Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ከጥቅም ያልዋሉት የቱሪስት መስህቦቹ 13ቱ ወራት

የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ የተለያዩ መድረኮችን አዘጋጅተዋል፡፡ በ1987 ዓ.ም. በያሬድ ሙዚቃ ቤት በባህላዊ ዳንኪራ (ካልቸራል ፎክ ዳንስ) በመሠልጠን እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ንቁ ተሳትፎ በማድረግም ይታወቃሉ፡፡ ‹ፌስ ኦፍ ኢትዮጵያ› የተባለ የባህል ቡድን በማቋቋም የኢትዮጵያን ባህል ለቱሪስቶች ለማስተዋወቅ ሠርተዋል፡፡ በሙዚቃና በሥዕል ሥራዎች በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ባህል ለውጭና ለአገር ውስጥ ቱሪስቶች በማስተዋወቅ ከቀድሞው የአዲስ አበባ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ  ዕውቅናና ሽልማትን አግኝተዋል፡፡ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን የሚያዘጋጁት (ኦርጋናይዘር) አቶ ደረጀ በለጠ የኢትዮጵያን ባህልና ቱሪዝም፣ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሙዚየሞችንና ሀብቶችን ጠብቆ ለከፍተኛ የገቢ ምንጭነት መጠቀም አለብን ይላሉ፡፡ ሥራቸውን አስመልክቶ አበበ ፍቅር አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፌስ ኦፍ ኢትዮጵያን ለመመሥረት ምን ነበር ያነሳሳችሁ?

አቶ ደረጀ፡- የቀድሞው የአዲስ አበባ ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ በ1987 ዓ.ም. በአማተር ደረጃ ተቋቁማችሁ ሥሩ ሲል፣ እኔም የራሴን የባህል ቡድን አቋቁሜ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከሮያል ኔዘርላንድስ ኤምባሲ 49 ሺሕ ደች ፍራንክ ሽልማት አግኝቼ በጀመርኩት እንቅስቃሴ በጣም ውጤታማ ነበርኩ፡፡ አሁን ላለሁበት ደረጃም ገንዘቡ መሠረት ሆኖኛል፡፡ በወቅቱ ቱሪስቶችና ኤምባሲዎች የመስቀል በዓልን ጨምሮ ሌሎች በዓላትን ለማክበር ሲመጡ የኢትዮጵያን ባህል፣ የበዓሉን ሥነ ሥርዓት የሚያስተዋውቁ በቂ ነገሮች አልነበሩም፡፡ ደመራው ይደመራል ያበቃል፡፡ ከእነዚህና መሰል ክፍተቶች በመነሳት እኔም ፌስ ኦፍ ኢትዮጵያን በማቋቋም የውጭ እንግዶች ሲመጡ ለምንድነው ቡና ጠጡ ተብለው የማይጠሩት? ቡና ጠጡ ተብለው ቢመጡ ለእነሱም ለእኛም የኢትዮጵያን ባህልና ወገናችንን ለማስተዋወቅ ይረዳናል በሚል የሩሲያ ባህል ተቋም  (ፑሽኪን) አዳራሽን ጠይቄ ተሳካ፡፡ ከሽሮሜዳ የባህል አልባሳትን በማዘጋጀት እንኳን ለኢትዮጵያ የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት የበገና ድርደራ በማድረግ ሁሉንም ኤምባሲዎች ጠርቼ አስተዋውቄያለሁ፡፡ በፕሮግራሙ በጭራሽ ያልጠበቅኳቸውና ያልጠራኋቸው ሰዎች ታድመው ነበር፡፡ አዳራሹ በሙሉ በዲፕሎማቶች ተሞልቶ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው ባህላችንን በቅጡ ብናስተዋውቅ ምን ያህል ተጠቃሚ ልንሆን እንችል እንደነበር ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንደዚህ የሆነው ከምን የተነሳ ነበር?

አቶ ደረጀ– በወቅቱ በነበረን ዝግጅት በዲፕሎማቶችና በቱሪስቶች መጨናነቆችን ለእኔ ያስተላለፈልኝ መልዕክት ሰዎች የሚዝናኑበት ማጣታቸውን፣ በተለይ ቱሪስቶች ሆኑ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ባህል ለማወቅ የሚጓጉ መሆናቸውን ሆኖም ዕድሉን አላገኙም የሚል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንዳነሱት የጠቀሷቸው ችግሮች የነበሩት በ1990ዎቹ ገደማ ነበር፡፡ አሁን ላይስ የኢትዮጵያን ባህል ለማስተዋወቅ የሚሠሩ ሥራዎችንን እንዴ ያዩዋቸዋል?

