ለመጪው 2016 ዓ.ም. ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለታቀደው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 4.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የሚያስፈልጋትን ነዳጅ ለማስገባት የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ ቪቶል የተባለው የባህሬን ኩባንያ በድጋሚ በማሸነፉ የኮንትራት ውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ2016 ዓ.ም. ለማስገባት ያቀደውን ሙሉ ለሙሉ ቤንዚን፣ እንዲሁም ከጠቅላላው የነጭ ናፍጣ ግዥ 40 በመቶውን ቪቶል ኩባንያ እንደሚያስገባ ታውቋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ለአንድ ዓመት የሚያስፈልገውን 760 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቤንዚንና 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ ኩባንያው ያቀርባል፡፡ ቪቶል ጨረታውን ያሸነፈው ከሁለት ሌሎች ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ እንደሆነ፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ቪቶል እየተጠናቀቀ ላለው የበጀት ዓመት በተመሳሳይ የወጣውን ጨረታ አሸንፎ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2016 በጀት ዓመት ወደ አገር ለማስገባት ከታቀደው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ውስጥ 2.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያህሉ ነጭ ናፍጣ ነው፡፡ ቀሪው 760 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ሲሆን፣ 680 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ ለማስገባት ከታቀደው 2.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ ውስጥ ደግሞ 1.2 ሚሊዮን የሚሆነውን ቪቶል ኩባንያ የሚያቀርብ ሲሆን፣ መቶ በመቶ (760 ሜትሪክ ቶን) ቤንዚን የሚያቀርበው ይኸው ኩባንያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሁለት መንገዶች የነዳጅ ግዥ የምትፈጽም ሲሆን፣ አንዱ መንግሥት ከመንግሥት ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት ነው፡፡ ለበጀት ዓመቱ ከሚያስፈልገው ነጭ ናፍጣ 60 በመቶና ሙሉ በሙሉ የአውሮፕላን ነዳጅ ከኩዌት ይገባል፡፡ ሁለተኛው ነዳጅ የሚገባበት መንገድ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማድረግ በሚፈጽም ግዥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚያስልጋት ሙሉ የቤንዚን ፍጆታ የሚገባው በዓለም አቀፍ ጨረታ በሚደረግ ውድድር እንደሆነ አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ቤንዚን ከዚህ ቀደም ከሱዳን ይገባ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከሱዳን የሚገባው ነዳጅ በመቋረጡ በጨረታ ግዥው ይፈጸማል፡፡ አሁን ግን በጨረታ ያሸነፈው ቪቶል የሚያስገባው መሆኑን ከአቶ ታደሰ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዓመታዊ ፍጆታው 40 በመቶ የሚሆነውን የነጭ ናፍጣም በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ጨረታ ተገዝቶ ይገባል ብለዋል፡፡
ለ2016 በጀት ዓመት ያስፈልጋል ተብሎ የታቀደው ነዳጅ ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በስምንት በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በተናጠል ሲታይም ቤንዚን ስምንት በመቶና ነጭ ናፍጣ አምስት በመቶ ጭማሪ ይኖራቸዋል፡፡ ከሌላው ጊዜ የተለየ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት የአውሮፕላን ነዳጅ መሆኑን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በ2016 ዓ.ም. የሚገባው የአውሮፕላን ነዳጅ በሃያ በመቶ ጭማሪ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት በኮቪድ ምክንያት ቀንሶ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመምጣቱ፣ የነዳጅ ፍጆታም የሚጨምር በመሆኑ ከሌላው ጊዜ ከፍ ሊል መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው የነዳጅ ዋጋ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ሳቢያ ያልተረጋጋ ቢሆንም፣ ከዓምናው መጠነኛ መሻሻል እንዳለው ግን ተገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚያመለክተው፣ በ2016 በጀት ዓመት ለአጠቃላይ የነዳጅ ግዥ ወጪ የሚጠበቀው 4.4 ቢሊዮን ዶላር ሊሆን የቻለው፣ ዘንድሮ ከዓምናው የተሻለ ዋጋ በመቅረቡ ነው፡፡ በዓምናው ዋጋ ቢሰላ ኖሮ በ2016 በጀት ዓመት የሚገባው ነዳጅ ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር ሊያስወጣ ይችል እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ የ2015 የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ ያስገባቸውና የምታስገባው ነዳጅ መጠን 3.9 ሚሊዮን ቶን ነው፡፡
በጨረታ ግዥው የሚፈጸመውን ነዳጅ ለማስገባት በቪቶል ኩባንያና በኢትዮጰያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መካከል የተደረገውን ስምምነት፣ የቪቶል ባህሬን ኃላፊና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ፈርመዋል፡፡