Monday, May 20, 2024

ከዛንዚባር ንግግር መልስ ያለው የመንግሥትና የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ቁመና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወትን በመቅጠፍና በማቁሰል፣ ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን ለከፋ ድህነት የዳረገውና ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የአገር ኢኮኖሚ ጉዳትና ኪሳራ ያደረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በድርድር ተቋጭቶ አንፃራዊ ሰላም የመጣ ቢመስልም፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው የሰላም ሁኔታ ግን እምብዛም በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው ተደጋጋሚ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡

ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ በሚይዘው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ፣  የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰውና መንግሥት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› እያለ የሚጠራው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየመው ቡድን፣ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በትንሽ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ጭምር በበርካታ አካባቢዎች በሚያደርሳቸው ጥቃቶች የሕዝቡ የደኅንነት ሥጋት እያየለ መጥቷል፡፡

ችግሩ የኦነግ ሸኔ ጥቃት ገፈት ቀማሽ ከሆነው ኦሮሚያና አዋሳኝ ክልሎች ለሚኖሩ ዜጎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ ከዚያም ያለፈ አገራዊ ዳፋና ቀውስ ሊያመጣ እንደሚችል በተለያዩ መንገዶች አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በቅርቡ በታንዛኒያ ዛንዚባር ደሴት ለዘጠኝ ቀናት ገደማ የሰላም ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በዛንዚባር በነበረው የመጀመርያው ምዕራፍ ንግግር ወሳኝ ነጥቦች ላይ ከስምምነት መድረስ ባይቻልም ሁለቱም ወገኖች ለቀጣይ ውይይት ፈቃደኛ ስመሆናቸው የንግግሩን መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጡት የተናጠል መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡  

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ የቆመለትን ዓላማ ለማሳካት ጦርነት አማራጭ ነው ብሎ እንደማያምን፣ በተደጋጋሚም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ እንደነበር አስታውቋል፡፡ ቡድኑ በስፋት ይንቀሳቀስባቸዋል ከሚባሉት አካባቢዎች ውስጥ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ቄሌም ወለጋ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ ምሥራቅ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ጉጂና ቦረና ገጠራማ አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከዛንዚባር ንግግር በኋላ  የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› አባላትም ሆኑ ራሳቸውን በታጣቂ ቡድኑ ስም የሚጠሩ የታጠቁ አካላት፣ ለአዲስ አበባ ቅርብ በሆኑና ከተጠቀሱት አካባቢዎች ውጪም በመንቀሳቀስ በንፁኃን ላይ ጥቃት እያደረሱ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በድርድሩ ማግሥት በቅርቡ ራሳቸውን የአሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት ብለው የሚጠሩና የታጠቁ አካላት በቢሾፍቱ፣ በአርሲ በቆጂና በወለንጪቲ አካባቢዎች ወደ ከተማ ዘልቀው እስር ቤቶችን ሰብረው በመግባት እስረኞችን እንዳስለቀቁ፣ እንዲሁም የመንግሥት ሹሞችንና ንፁኃንን መግደላቸውን ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኦነግ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዛንዚባር ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለ ምንም ስኬት ተጠናቋል ብለው አያምንኑም፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ተደራዳሪ አካላት በንግግራቸው አነስተኛ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንኳ ደርሰው ባለመውጣታቸው ጦርነቱ አሁንም ስለመቀጠሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁንም ተስፋ የማደርገውና ሕዝብም እያለ ያለው ወደ ሁለተኛ ዙር ንግግር በቶሎ እንዲገቡና በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲመጣ ነው፤›› የሚሉት አቶ በቴ፣ ይህ ሁለተኛ ንግግርና ድርድር መቼ እንደሚጀመር ባይታወቅም በሁሉም ዘንድ ተስፋ አሳድሯል ብለዋል፡፡

በዛንዚባር በነበረው ድርድር በፌዴራል መንግሥቱና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተነሱ ዝርዝር ሁኔታዎችና ስምምነት ላይ ያላደረሷቸው ጉዳዮች በግልጽ አለመነገሩን አቶ በቴ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም አካላት ወደ ንግግር ከመግባታቸው በፊት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሲናገር የነበረው፣ በሁለቱ አካላት መካከል የሚጀመረው ንግግር የመጨረሻ አለመሆኑን፣ በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ ለሚታሰበው ዋናው ንግግር መንገድ የሚከፍትና እንዴት ድርድር መካሄድ እንዳለበት ነገሮችን የሚያስቀምጥ ቅድመ ድርድር ነው በሚል መግለጫ መስጠቱን አውስተዋል፡፡

