- ሃሎ፡፡
- እንዴት አሉ ክቡር ሚኒስትር።
- ደህና ነኝ። አንተስ? አስተዳደሩስ?
- ሕጋዊ ሰውነታችን ተነጥቆ እንዴት ማስተዳደር እንችላለን ክቡር ሚኒስትር?
- ለዚህ ጉዳይ እንደደወልክ ገምቻለሁ።
- ደብዳቤም እኮ ልከናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አዎ። ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውኛል። አንድ ግን ያስገረመኝ አለ።
- ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለቦርዱ ጥያቄ ያቀረባችሁት መቼ ነው?
- ግንቦት 4 ነው።
- ቦርዱ ደግሞ በማግስቱ ቅዳሜ ግንቦት 5 ውሳኔውን ይፋ አደረገ አይለም?
- ልክ ነው።
- ያው ግንቦት 6 ቀን ደግሞ እሑድ መሆኑ ይታወቃል።
- አዎ።
- ታዲያ የቦርዱ ውሳኔ ዘግይቶ ግንቦት 7 ነው የደረሰን እንዴት ይባላል? ወይስ ምጸት መሆኑ ነው?
- የምን ምጸት ክቡር ሚኒስትር?
- በዕለቱ አጠናቀቁት ማለታችሁ ይሆን?
- ምኑን ነው የሚያጠናቅቁት?
- ግንቦት 7 የጀመሩትን!
- እሱን ደብዳቤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አይደለም።
- እና የማን ነው?
- የፓርቲያችን ነው።
- ነው እንዴ?
- አዎ። አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ መግባት እችላለሁ ክቡር ሚኒስትር?
- ለዚህ ጉዳይ አልነበር እንዴ የደወልከው?
- ቢሆንም የግንቦት ወር ቀናቶች ጉዳዬ አይደሉም።
- በል እሺ ወደ ጉዳይህ ግባ።
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ጉዳይ መፈታት አለበት። እርስዎም ጣልቃ መግባት ያለብዎት ይመስለኛል።
- እኔማ እንዴት ጣልቃ እገባለሁ?
- ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ካልተስተካከለ በሰላም ስምምነቱ ላይ ተፅዕኖ ያመጣል። ስለዚህ ጣልቃ ገብተው መፍትሔ ሊሰጡት ይገባል።
- በሕግ መሠረት የሚሠራ ገለልተኛ ተቋም እኮ ነው? እንዴት ብዬ ጣልቃ እገባለሁ?
- የሕግ መኖርና በሕግ መሥራት ያስፈለገበት መሠረታዊ ዓላማ ሰላም ለማስፈን እንጂ ሰላምን ለመጻረር አይደለም። ይህንን እንደሚገነዘቡ እረዳለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- ቢሆንም ይህ ጉዳይ በሕግ መሠረት መፍትሔ ማግኘት የሚችል ቀላል ጉዳይ እንጂ እናንተ እንደምትሉት ዓይነት ክብደት የለውም።
- ከባድ ነው እንጂ ክቡር ሚኒስትር። የሳለም ስምምነቱን የፈረመው ፓርቲ ህልውና ጠፍቶ እንዴት ወደፊት መራመድ እንችላለን?
- እኔ እንደተረዳሁት ፓርቲው ህልውናው ሙሉ በሙሉ ሊያጣ የሚችል አይመስልኝም።
- እርስዎ ጣልቃ ካልገቡ በቀር እንዴት ይሆናል?
- በሕጉ መሠረት እንደ አዲስ ምዝገባ ማድረግ ይቻላል።
- ይህንን እንደሚሉ እርግጠኛ ነበርኩ።
- እንዴት?
- መጥፎ ህልም አባኖኝ ነው ወደ እርስዎ ለመደወል የወሰንኩት።
- ህልም?
- አዎ። እንደ አዲስ ምዝገባ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበን የተሰጠንን ምላሽ ሰምቼ ነው የባነንኩት።
- ምላሹ ምን ነበር?
- ለምዝገባ ያቀረባችሁት ስም በሌላ ፓርቲ ተይዟል የሚል ነበር።
- የእናንተ ፓርቲ ስም ተይዞ?
- አዎ!
- ማነው የያዘው?
- ወራሾች ነን የሚሉ ናቸው።
- አይ አንተ፡፡
- እንዴት?
- ህልም አይደለማ ያባነነህ?
- ታዲያ ምንድነው?
- ትዝታ ነው፡፡
- የምን ትዝታ?
- የቅንጅት!
- Advertisment -
- Advertisment -