አቶ ደረጀ፡- በአሁኑ ወቅት ትንሽ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየመጡ ነው፡፡ የከተማዋ ገጽታም እየተቀየረ ነው፡፡ መንገዶቿም ከቆሻሻ እየፀዱ ይመስላል፡፡ አንድ ቱሪስት በእግሩ ወክ ሲያደርግ እያስነጠሰው መሄድ የለበትም፡፡ ይህ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ መሻሻል እየታየበት ነው፡፡ ሆኖም ዓመቱን ሙሉ ቱሪስትን መሳብ የምንችልበት አቅም ቢኖርም አልሠራንበትም፡፡

ሪፖርተር፡- የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር እንደ ባለሙያ ባህል ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝምን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ምን መሥራት አለባቸው ይላሉ?

አቶ ደረጀ፡- የባህል ምግብ ቤቶች፣ የባህል ጭፈራ ቤቶችና ሌሎች ባህል ባህል የሚሸቱ ትርዒቶች ቢደረጉ የቱሪስት ፍሰቱ ይጨምራል፡፡ በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ውጭ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ወደ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሄድ ያሉትን ጥሩና ሳቢ ባህላዊ እሴቶች  በተገቢው ሁኔታ ሲመለከቱ ጓደኞቻቸውን በመሳብ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡ እዚህ ላይ ቢሠራ መልካም ነው፡፡ እኛ ካልሠራንና ወደ ተግባር ካልገባን ማንም ሊሠራልን አይችልም፡፡

እኔ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የባህል ልብሴን ለብሼ ስታይ ከየት ነህ የሚለው ጥያቄ ይበዛል፡፡ እኔ አገሬ በአፍሪካም ሆነ በዓለም በቱሪዝም በደንብ ትታወቃለች የሚል ነገር የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ናት ነው የሚባለው፡፡ አንድ አፍሪካዊ ስለ አፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ በቅኝ ግዛት ስላልተገዛች አገር የማያውቅ ከሆነ ኢትዮጵያ አትታወቅም ማለት ነው፡፡ ቱሪዝሙና ባህሉ በደንብ ከተሠራ የአገራችንን መለያ ይዘን መንቀሳቀስ እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ 13 ወራት ደስ የሚል ፀሐይ አላት፡፡ ዝናብ ከዘነበ በኋላ ሞቅ ያለና ተስማሚ ሙቀትን የምትሰጠን ምድር ናት፡፡ ይህንን ሁኔታ በውጭ አገር ከተመለከትን ተፈጥሮ አመጣጥኖ አልሰጣቸውም፡፡ ለበሽታ የሚያጋልጥ በረዶአማ ቅዝቃዜ አልያም ሐሩር ነው ያለው፡፡ በኢትዮጵያ በ13 ወር ውስጥ ምን አለ? ካልን መሬታችን በመስከረም ከሚሰጠው አደይ አበባው ጀምሮ በርካታ ልንሠራባቸው የሚገቡ የቱሪስት መስህቦች አሉ፡፡ ከሽሮሜዳ በላይ ሆነው ከእንጦጦ ተራራ ወደ ታች ማየት ራሱ የገቢ ምንጭ መሆን ይችላል፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ ያሉት አዕዋፋት መንፈስን ያድሳሉ፡፡ ከከተማ ወጣ በምንልበት ወቅት ዘመናዊ ቤቶች ባይበዙ ባይ ነኝ፣ ባህላቸውን ሳይለቁ ቱሪስትን በሚስቡ መንገድ ቤቶች ቢሠሩ የተሻለ ነው፡፡ ባህልን ለማሳደግ ከመንግሥት ብቻ ድጋፍ መጠየቅ አይገባም፡፡ ሕዝቡ በራሱ የሚሠራውን እያንዳንዱን ነገር ባህልና ወጉን በጠበቀ መልኩ ለቱሪስት ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጥ በሰፊ ቢሠራበት ዘርፉ ለግለሰብና ለድርጅት ገቢ ከማገኘት ባሻገር የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ማሳደግና ለአገርም ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት የሚያስችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቱሪስቶች በተለይ ደግሞ ወደ ገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ለመጎብኘት ሲሄዱ በአብዛኛው ገንዘብ ስጡን የሚል ውትወታ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ምናልባት ከችግር ባሻገር ከግንዛቤ እጥረትም የሚመነጭ ነው፡፡ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያሉ የዘርፉ ኃላፊዎች ምን መሥራት አለባቸው ይላሉ?

አቶ ደረጀ፡- ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ቢሮ መዋቅር ድረስ በቱሪዝምና  በባህል ዙሪያ ትስስር በመፍጠር እየተናበቡ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የሆቴል፣ የባህል ምሽቶች፣ የአርት ጋለሪዎችና ጥንታዊ ሙዚየሞች ለዕይታ ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ ብሔራዊ ሙዚየም ያሉ ሁሉ 24 ሰዓት ለጎብኝዎች ክፍት መሆን ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን ከገመገምኩት አንፃር ሙዚየሞች በራቸውን ዘግተው ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን እዚያ ውስጥ ያለውን ቅርስ ለማስተዋወቅ ባለሙያ በመመደብና በሚዲያም ጭምር በማስተዋወቅ በደንብ ሊሠራበት ይገባል፡፡ ማንኛውም ሰው በቱሪዝም ዙሪያ ሥራ ልሥራ ብሎ ሲነሳ፣ መንግሥት ያለምንም ገደብ ያለምንም መሥፈርት ከጀርባው ሌላ ወንጀሎች እስከሌሉበት ድረስ፣ በደንብ እንዲሠራ ዘርፉን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ለምሳሌ እኔ በቱሪዝም ዙሪያ ሐሳቤን ልስጥ ብዬ ስነሳ ሐሳብህን አልፈልግም ተወው ማለት የለበትም፡፡ ምናልባት ከብዙ ሐሳቤ ውስጥ ትንሿ ነገር ተመዛ ጠቃሚ ልትሆን ትችላለች፡፡ ስለዚህ በቱሪዝምና በባህል ዙሪያ በብቃት መሠራትና መተዋወቅ ይኖርበታል፡፡  

ሪፖርተር፡- የአደባባይ በዓላትና ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ክብረ በዓሎች በሚከበሩበት ወቅት ፖለቲካዊ ይዘት እንዳይኖራቸውና በዓሉን ኅብረተሰቡ በሚፈልገው መንገድ ያከብር ዘንድ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ደረጀ፡- በዓላት የገቢ ማስገኛ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የዓድዋ በዓል ከባህልነቱ ባሻገር ትልቅ የገቢ ማስገኛ ነው፡፡ ዓድዋ የአያት የቅድመ አያቶቻችን ጣፋጭ ድል ነው፡፡ ኃላፊነት ተሰምቶህ ያለ ምንም መሸራረፍ ለትውልድ የምታስተላልፈው ውድ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቅርስ ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም መስህብ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሊያስጠብቀውና ሊያስረክበው ይገባል እንጂ የራሱን ሐሳብን ብቻ ይዞ መምጣት የለበትም፡፡ ነገር ግን በዓል ላክብር ብሎ ወደ አደባባይ ከሚወጣው ሕዝብ መካከል ሥርዓት አልበኛውን ማስወጣት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት የበዓሉ ባለቤት ለሆነው ለሕዝቡ ሙሉ ኃላፊነትን መስጠት ይኖርበታል፡፡ ራሱ መንግሥት ደግሞ ያለ ምንም ፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ትክክለኛ ባህሉና የበዓሉ አከባበር ይንፀባረቅ ዘንድ ከኅብረተሰቡ ጋር በመግባባትና በመናበብ ሊሠራ ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እዚህም እዚያም የጦርነት ድምፆች በየአካባቢው ይሰማሉ፡፡ የውጭ አገር ጎብኝዎች ይቅርና የአገር ውስጥ ጎብኝዎችም በሚፈልጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመጎብኘት አዳጋች በሆነበት ወቅት ስለ ቱሪዝም ዕድገት እንዴት ማውራት ይቻላል?

አቶ ደረጀ፡- አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ላሊበላ ላይ አንድ አስጎብኝ አለ እንበል፡፡ ስለ ላሊበላ እረኛው ራሱ ነው የሚያስጎበኘው፡፡ ከዚያም ዳግም ሙያተኞች ወደ ውስጥ አሉ ወደ ትግራይ ስትሄድም ስለ አክሱም ሐውልት መረጃ የሚሰጡ አሉ፡፡ ይህ ማለት ቱሪስቱን በጨዋ ደንብ እየጠራ የሚያስጎበኘው ባለቤቱ ሕዝቡ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ባህላቸውን የቱሪስት መስህባቸውን ለማሳየት በመጀመርያ ኃላፊነት አለባቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቱሪስት ፍሰቱን ለማስቀጠል ሰላም መኖር አለበት፡፡ በመጀመርያ መንግሥት በመቀጠል የቱሪስት መዳረሻ ያለባቸው ሁሉም ክልሎች እዚያ አካባቢ ሽፍታና ዘራፊ እንዳይኖር በማንኛውም መንገድ የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ መስከረም የሚል የግጥም መድበል አዘጋጅተው ለአንባቢያን ሊያቀርቡ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ የግጥም መድበሉ በምን ጉዳዮች ያተኮረ ነው?

አቶ ደረጀ፡- የግጥም መድበሉ እስከ ዛሬ ድረስ ተሠርቷል ከሚባሉ የመጻሕፍት አዘገጃጀት ለየት ያለ ነው፡፡ ርዕሱ ‹‹የኢትዮጵያ መስከረም›› ነው፡፡ የኢትዮጵያ መስከረም እንደምናውቀው ደስ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በሚያምር መስከረም የሚጀመር አዲስ ዓመት ወይም ሥራ እስከሚቀጥለው መስከረም ድረስ ስኬታማ በመሆን ፍሬው ጣፍጦ ስለሚበላ ነው የኢትዮጵያ መስከረም ያልኩት፡፡ ውስጡ ያሉትን ግጥሞች ማንኛውም ሰው ሊያዜማቸው የሚችሉና ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ ናቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...