በመሆኑም ለመጀመርያ ጊዜ በተደረገው የሁለቱ አካላት ንግግር የሚነሱ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ለመስማማትና ለመነጋገር ከሆነ፣ ለዘጠኝ ቀናት የቆየው ንግግር ከሸፈ ማለት እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡

 በሌላ በኩል ዘጠኝ ቀናት የፈጀ ንግግር መደረጉ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ያስረዱት አቶ በቴ፣ ሁለቱ አካላት በጣም በተራራቀ መንገድ ሐሳብ ይዘው ቀርበው ቢሆን ኖሮ ከጅምሩ የዚህን ያህል ቀን መቀመጥ ላያስፈልጋቸው ይችል እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡

ስለዚህ ይህ በቅድመ ውይይቶች ላይ የተሻለ ስምምነት እንዳለ ቢያሳይም፣ ምናልባት መንግሥት የነበረው ዕሳቤ በዚያው ውይይቱን ጨርሶ ዕልባት ለመስጠት አቅዶ የሄደ እንደሚመስል አክለዋል፡፡

መንግሥት በአንድ ጊዜ ንግግርና ድርድር ለጉዳዩ ዕልባት መስጠት አስቦ ከሆነ ወደ ታንዛኒያ የሄደው፣ ጉዳዩ የመንግሥት ቁርጠኝነት ላይ የሚወሰን እንደሚሆን አቶ በቴ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

መንግሥት ለሚነሱ ቅድመ ሁኔታዎችና ለሰጥቶ መቀበል ያለው ቁርጠኝነት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ፣ ምን ያህል አዎንታዊ ምላሽ ሰጠ የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ወደ ትጥቅ የገባው አካል ጫካ እንዲገባ ያነሳሳው የራሱ የሆነ ዓላማ ስላለው፣ ይህ አካል የሚጠይቀው ጉዳይ ከተፈታለት ለመስማማት ችግር ያለበት አይመስለኝም ብለዋል፡፡

ለዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የነበረው ንግግር መጠናቀቁን ተከትሎ ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በኦሮሚያ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋምና የኦሮሞ ነፃነት ታጣቂዎች ስምምነት ላይ እስኪደረስ ትጥቅ ሳይፈቱ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ፣ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ሪፎርም ተካሂዶ ወደ መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ይግቡ የሚል ጥያቄ ማቅረቡን፣ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት መቀበል እንዳልፈለገ ያመለክታሉ፡፡

ይህን በተመለከተ ሪፖርተር የሽግግር መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ይቋቋም መባሉን እንዴት ይመለከቱታል በማለት የጠየቃቸው አቶ በቴ፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት ካልተቻለ ምን ይቻላል? የማይቻል ነገር ያለ አይመስለኝም፣ እሱ ካልተቻለ ያ ኃይል ምን አግኝቶ ነው ፖለቲካው ውስጥ የሚገባው?›› ሲሉ ጥያቄ መሰል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

‹‹ዋናው ነገር እኮ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ ለመስጠት መንግሥት ፈቃደኛ አይደለም፣ በመሆኑም የእኛን ፓርቲ ጨምሮ ሰላማዊ ፓርቲዎች በር ስለተዘጋባቸውና ከምርጫ ፉክክር ውጪ በመደረጋቸው የትጥቅ ትግል እንዲሰፋ አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በምርጫ ሥርዓት ውስጥ ባለማለፉ የሥልጣን ክፍፍሉ ውስጥ አልተሳተፈም፡፡ ባለመሳተፉ ድግሞ አሁን ለድርድር ያቀረበው የሽግግር መንግሥት መቋቋም ካልቻለ ይህ ድርጅት ምንም የተለየ ፍላጎት የሌለው በመሆኑ፣ የሚቀጥለው አገር አቀፍ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የድርድሩ ውጤት የታለመለትን ዓላማ አያመጣም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በድኅረ ታንዛኒያ ንግግር በኦሮሚያ ክልል አልፎ አልፎ የሚታዩ በመሣሪያ የታገዙ ጥቃቶች ተገቢ አይደሉም የሚሉት አቶ በቴ፣ መንግሥት በትንሹም ቢሆን ተኩስ ማስቆም እንኳ ባይችል ግጭቶች እንዳይሰፋፉና ባሉበት እንዲቆሙ ማድረግ አንዱ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት ይህን የተስፋፋ ግጭት ማስቆም አለመቻሉ እንደሚያሳስባቸው የገለጹት አቶ በቴ፣ በዛንዚባሩ ንግግር ማግሥት መንግሥት በመሀል፣ በምዕራብ፣ በደቡብ፣ በምሥራቅ ኦሮሚያ ኃይል አስማርቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ያለውን ችግር በጦርነት ዕልባት ለመስጠት የወሰነ በሚመስል ሁኔታ መጠነ ሰፊ ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህንን ጦርነት ቀጥታ ለመቀልበስ፣ አፀፋዊ መልስ ለመስጠትም ሆነ ለሌላ ዓላም እነሱ የሚሉትን በግልጽ ባላውቅም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም አብሮ ይህ ጥቃት እንዲስፋፋ እያደረገ ነው፡፡ ይኼ ለእኛ ያሳስበናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ በቴ ምናልባት የሰሞነኛው የተኩስና የግጭት እንቅስቃሴ ሲታይ በተለይ በመንግሥት በኩል የተያዘው ዓላማ ጦርነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሆነ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ላይ ድል በመቀዳጀት በሚቀጥለው ጊዜ በሚኖረው ድርድር የመደራደሪያ ነጥቡንና አቅሙን ከፍ ለማድረግ የታሰበ እንደሚመስል አብራርተዋል፡፡

 ይሁን እንጂ መቼም ቢሆን የዚህ ዓይነቱ መደበኛ ያልሆነ ጦርነት በአንድ ወቅት በተከፈተ ውጊያ እንደማይጠፋና ከተለመደው ጦርነት ለየት ያለ በመሆኑ፣ የሆነ ክፍለ ጦርን በመደምስስ ወይም የሆነ ቦታን በማስለቀቅ ጦርን በማድረቅና አቅምን በማዳከም የበላይነት የሚገኝበት ባለመሆኑ፣ በዚህ አካሄድም ማንም የበላይነቱን ሊይዝ አይችልም ብለዋል፡፡

አቶ በቴ በኦሮሚያ አልፎ አልፎ የሚታየውና የቀጠለው ግጭት በቀጣይ ጊዜያት ድርድር ለማድረግ ስለሚኖረው ጫና ሲያብራሩ፣ ጦርነቱ በተለይም መንግሥት የበላይነቱን ቢዝይና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለየ መንገድ ሰላምን አስጠብቄያለሁ ቢል ከምዕራባውያኑ ሊመጣ የሚችለውን ጫና መቀልበስ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አቅም እንደሌለውና የሰላም ሥጋት አለመሆኑን ለማሳየት፣ በተለያዩ አካባቢዎች መንግሥት ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እየሆነ ያለው ጫና በተቃራኒው ስለመሆኑና በይበልጥ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወደ መሀል መቅረቡን፣ እንዲያውም አንዳንዶቹ በሚዲያ እንዳሉት ‹‹አዲስ አበባን እንደ ታቦት በመዞር›› በቅርብ ርቀት ላይ ብዙ ኃይል አከማችቶ ሊደፈር የማይችል መሆኑ በተለየ ሁኔታ እየታየ ነው ብለዋል፡፡

ይህ ማለት ደግሞ በቀጣይ ወደ ድርድር ሲገባ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ኃይልን የመደራደር አቅም ከበፊቱ በላይ እንዲሆን በማድረግ የሥጋት መጠኑን ይጨምራል እንጂ፣ መንግሥት እንደሚለው አሳንሶ ማየቱ ትክክለኛ ዕሳቤ አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

የደኅንነትና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ለሚ ስሜ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል በቅርቡ በዛንዚባር በተደረገው ንግግር ችግሩን ለመፍታት በድጋሚ ለመገናኘት መስማማታቸው መልካም ቢሆንም፣ ሁለቱም ያስቀመጡዋቸው መሥፈርቶች ከበድ ከበድ ያሉ ስለመሆናቸው አውስተዋል፡፡ ለአብነትም ክልል አቀፍ የሽግግር መንግሥት እፈልጋለሁ የሚል ሐሳብ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በኩል መነሳቱን፣ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ ይህንን መቀበል እንደማይፈልግ በንፅፅር አቅርበዋል፡፡

መንግሥት ይህን ጥያቄ ለመቀበል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አሁን ባለበት ሁኔታ ለመንግሥት በጣም አሥጊ ደረጃ ላይ ባለመድረሱ፣ መንግሥት ጥያቄውን ለመቀበል ከባድ እንደሚሆንበት ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አቅሙ ጠንክሮ የመንግሥት ቁመና አሥጊ ደረጃ ላይ ደርሶ መንግሥት የመሆኑ ጉዳይ የማይቀር ቢሆን ኖሮ፣ ሥልጣን ተከፋፍሎ የሽግግር መንግሥት እንመሥርት ሊባል ይቻል እንደነበር የሚናገሩት አቶ ለሚ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣሁት በምርጫ ነው፣ የፀጥታ ተቋማትን በበላይነት የመቆጣጠርና የመምራት ኃላፊነት የእኔ ነው የማለት መብት አለው፡፡ በዚህ የተነሳ መንግሥት በደርድሩ ለክልል አቀፍ የሽግግር መንግሥት ዝግጁ አይደለሁም ሲል፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በኩል ደግሞ መንግሥት ይህን ካልፈቀደ ምንም ዓይነት ንግግር ጥቅም የለውም የሚል አዝማሚያ ስለመኖሩ አስረድተዋል፡፡

 በሌላ በኩል የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ትጥቅ ፈትቶ ካምፕ ውስጥ በመግባት በትክክለኛው የፀጥታ ሪፎርም አማካይነት በማለፍ ወደ አገሪቱ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲገባ ቢፈለግም፣ መሣሪያ በመፍታት ወደ ድርድር አንገባም የሚል ፍላጎት እንዳለ አውስተዋል፡፡  

እነዚህ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተፈጻሚ የመሆን ዕድላቸው በጣም ጠባብ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ለሚ፣ በዛንዚባር በነበረው ንግግር መንግሥት ግን ኦነግ ሸኔ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደገና ከልሶና ፈትሾ እንዲመጣ ተነጋግረው መለያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ንግግር የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተወካዮችን መንግሥት አቅማችሁ ትንሽ ነው በሚል ግፊት አድርጎባቸው የነበረ በመሆኑ የታጣቂ ቡድኑ አቅሙ ትንሽ አለመሆኑንና ለቀጣይ ጊዜ የመደራደር አቅሙን ከፍ ለማድረግ፣ በንግግሩ ማግሥት በተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች ተኩስ በመክፈት ለመንግሥት አቅሙን እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ለሚ እንደሚሉት በተለያዩ አካባቢዎች በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ስም የመንግሥትን ደካማ መዋቅር በመጠቀም መሣሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ የግጭት እንቅስቃሴ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ላይገናኝ እንደሚችልና ለወደፊት በሁለቱ አካላት መካካል ድርድር ተደርጎ ሰላም ቢመጣም ሊቆም የማይችል መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህ አልፎ አልፎ የሚታይ ግጭት ሊፈታ የሚችለው በመንግሥት ጥንካሬና የፀጥታ ሁኔታውን በማጠናከር ብቻ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የሚታዩት ግጭቶች ሁሉ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን የመደራደር አቅም የሚጨምሩ በመሆናቸው፣ ከሰሞኑ የተፈጸሙትን ሁሉ የራሱ ቢያደርጋቸው ኖሮ በመግለጫ ያስታውቅ ነበር ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች መወጣጠሩን የገለጹት የደኅንነትና የፖለቲካ ተንታኙ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚታየው የፀጥታ ችግር የመከላከያ ሠራዊት ብዙ ቦታዎች ሥምሪት በማድረጉና ራሱ የመንግሥት መዋቅር ጤነኛ ባለመሆኑ፣ ካኮረፉ የታጣቁ ኃይሎች ጋር ራሳቸውን ያመሳሰሉ አካላት በመኖራቸው በቅርቡ በቢሾፍቱም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የታዩት ጥቃቶች፣ በግልጽ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አማካይነት የተፈጸሙ ላይሆኑ እንደሚችሉ አውስተዋል፡፡

በሽግግር ውስጥ እንዲህ ዓይነት አደረጃጀቶች መብዛት የተለመደ ስለመሆኑ  አቶ ለሚ ገልጸዋል፡፡ ከሰሞኑ በቢሾፍቱም ሆነ በበቆጂ ወይም በወለንጪቲ የተፈጸሙ ጥቃቶች ለኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አንድ የአቅም ማሳያ ይሆኑ እንደነበር ጠቅሰው፣  ተፈጠረ የተባለውን ራሱ ፈጽሞት ቢሆን ኖሮ ኃላፊነቱን ይወስድ ነበር ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ ይህ ግጭትም ሆነ ጥቃት ቢቀጥል ለቀጣዩ ንግግር እንቅፋት ላይሆን ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -