የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከወሰን ማስከበርና ካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ከ4.4 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የክስ ፋይሎች እንደተከፈቱበት ተገለጸ፡፡
ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ቅሬታ አለን ባሉ ወገኖች በተመሠረተበት ክስ በሚሰጥ ውሳኔ፣ ያለአግባብ ከተቋሙ ባንክ አካውንት ገንዘብ እየወጣ መቸገሩንም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ወሰን ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አየለ ለሪፖርተር እንደገለጹት ባልተገባ መንገድ በፍርድ ቤት እየቀረበባቸው ያለው ክስ ተቋሙን እየተፈታተነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም 4.4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የክስ ፋይል እንደተከፈተባቸውና እየተከራከሩ ቢሆንም፣ አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
በእነዚህ ክሶች ፍርድ ቤቶች ተፅዕኖ የሚያደርጉባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ደረጀ በታች ፍርድ ቤቶች እየተፈረደባቸውና ተገቢውን ክርክር ሳያደርጉ አፈጻጸም እየወጣ ከተቋሙ የንግድ ባንክ አካውንት ገንዘብ እየተወሰደ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይግባኝ ለማለት እንኳን ዕድል ሳይሰጣቸው የሚወጣው አፈጻጸም የባንክ ቅርንጫፉ ኃላፊዎችን በማሰር ጭምር የሚፈጸም በመሆኑ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነባቸውም የአቶ ደረጀ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡
የመንግሥት ገንዘብና የሕዝብ ሀብት ባልተገባ የካሳ ክፍያ ጥያቄ ያለአግባብ እንዳይወጣ ለመከላከል እንቅፋት የሆነባቸው፣ በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚፈጸም አግባብ ያልሆነ ተግባር መንግሥት አውቆ መፍትሔ እንዲያበጅ በጽሑፍና በተለያየ መንገድ ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሁኔታው ከሙስና ጋር የተያያዘ እንደሆነ በማመልከትም ጉዳዩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የተቋማቸውን ህልውና የሚገዳደር ሊሆን ስለሚችልና በመንገድ መሠረት ልማት ግንባታ ላይም እንቅፋት ስለሚሆን፣ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻው ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከወሰን ማስከበርና ካሳ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ ሌሎች በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉ ሲሆን፣ በተለይ በመንገድ ወሰን ውስጥ የሚደረጉ ሕገወጥ ግንባታዎች፣ መንግሥትን ላላስፈላጊ ወጪ እየዳረጉ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ እንዲህ ያለው ሕገወጥ ተግባር በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች ተባባሪነት ጭምር የሚከናወን በመሆኑ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አፋጣኝና ሁነኛ የሆነ አሠራር መዘርጋት እንደሚያሻም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ መንግሥት ይህንን ችግር በሚገባ የሚገነዘብ መሆኑን ያስረዱት አቶ ደረጀ ችግሩን የሚፈታ ሕግ እየቀረፀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ከችግሩ አንፃር ሕጉ ወጥቶ በቶሎ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል ባይ ናቸው፡፡
አስተዳደሩ ወሰን ለማስከበር መንገዱ በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላሉ ንብረቶች በየዓመቱ ከአሥር እስከ 12 ቢሊዮን ብር ካሳ ሲከፈል መቆየቱ ታውቋል፡፡