ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት በእንግሊዝ አርፎ ሥርዓተ ቀብሩ በዚያው የተፈጸመው የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ፣ ልዑል ዓለማየሁ አፅምን እንግሊዝ እንደማትመልስ አስታወቀች፡፡
በባኪንግሃም ቤተ መንግሥት በዊንድሶር ካስል ውስጥ በንጉሣውያን መካነ መቃብር የተቀበረውን የልዑል ዓለማየሁ አፅምን ወደ ኢትዮጵያ አፍልሶ ለማምጣት በኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ነበር፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የኢትዮጵያዊውን ልዑል ዓለማየሁ አፅም እንዲመለስ የቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበል የገለጸው የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ነው፡፡
ከአፄ ቴዎድሮስ ትውልድ ሐረጉ የሚመዘዘው ፋሲል ሚናስ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት፣ ‹‹አፅሙ እንደ ቤተሰብና እንደ ኢትዮጵያውያን እንዲመለስ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የተወለደባት አገር እሷ ስለሆነች፤›› ብሏል፡፡ ‹‹በእንግሊዝ መቀበሩ ትክክል አልነበረም›› ሲልም አክሏል፡፡
ነገር ግን የባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ አፅሙን ከተቀበረበት ማውጣት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ጸሎት የተቀበሩትን ሌሎችን ሊጎዳ እንደሚችል አመልክቷል፡፡
‹‹በአካባቢው ያረፉት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሳይረብሽ አፅሙን ቆፍሮ ማውጣት የሚቻልበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፤›› ብሏል፡፡
የቤተ መንግሥቱ መግለጫ በተጨማሪም የዊንድሶር ሕገ ቀኖና መሠረት፣ ‹‹የሟቹን ልዑል ክብር የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው›› ብሏል፡፡
‹‹ስለዚህ ጥያቄውን ለማስተናገድ እንደማይቻል ስንገልጽ በሐዘኔታ ነው፤›› ብሏል፡፡
ዳግማዊ ቴዎድሮስና ልዑል ዓለማየሁ
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ በዋናነት የሚያስጠቅሳቸው ለዘጠኝ አሠርታት ግድም የቆየውን ዘመነ መሣፍንትን እንዲያበቃ ያደረጉና የአሃዳዊ መንግሥት መሥራችነታቸው ነው፡፡
ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም. (በአንዳንድ ጽሑፎች 1810 ዓ.ም. ይላሉ) የተወለዱት ዳግማዊ ቴዎድሮስ ከየካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። በትውልድ ስማቸው ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ሲባሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ እንዲሁም መይሳው ካሳ ይባሉ ነበር፡፡
በታሪክ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ አስተያየት የአፄ ቴዎድሮስ ሕይወት በሦስት ቦታዎች ይጠቃለላል፡፡ ቋራ፣ ጋፋትና መቅደላ። የመጀመሪያው የፖለቲካና ወታደራዊ መሠረትን ሲወክል፣ ሁለተኛው የዘመናዊነትን ፍላጎት ይወክላል፣ ሦስተኛው ደግሞ መጠለያንና የሞት ቦታን ይወክላል። አጠቃላዩ የቴዎድሮስ ውጤት ቅይጥ ነው፡፡
በወርኃ ሚያዝያ 1860 ዓ.ም. ታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ የተሰዉበት ዕለት፣ «ሽጉጣቸውን አጉርሰው ራሳቸው የጎረሱበት ክስተት፡፡ የዘመኑን ትንሣዔ በዓል አክብረው በማግሥቱ የማዕዶት ዕለት ያረፉበት ነው፡፡»
የመጨረሻው የመቅደላ ግብግብ ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ወደ ማቆሙ ተቃረበ፡፡ በጄኔራል ናፒር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ በየአቅጣጫው መሯሯጥ ጀመረ፡፡ ግርማ ኪዳኔ እንዳተቱት፣ የቴዎድሮስን ሁኔታ አስመልክቶ የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተር እስታንሊ ሲናገር ሰኞ ከቀኑ አሥር ሰዓት አካባቢ እንግሊዝ በመቅደላ ላይ ካሰማራቻቸው ወታደሮች መካከል ሁለት የአየርላንድ ወታደሮች የተኩስ ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተክለፈለፉ እንደደረሱ፣ አንድ ያልታወቀ ኢትዮጵያዊ ከመሬት ላይ ተዘርሮ ለመሞት በማጣጣር ላይ እንዳለ ያገኙታል፡፡
‹‹እነሱ ወዲያው አላወቁትም እንጂ ግለሰቡ ተራ አይደለም፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ ዳግማዊ ናቸው፡፡ አፄ ቴዎድሮስን በሕይወት ሳሉ የሚያውቃቸው ራሳም መጥቶ እሳቸው ስለመሆናቸው እንዲያረጋግጥ ተደረገ፡፡ እየሮጠ መጥቶ ሲያያቸው አፄው ሆነው አገኛቸው፡፡ በእሱና በንጉሡ መካከል አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርም፣ ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ሁኔታውን እንደተመለከተ መንፈሱ ተረበሸ፡፡››
«ጥይት ስለውኃ ማነው የሚጠጣ?
