሚሰጠውን ደረጃ ነው፡፡ ነገር ግን 200 ካሬ ሜትር የሆነውን ቦታ 400 ካሬ ሜትር ብለው እንዳያመጡ ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ መንገድ ትልቅ ሀብት ነው፣ ብዙ መዋለ ንዋይ የሚፈስበት ነው፡፡ መንግሥት መንገድ የሚሠራው ለሕዝብ ነው፣ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፣ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ነው፣ ይህንን እያንዳንዱ ዜጋ ሊያውቀው ይገባል፡፡ ብክነትን ለመቀነስና አላስፈላጊ ወጪ ለማስቀረት ለወሰን ማስከበርና ለካሳ ክፍያ ችግሮች ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በዚህ ረገድ ብዙ መሥራት ያስፈልገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው ኃላፊነት ግን የእናንተም መሆን የለበትም? የቁጥጥር ሥራው በእናንተ የበላይነት መከናወን አልነበረበትም?

አቶ ደረጀ፡- የእኛ መሆን አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ደረጀ፡- የእኛ መሆን የማይችልበት ምክንያት ሥልጣን ስለሌለን ነው፡፡ እኛ አልሚ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ሥልጣን የለንም ትላላችሁ? ገንዘብ እኮ የምትከፍሉት እኮ እናንተ ናችሁ?

አቶ ደረጀ፡- ለዚህ ነው አጠቃላይ አሠራሩ ባለቤት ያስፈልገዋል የምንለው፡፡ አንደኛ ገንዘብ የሚሰጠን የገንዘብ ሚኒስቴር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያስገምታል፣ ይከፍላል፣ ሥራውን ያስተባብራል፣ መንገዱን ያሠራል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ግምት የሚሠራ አካል አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን አሠራር ከወረዳና ከከተማ አስተዳድሮች አውጥቶ በሕጉ ላይ በተቀመጠው መሠረት በገለልተኛ አካል ማሠራት ነው፡፡ ነፃ በሆነ አካል መሠራት አለበት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በነፃ አካል የሚሠራም ቢሆን የቁጥጥር ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ቁጥጥር እንዳይኖር ያደረገው ከነጠላ ዋጋና ከምርታማነት ጋር የተያያዘ ስታንዳርድ አለመኖሩ ነው፡፡ ይኼ ከባድ ሥራ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ምርታማነትን በተመለከተ የግብርና ሚኒስቴር ያውቃል፡፡ ስለዚህ ይፋዊ ስታንዳርድ ሊወጣ ይገባል፡፡ የገበያ ዋጋ በየጊዜው ቢለዋወጥም በየጊዜው ማሻሻል ይችላል፡፡ የኮንስትራክሽንንም እንዲህ ማድረግ ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህንን ስታደርጉ ዋጋ የማውጣቱ ሥልጣን ግን የማነው?

አቶ ደረጀ፡- የእኛ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው፡፡ የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር ነው፡፡ ይህንን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡ እነዚህን ነፃ ተቋማት የምንላቸውም ቢሆኑ ያለመረጃ በገለልተኝነት ሊገምቱ አይችሉም፡፡ ችግሩ እኮ መነሻ ነገር ስለሌለ ሁሉም እየተነሳ የፈለገውን ዋጋ ይተምናል፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ ለግምት መነሻ የሚሆን ስታንዳርድ መንግሥት ማውጣት አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች