Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትምህርት ቤቶችን በር አንኳኩተው የገቡ አዋኪ ድርጊቶች

የትምህርት ቤቶችን በር አንኳኩተው የገቡ አዋኪ ድርጊቶች

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ስለትምህርት ተፅዕኖ ፈጣሪነት ብዙ ሰዎች የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል እ.ኤ.አ. ከ1896 እስከ 1980 የኖረው ስዊዘርላንዳዊው ሳይኮሎጂስትና ፈላስፋ ዤን ፔያኔት፣ ‹‹ትምህርት ማለት ምን ያህል ሸምድደን በአዕምሯችን ይዘነዋል፡፡ አሊያም ምን ያህል የመጻሕፍቱን ክፍሎች አንብበናል ሳይሆን፣ የምናውቀውንና የማናውቀውን ምን ያህል መለየት ችለናል የሚለውን መመለስ መቻል ነው፤›› ይላል፡፡

‹‹የትምህርት ዋናው ተግባር አንድ ሰው አትኩሮና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንዲችል ማድረግ ነው፣ የተማረ አቅምንና ምሉዕ ምግባር መፍጠር የትክክለኛ ትምህርት ግብ ነው፤›› ሲልም ግሪካዊው ፈላስፋ ፕሌቶ ጽፎ አልፏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እነዚህና ሌሎች የዓለም ፈላስፋዎች ስለትምህርት አስፈላጊነትና ገጽታ ቀያሪነት በየመዘመናቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ዘመናዊ ትምህርት በ1900 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒልክ እንደተጀመረና ይህም መደበኛ ትምህርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ እንደ አንድ ዓብይ ክስተት የሚቆጠር ድርጊት እንደሆነ ይነገራል፡፡

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃም ከዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዘው እንደ ባቡር፣ ሆስፒታል፣ ባንክ፣ መኪናና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለደረሰችበት ጥሩም መጥፎም ተብለው ለሚነሱ ጉዳዮች ትምህርትና የትምህርት ፖሊሲዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች መሆን አለባቸው የሚሉ አይጠፉም፡፡

በአንድ በኩል የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በዋናነት በሥነ ምግባር፣ በመልካም ዕሴትና በብቃት የታነፁ ዜጎች ለማፍራት በሚያስችል መንገድ ተቀርፆ፣ የኢትዮጵያን ዕድገትና አንድነት በሚያስቀጥል መልኩ ለአገር በቀል ዕውቀቶች ተገቢውን ትኩረት የሰጠ መሆኑን የትምህርት ፖሊሲው ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል የትምህርትና የሥልጠና ሥርዓቱ በንድፈ ሐሳብ እንጂ በተግባር፣ በክህሎትና በፈጠራ ላይ ያላተኮረ፣ የምዘና ሥርዓቱም ዕውቀትን ብቻ የሚመዝን ነው፣ በዚህም ኅብረተሰቡ በትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ የጥራና ተገቢነት ጥያቄ ሲያነሳበት የቆየበት ሁኔታ እንደነበረ፣ እንዲሁም ከትምህርት ሥልጠናው ዕውቀትና ክህሎት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ፣ ትውልዱን የምስክር ወረቀትና የዲፕሎማ አምላኪ እንዲሆን አድርጎታል የሚሉ አካላቶች ይገኙበታል፡፡

ሥርዓተ ትምህርቱ አገር ፍቅር፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴትን እንዲሁም የግብረ ገብነትን እሴቶች በዕውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት በተጨባጭ ማስረፅ ባለመቻሉ፣ ግለኝነት እያየለ ብሔርተኝነት እየገነነ የአገር ፍቅር እየደበዘዘ በመምጣቱ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮባት እንደቆየ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡

እነዚህንና ሌሎች በትምህርቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርሳሉ ተብለው የተጠቀሱትን ችግሮች መፍታት ያስችላል የተባለ አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትምህርት ሚኒስቴር 2013 ዓ.ም. ማውጣቱና በሥራ ላይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በፀደቀው ፍኖተ ካርታ እንደተገለጸው፣ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ 80 በመቶ አፈጻጸም እንዲኖራቸው እንደ ደረጃ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚህ ስኬት ደግሞ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በሙሉ ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል ተብሎ ነበር፡፡

ከዚህ ባሻገር ተማሪዎች በጥሩ ሥነ ምግባር ታንፀው ያድጉ ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ቢገለጽም፣ የተማሪዎች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆልና ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ፍላጎትና አመለካከት እየቀነሰ መምጣት በብዛት እየተስተዋለ እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ የዳሰሳ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በተለይ ደግሞ ለታዳጊ ተማሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በትምህርት ቤት አቅራቢያ የሚፈለፈሉት አዋኪ ድርጊቶች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው መደረክ ተነግሯል፡፡

ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው ከትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚከፈቱ ቪዲዮ ቤቶች፣ መጠጥና ጭፈራ ቤቶች፣ የሐሺሽና የትምባሆ መሳቢያ ቤቶችና በአጠላቃይ ተማሪዎች ትህርታቸውን በጥሞና እንዳይከታተሉና ወደአላስፈላጊ ጉዳዮች እንዲሳቡ የሚወተውቱ አዋኪ ድርጊቶች በእጅጉ እየተስፋፉና እየተንሠራፉ እንደመጡ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተበጀላቸው የተማሪዎች ሥነ ምግባር በአሥጊ ሁኔታ ላይ እንደሆነ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ተናግሯል፡፡

ከጉዳዩ አሳሳቢነት በመነሳት ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣንና ባለድርሻ አካላት በትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኙ አዋኪ ድርጊቶችን በተመለከተ ውይይት አድርገው ነበር፡፡

በውይይቱ በትምህርት ቤቶች አካባቢ 200 ሜትር ሳይርቁ የትምህርት ቤትን አጥር ተደግፈው የሚሠሩ ንግድ ቤቶች በእጅጉ እንደተስፋፉ ተነስቷል፡፡

ከራቁት ጭፈራ ቤት እስከ አደንዛዥ ዕፆች ለተማሪዎች                                                                                በገፍ እየቀረቡ እንደሆነና በርካታ ተማሪዎችም በተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች ተዘፍቀው እንደሚገኙ ተነግሯል፡                                                                                                    

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሚገኙ የመግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች ለትውልድ በማያስቡና የራሳቸው ጥቅም ብቻ በሚታያቸው ግለሰቦች በሚከፈቱ አዋኪ ድርጊቶች ተከበዋል፣ አፋጣኝ መፍትሔ ከሚመለከተው ሁሉ ይሻሉ ሲሉም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እነዚህን እኩይ ተግባራት በሚፈጽሙ አካላት ላይ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እየወሰደ ያለውን ሰሞነኛ ዕርምጃ አስታውሰው፣ ዕርምጃው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ በነበረው ውይይትም አዋኪ ድርጊቶች የተባሉ በትምህርት ቤት ዙሪያ ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ፣ በተማሪዎች ቦርሳ ተጠቅልለው፣ የትምህርት ቤት ቅጥር ግቢን አንኳኩተው መግባታቸው ተነግሯል፡፡

በጉዳዩ ላይ በተደረገ ዳሰሳ ተማሪዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ተወያዮች ተናግረዋል፡፡ በዚህም መፀዳጃ ቤቶች የሲጋራ ማጨሻ የትምህርት ቤት እርሻዎች የሐሽሽ መብቀያ ቦታዎች ሆነው እንደተገኙ ተነግሯል፡፡

በቅሎ የተገኘው ተክል ማን እንደዘራው ባይታወቅም፣ መዘራትና መብቀሉን ግን የትምህርት ቤቱ ርዕሳነ መምህራንም ሆኑ መምህራን እንደማያውቁ ነው የተነገረው፡፡

ከእነዚህ ግኝቶችና ተጨባጭ ማስረጃዎች በመነሳት ችግሩ ሥር እየሰደደና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን፣ የሚመለከተው ሁሉ በአንክሮት ሊከታተለው እንደሚገባም ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ መምህራን ማኅበር የመጡ ተሳታፊ አሳስበዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንቅፋት ከሆኑት ምክንያቶች መካከል አዋኪ ድርጊቱን በሚፈጽሙም ሆነ ድርጊቱ እንዲፈጸም በሚያደርጉ ሰዎች ላይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ተመጣጣኝና አስተማሪ አለመሆናቸው እንደሆነ ተወስቷል፡፡

በትምህርት ቤት ዙሪያ እስከ ሁለት መቶ ሜትር ባለው ርቀት ፊልም ወይም ማንኛውንም ቪዲዮ ማሳየት ሁለት ሺሕ ብር ቅጣት የሚያስከትል ሲሆን፣ የቀንም ሆነ የማታ ጭፈራ ማከናወን እንዲሁም ማንኛውንም የአልኮል መጠጥ መሸጥ እስከ 10 ሺሕ ብር የሚያስቀጣ እንደሆነ የተነገረ ተነግሯል፡፡ በተጠቃሚው ላይ ግን ከምክር አገልግሎት የዘለለ ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንደማይወሰድበት ነው የተነገረው፡፡

እነዚህና ሌሎች ዕርምጃ የሚወሰድባቸው ሒደቶች አስተማሪና ቆንጣጭ ባለመሆናቸው፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎች ሊታረሙ አልቻሉም ሲሉም አንድ ተሳታፊ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ያለው የቅጣት አዋጅ መስተካከል ያለበት ቢሆንም፣ በአዋጁ መሠረትም የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ላለፉት ዘጠኝ ወራት ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው በተከፈቱ 2,662 ተቋማት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቋል፡፡

በተለይ ደግሞ በቅርቡ የተጀመሩ ዕርምጃዎች እንዳሉና ዕርምጃዎቹ ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...