Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና አስተዳዳራዊ ነፃነት በመስጠት፣ የራሳቸውን ሀብት እንዲያመነጩ የሚፈቅድ ሕግ ለመደንገግ የተዘጋጀው አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ሲፀድቅ፣ በርካታ የፓርላማ አባላት የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዳያመጣ በሚል ሥጋት ተቃውሟቸውን ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት፣ የቀረቡ ግብዓቶችን በማካተት እንዲፀድቅ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ያቀረበው ረቂቅ፣ በአራት ተቃውሞና በ13 ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡

ይሁን እንጂ የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ ወደ ሥራ ሲገባ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን አሰምተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) አዋጁ ከትምህርት ፍትሐዊ ተደራሽነት ጋር ሊያመጣ የሚችለውን አንድምታ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ከፍለው ለመማር የሚያስችል የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መደላድሎች አሉ ወይ በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ መጀመርያ ማኅበራዊ መደላድሉን መፍጠር መቅደም አለበት ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ወ/ሮ ተስፋነሽ ተፈራ የተባሉ የምከር ቤቱ አባል፣ ከድህነት ወለል በታች የሆነ በርካታ ሕዝብ በሚኖርባት አገር ውስጥ፣ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በውድ ክፍያ የሚያስተምሩ ከሆነ መክፈል የሚችለውን ብቻ በማስተማር መክፈል የማይችለውን ማስቀረት አይሆንም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል መክፈል ለማይችሉ ድጎማ ይደረግ ቢባል እንኳ፣ መክፈል የሚችልና የማይችል በሚል መለያየቱ በተማሪዎች ላይ አሉታዊ ሚና ያሳድራል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ ገንዘብ የሚያስተምሩ ከሆነ፣ ከግል ዩኒቨርሲቲዎች በምን ይለያሉ በማለትም አክለው ጠይቀዋል፡፡

አዋጁ እንደሚያብራረው መንግሥት ለዩኒቨርሲቲዎች በጀት ይመድባል፡፡ በጀቱም ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና አካታችነትን ለማረጋገጥ የመግቢያ መሥፈርት አሟልተው የትምህርት ወጪያቸውን መሸፈን ለማይችሉ ተማሪዎች፣ በተጓዳኝ የማስተማሪያ ሆስፒታል ላላቸው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚውል፣ አፈጻጸሙ ግን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ እንደሚወሰን ተደንግጓል፡፡

አዳሙ ቀነዓ (ረዳት ፕሮፌሰር) የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው አዋጁ ውድድር ለመፍጠር ሊያግዝ ቢችልም እንኳ፣ በርካታ መሰናክሎች ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት ውስጥ እንደሚኖር ጠቁመው፣ ‹‹እኔ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን የሀብታሞች ትምህርት ቤት ብዬ ነው የምቀበለው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም አዋጁ አገራዊ ፋይዳ አለው ተብሎ የተዘጋጀ ሊሆን ቢችልም፣ በአሁኑ ወቅት ማኅበረሰቡ እየጠየቀ ያለው ይህንን አለመሆኑንና በድሆችና በሀብታሞች መካከል ሌላ ልዩነት እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ አንዳንዱ ዕውቀት አለው፣ ነገር ግን ገንዘብ የለውም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ገንዘብ ኖሮት ዕውቀት ያለው ስለሚኖር፣ ለዚህ መፍትሔው መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ደግፎ የተሻለ ዜጋ መፍጠር መቻል ይገባል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆነውን የማኅበረሰብ ክፍል ያገለለ ስለመሆኑ በመጥቀስ፣ ‹‹ጉዳዩ እዚህ ውስጥ ካለን አባላት ውስጥ አብዛኞቻችን ያሳስበናል፤›› ያሉት አዳሙ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ለምሳሌ እኔ ከተወከልኩበት ኢሉአባቡር ዞን ዲራሞ ወረዳ አንድ ሰው በዚህ ሁኔታ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ይገባል ብዬ አላስብም፡፡ እስኪ ሁላችንም የምክር ቤት አባላት የወጣንበትን ማኅበረሰብ እንይ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ይህ ጊዜውን ያልጠበቀ አዋጅ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሚፀድቅ ውሳኔ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፣ ካልሆነ ታሪካዊ ስህተት እንዳንሠራ ሥጋት አለኝ፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

አቶ ከድር እንድሪስ የተበሉ የምክር ቤት አባል ደግሞ አሁን አገርና ሕዝብ ካሉበት ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ አኳያ ሕዝቡ በገንዘብ ከፍሎ መማር ይችላል ወይ ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አክለውም የአዋጁ አጠቃላይ ዕሳቤ የሊበራሊዝም አስተሳሰብ የተጫነው ይመስላል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ከፍሎ ለመማር የሚችልበት ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ጊዜው አሁን ስላልሆነ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

‹‹በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው አሠራር ግልጽ ባልሆነበት በዚህ ጊዜ፣ አዋጁን የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ውይይት ሳያደርጉበት ለማፅደቅ መቸኮል የለብንም፤›› ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ሱመያ ደሳለኝ የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ፍሬው ተስፋዬ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ አዋጁ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ከጀመሩት ነፃ ተቋማትን የመገንባት ዕሳቤ ጋር አብሮ የሚሄድ ዓላማን የያዘ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋ በልጂጌ ዋናው መነሻ የመንግሥት ድጎማ ወይም በጀት ለማቋረጥ ሳይሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎች ካላቸው አቅም አኳያ ተጨማሪ የገቢ ማግኛ መንገዶችን መፍጠርና አቅም ማጠናከር እንጂ መንግሥት የሚመድበውን የድጎማ በጀት ለመቀነስ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ‹‹ከምንወክለው ሕዝብ የሚመጡ ተማሪዎች የመግቢያ መሥፈርቱን አሟልተው ነው፡፡ ነገር ግን ገንዘብ መክፈል ለማይችሉ ተማሪዎች መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ ያስተምራል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ ተማሪ ለመሳብ የራሳቸውን አሠራር መዘርጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...