ቴዎድሮስ ብቻ ነው ጥሙን የሚወጣ፤» እንዲል፡፡
የእንግሊዝ ሠራዊት አገሪቱን ለቅቆ የወጣው በመቅደላ ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ባሠሩት ‹‹ብሔራዊ ሙዚየም›› ውስጥ የተከማቹትን ውድ ቅርሶችን በመዝረፍ ነበር፡፡ ከቅርሶቹም ሌላ የአፄውን ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅንና ልጃቸውን ልዑል ዓለማየሁን ይዘው ተጉዘዋል፡፡ በጉዞ ላይ ሳሉ እቴጌ ጥሩወርቅ ድንገት በማረፋቸው፣ በመቐለ ደቡባዊ ምሥራቅ በምትገኘው ጨለቖት ሥላሴ ተቀብረዋል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ አንድሪው ሄቨንስ የተባለ ጸሐፊ በቅርቡ ባሳተመው ‹‹ዘ ፕሪንስ ኤንድ ዘ ፕላንደር›› በተሰኘ መጽሐፉ፣ እንግሊዛውያን ልዑሉንና እናቱን የወሰዷቸው በመቅደላ ዙሪያ የነበሩ የአፄ ቴዎድሮስ ጠላቶች ይዘው ይገድሏቸዋል ብለው በመሥጋታቸው ለደኅንነታቸው ሲሉ ነው ይላል።
ሄቨንስ በዚሁ መጽሐፉ ልዑል አለማየሁ ብሪታንያ ከደረሰ በኋላ ቤት ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ ውጪ ወጥቶ መጫወትን ይመርጥ እንደነበር፣ ለፈረስና ለፈረስ ግልቢያ ልዩ ፍቅር እንደነበረው አሥፍሯል።
ልዑል ዓለማየሁ በ18 ዓመቱ ከመተንፈሻ አካሉ ጋር በተያያዘ ሕመም ኅዳር 4 ቀን 1872 ሕይወቱ ማለፉን፣ ዜና ዕረፍቱን ተከትሎም ንግሥት ቪክቶሪያ ሐዘናቸውን መግለጻቸው የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
‹‹ዛሬ ጠዋት መልካም የሆነው ዓለማየሁ ሕይወቱ ማለፉን ስሰማ ከባድ ሐዘንና ድንጋጤ ተሰምቶኛል። በባዕድ አገር ብቻውን፣ አንድም ዘመድ ይሁን የቅርብ ሰው ሳያይ ደስተኛ ሕይወት አልነበረውም። ሁሉም ዓይነት ፈተና ተጋርጦበት ነበር…፣ ሰዎች ትክ ብለው ሲመለከቱት በቆዳ ቀለሙ ይመስለው ነበር። …ሁሉም በጣም አዝኗል።››
የልዑል ዓለማየሁ አያት ደብዳቤ
ልዑል ዓለማየሁ ከመሞቱ ከስምንት ዓመት በፊት የእቴጌዪቱ እናት፣ የዓለማየሁ አያት ወ/ሮ ሳቃየ በስደት የነበረው የልጅ ልጃቸው ናፍቆት ቢበረታባቸው ከ151 ዓመታት በፊት ጥር 4 ቀን 1864 ዓ.ም. ደብዳቤ ጻፉለት፡፡ በብሪታንያ ግምጃ ቤት የሚገኘው ደብዳቤ ይዘት እንደወረደ እነሆ፣
ይህ፡ ቃል፡ ይድረስ፡ ከደጃዝማች፡ ዓለማየሁ፡፡
የተላከ፡ ከወይዘሮ፡ ሳቃየ፡ ከቴየ፡ ጥሩነሽ፡ እናት፡ እኔም፡ ያለሁ፡ ከእናትህ፡ አገር፡ ከደጃዝማች፡ ውቤ፡ ደብር፡ ነው፡፡ ልጄ፡ ወዳጄ፡ እጅጉን፡ እንዴት፡ አለህ፡ ከተለያየን፡ ጀምሮ፡ እስከ፡ ዛሬ፡ ድረስ፡ ምነው፡ ወረቀት፡ አትሰድልኝ፡ በኃዘን፡ በልቅሶ፡ ስሞት፡ አላንተ፡ በቀር፡ ሌላ፡ ልጅ፡ ሌላ፡ ተስፋ፡ የለኝም፡፡ አሁንም፡ ተሎ፡ ወረቀት፡ ስደድልኝ፡ መልክህን በሥዕል፡ አድርገህ፡ ዘወትር፡ እንዳየው፡፡ ክርስቶስ፡ ለመገናኘት፡ ያብቃን፡ አሜን፡፡
ከንግሊዚቱ፡ ንግሥት፡ ከመስኮብ፡ ንጉሥ፡ ከፈረንሳዊ፡ ንጉሥ፡ ነገሥታቱ፡ ሁሉ፡ ወዳጅ፡ ሁን፡ ወረቀት፡ ላክ፡ ሀበሻ፡ ሰው፡ ሁሉ፡ አንተን፡ ይጠብቃል፡ ይመኛል፡ ብልህ፡ ሁን፡ የሀበሻ፡ ሰው፡ ዓይን፡ አውጣበት፡ ዕውር፡ ሁኗል፡ ጥበብ፡ አውጣለት፡ እንዲህ፡ ዕውር፡ እንደሆነ፡ አይቀር፡፡
በዘመነ ዮሐንስ በጥር በ፬ ቀን ተጻፈ፡፡
ቅንብር በሔኖክ ያሬድ