Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የማፍረስ አባዜ ቢበቃስ!

ሰላም! ሰላም! ውድ ወገኖቼ እንደምን ሰነበታችሁ? ዘንድሮ በወጉ ካልተጠያየቅን የክራሞታችን ነገር እያስፈራ ነው፡፡ በቀደም ዕለት አንድ ወዳጄ ከቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) እኩለ ሌሊት ላይ ይደውልልኛል፡፡ እኔ ደግሞ ምን ዓይነት ሥራ ተገኝቶ ነው በዚህ ደረቅ ሌሊት የሚደውልልኝ ብዬ ሰፍ ብዬ ስልኬን ሳነሳ፣ ድምፁ እየተርበተበተ የሚናገረውን መስማት ተሳነኝ፡፡ በለቅሶና በሳግ መሀል ያለ እርብትብት የሚል ድምፅ ታውቃላችሁ? ወዳጄ ምን ሆኖ ነው ብዬ፣ ‹‹ወንድሜ ምን ሆነህ ነው? ምን ጉድ ገጥሞህ ነው?›› እያልኩ በጥያቄ ሳጣድፈው፣ ‹‹አንበርብር አለቅን፣ ምን እንደሆኑ የማይታወቁ ታጣቂዎች ይኼው ላያችን ላይ ተኩስ እያዘነቡ ነው…›› ሲለኝ እውነትም የተኩስ እሩምታ ይሰማል፡፡ እንዴ የጀግናው አየር ኃይላችን መቀመጫ በሆነችው ደብረ ዘይት በዚህ ውድቅት ምን መዓት መጣ ብዬ ስጮህ ስልኩ ጥርቅም ብሎ ተዘጋ፡፡ ብለው ብሠራው ስልኩ አይነሳም፡፡ እንዳይነጋ የለም ግማሽ ሌሊት ሙሉ ቁጭ ብዬ አድሬ ሰማዩ ወገግ ሲል ስልኩን ስሞክር ተነሳ፡፡ ለካስ ታጣቂዎች በፖሊስ ጣቢያ ላይ ተኩስ ከፍተው በሥራ ላይ የነበሩ የፖሊስ ባልደረቦችን ፈጅተዋል፡፡ ነፍስ ይማር ብያለሁ፡፡ ይታያችሁ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ፣ ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ይህ ሁሉ ጉድ የተፈጸመው፡፡ ጎበዝ ለመሆኑ ደህና ናችሁ? እኔ ግን በእጀጉ ፈርቻለሁ!

በአንድ ወቅት ነው አሉ ‹ዕንቁላል ቀስ በቀስ ቦምብ ይሆናል› ማለት ወግ ሆኖ ነበር። ዕድገታችን የማያመጣብን ጉድ የማይለዋውጥብን አባባል የለም። አሁን እስኪ አንድ ዕንቁላል በስንት ተገዝቶ፣ ስንቴ ተቀቅሎ፣ ስንቴ ተጠብሶ ተበልቶ ነው ወደ ቦምብነት ያደገው የሚለው ጥያቄ የእኔ ብቻ ሳይሆን የመሰሎቼ ጭምር ነው። በጥያቄ ላይ ጥያቄ ስንከምር በትውልድ ላይ ትውልድ ይደረብና ይኼው ነገሩ ሁሉ የመከራ ቋት ይሆናል። እውነቴን እኮ ነው። በቀደም ከእንቅልፌ ስነቃ ስልኬ እንደ ብራቅ ጮኸች። የፈረደበት የቴሌ ሎተሪ ‹ጅንጀና› ነው ብዬ እያዛጋሁ ሳየው ከአንድ ወዳጅ የተላከ ጥቆማ ነው። በዚህ ዘመን ወዳጅ አያሳጣ ማለት ቀላል ምርቃት አይደለም። ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ መሬት አስተዳደር፣ ወዘተ. ስትሄዱ ቢያንስ በቅጡ መረጃ የሚሰጥ ስለሌለ ወዳጅ ያስፈልጋል፡፡ ስልኬ ጮሆ ነበር፣ ከዚያስ አትሉም? ‹በማታ እያሽከረከሩ ዕንቁላል ከተወረወረብዎ መኪናዎን እንዳያቆሙ፣ ዝናብ መጥረጊያ እንዳይጠቀሙ› ይላል መልዕክቱ። ይብላኝ መኪና ደረሰኝ አልደረሰኝ እያለ ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ባንክ እየዞረ አካውንት ለሚከፍተው እያልኩ ነፍሴ መለስ አለች። ‹‹እንኳን መኪና ባጃጅም ሲደላ እኮ ነው…›› ስለው ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹መጀመርያ መንገድ ሲኖር እኮ ነው…›› አለኝ። ነገረኛ እኮ ነው!

