የጤና ሚኒስቴር ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ የአምስት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ከፍተኛ የአገልግሎት ፍላጎት ባለባቸው የጤና አገልግሎቶች ዙሪያ የስፔሻሊቲ ሥልጠናን ለማጠናከር የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ በ22 የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የስፔሻሊቲ ሥልጠና በስፔንና ጣሊያን ትብብር እየተሰጠ መሆኑን ያስታወሱት የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ በአውሮፓ ኅብረት የተደረገው የአምስት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በተለይ የዘጠኝ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካትና ጤናማ፣ የበለፀገና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሠለጠነ የሰው ሀብት ቁልፍ መሆኑን የጠቀሱት ሊያ (ዶ/ር)፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በጦርነት ወቅት ዕገዛ እንዳላቋረጡና በመልሶ ማቋቋሙ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውሰው፣ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በተናጠል ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ኅብረቱም የሚደግፍ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በይፋዊ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መድረኩ የአውሮፓ ኅብረት፣ የጣሊያን፣ የስፔን፣ የቤልጂየም፣ የፖርቱጋል፣ የቼክና የማልታ አምባሳደሮችና የአየርላንድ፣ የስዊድንና የፈረንሳይ ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች የተወከሉ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