በመጪው ቅዳሜ በይፋ ይመረቃል
ዘመን ባንክ በ1.5 ቢሊየን ብር ያስገነባውን ባለ 36 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉንና በመጪው ቅዳሜ ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ እንደሚመረቅ አስታወቀ።
ግንባታውን ያከናወነው የቻይና መንግስት ተቋራጭ (China Wu Y CO, LID ) ሲሆን ግንባታውን ለማጠናቀቅ አምስት አመታትን እንደፈጀበት ተገልጿል፡፡
የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘነበ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓም በሰጡት መግለጫ ፣ ሕንፃውን በ1.2 ቢሊዮን ብር ወጪ ለማጠናቀቅ ውለታ ከተገባ በኋላ ተጨማሪ ሥራዎች በመታከላቸው፣ ለአጠቃላይ ግንባታው 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
የዋና መሥሪያ ቤቱ ግንባታ መጠናቀቅ ባንኩ በራሱ ሕንፃ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ፣ ቀሪዎቹን የሕንፃ ክፍሎች በማከራየትም ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝና ለባንኩ ባለአክሲዮኖች ደንበኞች ከፍተኛ ዋስትናን እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የዋና መስሪያቤቱ ሕንጻ ግንባታ መጠናቀቅ ተበታትነው የቆዩትን የባንኩን የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ወደ አንድ ሕንጻ በመሰብሰብ ለደንበኞቹም ሆነ ለራሱ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለውም ተገልጿል።
ይህ ዘመናዊ ሕንጻ ሁሉንም የግንኙነት አማራጮች በቴክኖሎጂ ያቀፈ የመረጃ መሰብሰቢያና ማደራጃ እንዲሁም መተንተኛ ማዕከላት ያሉት፤ የአደጋ ጊዜ የነፍስ አድን የኤሌክትሪክ መሳሪያዎች የተገጠሙለት፤ ተለዋዋጭ የዓየር ሁኔታን የሚያመጣጥኑ፣ የሚቋቋሙና የሚያላምዱ መሰረተ ልማቶችን መያዙንም አመልክቷል።
ዘመናዊ የጽዳትና የንጽህና መጠበቂያ፣ እንዲሁም የአካል ብቃት ማጎልበቻ ክፍሎችን ፤ እስከ 200 ተሳታፊዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች እያንዳንዳቸው 13 ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዙ ስድስት አሳንሰሮች፤ 200 ተሽከርካሪዎችን ማቆየት የሚያስችል የምድር ቤትና ፎቅ ይዟል፡፡ ሕንጻው በ 2300 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን ከፊልና ሙሉ ምድር ቤቱን ጨምሮ 36 ወለሎች አሉት።
በተጨማሪም ደረጃቸውን የጠበቁና ልዩ የእንግዶችና የሰራተኞች መመገቢያ ቤቶች ፣ የምግብ ማዘጋጃ ክፍሎች ፣ የመዝናኛ አዳራሾችን የያዘ ሲሆን ፣ በቀጣይም ባንኩ በተረከበው ሕጋዊ ይዞታው ላይ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሕንጻ ግንባታ እንደሚያካሄድም አስታውቋል።
ዘመን ባንክ በዘንድሮው በጀት አመት የ5 ዓመት የስትራቴጂ እቅዱን እንዲሁም የ 10 ዓመት ሮድ ማፕ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ትግበራ መግባቱም ታውቋል።
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ፣ ዘመን ባንክ ባለፈው ዓመት የሥራ ክንውኑ ሁለት ቢሊየን ብር ማትረፉን ጠቅሰው ፣ ሊጠናቀቅ ጥቂት ወራት በቀሩት የዘንድሮው በጀት ዓመት ሦስት ቢሊዮን ብር ትርፍ ይገኛል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።