Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመስጅድ ፈረሳን በመቃወም እንዲቆም ለመጠየቅ በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የሰው ሕይወት አለፈ

የመስጅድ ፈረሳን በመቃወም እንዲቆም ለመጠየቅ በተደረገ ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የሰው ሕይወት አለፈ

ቀን:

  • በ56 የፖሊስ አካላትና አጋዥ ኃይሎች ላይ ጉዳት ደርሷል
  • ‹‹በሕዝበ ሙስሊም ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ኢፍትሐዊና ኢዴሞክራሲያዊ በመሆኑ እናወግዛለን››

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

የእስልምና እምነት ተከታዮች በሸገር ከተማ የሚፈጸመውን የመስጅድ ፈረሳ በመቃወም፣ መንግሥት እንዲያስቆም በሰላማዊ ሠልፍ ጥያቄ ሲያቀርቡ በተነሳው ረብሻ በንፁኃን ላይ ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ ተሰማ፡፡

የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መንግሥት የመስጅድ ፈረሳን እንዲያስቆም የጠየቁት ዓርብ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄዱት ሰላማዊ ሠልፍ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የእስልምና እምነት ተከታዮቹ በአዲስ አበባ በታላቁ በአኑዋርና በኒን መስጅዶች ባካሄዱት ሠልፍ አበክረው ያሰሙት የተቃውሞ ድምፅ፣ ‹‹መንግሥት በሸገር ከተማ የሚፈጸመውን የመስጅድ ፈረሳ ያስቁም!›› የሚል ነበር፡፡

‹‹ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በታላቁ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በሌሎች አካባቢዎች መስጅድ ፈርሷል በሚል ምክንያት በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ ረብሻ የሁለት ሰዎች ሕይወት አልፏል፤›› ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ሕይወታቸው አልፏል ከተባሉት ሰዎች በተጨማሪ አራት ሰዎች ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በ37 የፖሊስ አመራርና አባላት፣ በ15 የፖሊስ አጋዥ ኃይሎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና መላካቸውን ኮሚሽኑ አመላክቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ናቸው በተባሉ ሁለት አውቶብሶች ላይ ጉዳት ደርሷል ተብሏል፡፡ መነሻውን በታላቁ አኑዋር መስጅድ አድርጓል የተባለው ረብሻ በቆርቆሮ ተራ፣ በጋዝ ተራ፣ በአመዴ ገበያ፣ ሰባተኛ አካባቢ መዛመቱንና በድርጊቱ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 114 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በታላቁ አንዋር መስጅድ የተቃውሞ ሠልፍ ሲደረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሠልፉን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ በመልቀቅ ዕርምጃ እንደወሰደ ከተሠራጨው የምስል ቀረፃ ማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመስጅድ ፈረሳውን እንዲያስቆሙ ባለፈው ሳምንት በደብዳቤ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን፣ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በበኩሉ፣ በከተማ አስተዳደሩ እየተፈጸመ ነው ያለው የመስጅድ ፈረሳ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ማውገዙ፣ በሸገር ከተማ 19 መስጅዶች መፍረሳቸውን አስታውቋል፡፡

ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ መግለጫ ያወጣው አዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ ‹‹መብቱን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ በወጣ ሕዝበ ሙስሊም ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው፣ ኢፍትሐዊና ኢዴሞክራሲያዊ በመሆኑ እናወግዛለን፤›› ብሏል፡፡ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ሊጠይቅ በወጣ ሙስሊም ላይ ዕርምጃ የወሰዱ የፀጥታ አካላት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድም ጠይቋል፡፡

የሰላማዊ መብት ጥያቄን ተከትሎ በታላቁ አንዋር መስጅድ የፀጥታ አካል  በወሰዱት ኢሕገ መንግሥታዊና ኢሰብዓዊ ዕርምጃ የሰው ሕይወት ማለፉን ጠቁሞ፣ ‹‹ጥቃት የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታ አካላት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ብሎ በቀጣይም፣ ‹‹የሚመለከተው አካል በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተከናወነ ያለውን ድርጊት እንዲያስቆምና ወደ ውይይት በመምጣት ሥር ነቀል የዕርምት ዕርምጃ ተጠናክሮ እንዲተገበር አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ብሏል።

ምክር ቤቱ፣ ‹‹የሃይማኖት ጉዳይና የእምነት ተቋማት ጉዳይ ሁሌም ቢሆን በስክነት መታየት ሲገባው፣ ቀደም ብሎም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእምነት ተቋማቱ ጉዳይ ሲከተሉት የነበረውን አካሄድ እንደ ተሞክሮ ከመውሰድ ይልቅ፣ የተሠራው አስነዋሪ ተግባር የአገራችንንና የከተማችንን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል፤›› ሲል ድርጊቱን አውግዟል።

በሸገር ከተማ መስጅድን በተመለከተ እየተከናወነ ያለው ድርጊት፣ ኃላፊነት የጎደለው፣ የሕዝበ ሙስሊሙን ክብር ያዋረደ፣ አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ የመንግሥት የለውጥ ሪፎርምን ወደኋላ የሚመልስ በመሆኑ ጉዳዩ እንደ አገር ሊታሰብበት ይገባል ሲልም አስገንዝቧል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...