‹‹ተው እንጂ የምታማው ብታጣ ይኼን መንግሥት በመንገድ ታማለህ?›› አልኩት። መንገድና መሬት ያለ ነገር ሌላ ሥራ የላቸውም ያስብላል እኮ የእኛ አገር ነገር። ‹‹አለ ብለህ ነው? ይኼው ገጭ እጓ ስንል አይደል እንዴ የምንውለው። ተሠርቶ ተሞቷል አቦ…›› ብሎ ተነጫነጨብኝ። ንጭንጩ አጓጉል ሲሆንብኝ ጠረጠርኩ። የባሻዬ ልጅም ሰሞኑን ብስጭት በብስጭት ሆኗል። ምክንያቱን ስጠይቀው ሊነግረኝ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ጎትጉቼ ሳናግረው ደግሞ፣ ‹‹አንተ ሰውዬ እዚህ አገር ውስጥ እየኖርክና ይኼ ሁሉ ጉድ እየተሰማ ትንሽ እንኳን አይሰማህም?›› ሲለኝ እደነግጣለሁ፡፡ ‹አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን መርዶ ይረዳል› እንደሚባለው አጥብቄ ስይዘው፣ ‹‹ወገኖቻችን ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬና ጎጆ ተባረው እንደ ጉድፍ ሲጣሉ አልሰማሁም ለማለት ነው…›› እያለ ሲበሳጭ ጉዳዩ ይገባኛል፡፡ አንጀታችን እያረረ ነገን ተስፋ ባናደርግ ኖሮ የዘንድሮ ነገር ወይ ያስመንናል፣ ወይም አንደኛውን ከዚህ ሁሉ ጉድ በገዛ እጃችሁ ተገላገሉ ያሰኛል፡፡ ግና አምላክ በፈጠራት ነፍስ ማንም መወሰን ስለማይችል ይህ ድርጊት ተገቢ አይደለም፡፡ አሁንማ ከባለሥልጣናት አንስቶ እስከ ባለሀብት ተብዬዎች ድረስ ሰብዓዊነት ከጠፋ ሰነበተ። ጭካኔ ከፍቶ ሰብዓዊነት ሲነጥፍ ያስፈራል!

አንዳንዴ ነገረ ሥራችን ሁሉ ጨዋታ ብቻ ይሆን የለ? ዶላርን አይመለከትም ይኼ። በሩቅ እንደምንሰማው የቢል ጋጋታ ቀልባችንን አስጨንቆ የሚይዝበት ቀን እስኪመጣ፣ ቶሎ ቶሎ መጨዋወቱ ልባም መሆን ይመስለኛል ለማለት ነው። አደራ ደግሞ እንዲህ ስላችሁ ሥራውን ትታችሁ የዶላር ምንዛሪን የሚያስቀንስ ወሬ ወዳድ ስትሰበስቡ እንዳትውሉ። ሆ…ሆ… ዘንድሮ ሰው አላውቅ ያለው ‘ኔትወርክ’ የሚስተካከልበትን ቀን ብቻ ሳይሆን፣ ነገር የሚመጣበትን ቀዳዳ እኮ ነው። እንዲያው እኮ፡፡ በልቶ ብቻ ማደር እየከፋብን ስለሄደ ይኼን ያህል እጅ መስጠት የለብንማ። ታዲያስ ለአንዳንዱ ሰው እኮ ጨዋታም ምግብ ነው። እናም አዛውንቱ ባሻዬ ፈገግ ብለው ይሰሙኛል፣ እኔ ደግሞ አወራለሁ። በነገራችን ላይ የጨዋታን ነገር ያመጣሁት ለቀልድ ብዬ አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን አጉል ቀልዶች በዝተው እጅ እጅ እያሉ ስለሆነ፣ ለቀላጆችና ለቧልተኞች ቦታውን ለቀን እኛ እንደ ስሜታችን ለዘብ አድርገን እናውራው፡፡ ይሻለናል!

‹‹በአሁኑ ጊዜ እየተወለዱ ላሉ ሕፃናት ልጆች የሚወጡ ስሞች ምን እንደሆኑ ሰምተዋል?›› ስላቸው ስላቅ መሆኑ አስቀድሞ ገብቷቸው (እንኳን ይችን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን ዓይነት አስተያየት እያዩኝ)፣ ‹‹በል እስኪ ንገረኝ?›› ይሉኛል። ‹‹አሳረኛው ኑሮ፣ ውኃ ናፍቆቴ፣ መብራቴ ጠፋ፣ ሰላምን ያያችሁ፣ የሴረኛው ደባ…›› ስላቸው አቋርጠውኝ የሚጠጡት ቡና ትን እስኪላቸው ከአንጀታቸው ሳቁ። ‹‹ለመሆኑ የቱ ነው ለሴት የቱ ነው ለወንድ የወጣው?›› ቢሉኝ፣ ‹‹ተባዕትና እንስት ሰዋሰው አልተቀላቀለም እንዴ? ልማቱም ፆታ፣ መልክ፣ ቀለም ሳይለይ እንደ ጳጉሜን ካፊያ ለሁሉ እየተዳረሰ ነው…›› አልኳቸው። እንዲህ ስንጫወት ቆይተን፣ ‹‹የእኛ ሰው ተንኮሉ ቃላት ማዋደድ ላይ ተገድቦ ቢቀር ምንኛ ሸጋ ነበር?›› ብለው በሐሳብ ተመሰጡ። ባሻዬ እንዲያ ሲሉ የዴሞክራሲው አየር እንደ ልብ መንፈስ የጀመረ ቀን ከሐሳብ ልዩነትና ከቃላት ምልልስ አልፈን፣ የምንሻገረውን ድልድይ በሐሳባቸው እያፈረሱት ያሉ ይመስላሉ። ደግሞስ ቢዘገይ እንጂ ይቀራል ብላችሁ ነው? ተስፋ እናድርጋ!

እናላችሁ እንደ ወሬው ሁሉ የከተማውን አጭበርባሪዎች (ባለሥልጣናትም ሆኑ ባለሀብቶች እንዳሉበት ልብ ይሏል) በአቋራጭ ለመክበር፣ በመዋከብና በመጨናነቅ ታጅለው ሲቅበዘበዙ ስታዘብ አዕምሮዬ ፈጥኖ የሚያስበው ብዙ ነው። ላባቸውን ጠብ አድርገው ሠርተው ካለፈላቸው ውስን ባለሀብቶቻችን ውጪ የሌሎች ነገር ባይነሳ ይመረጣል፡፡ ቀንና ሌሊት አገር ለመዝረፍ ሲሉ በዓይናቸው እንቅልፍ ዝር የማይል፣ ግብር ከማጭበርበርና ከመሰወር ጀምሮ በሐሰተኛ ደረሰኝ የሚዘርፉ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በገፍ ደብቀው ሰው ሠራሽ እጥረት የሚፈጥሩ፣ ጥራት በሌላቸው ማቴሪያሎች ሕንፃዎችንና መንገዶችን የሚገነቡ፣ ትምህርት ቤቶችን እያደኑ የሱሳ ሱስ መደብሮችን በመክፈት ታዳጊዎችን በአጭር የሚያስቀሩ፣ ሳምንቱን ሙሉ ከዘመናዊ ልኳንዳ ቤት ሳይጠፉ ዳቢትና ሽንጥ እየዘለዘሉ በጦርነትና በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ዞር ብለው የማያዩ፣ የተራቡ ሕፃናት ዓይኖቻቸው እያዩ ያስተረፉትን ምግብ የሚደፉ፣ ወዘተ ሰው መሳይ በሸንጎዎችን ሳስብ ያቅለሸልሸኛል፡፡ ‹‹ያካበቱትን የኃጢያት ሀብት ጥለውት ወደ መቃብር አንዲት ከፈን ብቻ ይዘው መሄዳቸውን ዘንግተው፣ አንድም ቀን ፈጣሪን የሚያስደስት ሥራ ሳይሠሩ ድንገት በልብ ድካም ወይም በስትሮክ ማሸለባቸውን ከዘነጉ ከንቱዎች ድሮስ ምን ይጠበቃል?›› ሲለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ መልሴ ‹‹ምንም!›› ነበር፡፡ በቃ ይኸው ነው! 

አሉላችሁ ደግሞ የተሰጣቸውን ሕዝባዊ አደራ ዘንግተው እንዳይሆኑ ሆነው የሚያልፉ ሹም ተብዬዎች፡፡ ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› የሚባለው የድሮ ከንቱ አባባል በሚገባ እየሠራ ያለው በአሁኑ ጊዜ ነው ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም፡፡ በቀደም ከአንዱ ደንበኛዬ ጋር አንዱ ስም አይጠሬ ክፍለ ከተማ እንሄዳለን፡፡ ሒደቱ ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፈው የመሬት ካርታ የማግኘት ጉዳይ ነው እዚያ የወሰደን፡፡ እሱ እንደነገረኝ ጉቦ ከፍሎ ቢሆን ኖሮ አይደለም ስድስት ወራት ስድስት ቀናት አይፈጅም ነበር፡፡ ‹‹አቶ አንበርብር አርበኛው አያቴ ከመሞቱ በፊት ቃል አስገብቶኛል፡፡ ‹አገርህን አትበድል፣ ስትቸገር ድረስላት፣ ሕይወትህንም ሰዋላት፣ ምን አደረገችልኝ ብለህ አትጠይቅ፣ ለሹም ታዘዝ እንጂ አታሸርግድ፣ ጉቦ የሚባለውን ፀያፍ ነገር አትስጥም አትቀበልም፣ ለትውልዱ መልካም አርዓያ ሁን እንጂ ሞራል አላሻቂ እንዳትሆን ተጠንቀቅ፣ ሰዎችን ያለ ምንም ልዩነት አክብር፣ ለእንስሳትና ለዕፅዋት እንክብካቤ አድርግ፣ በአጠቃላይ ፈጣሪ የሚወዳቸውን መልካም ነገሮች ማከናወን ከቻልክ አንተ እውነትም ሰው ነህ› ነበር ያለኝ፡፡ ስለዚህ ጉቦ ሰጥቼ ክቡር የሆነውን ሰውነቴን አላረክሰውም ብዬ ነው የምንገላታው…›› ሲለኝ ዕንባዬ ሳላውቀው ዝርግፍ አለ፡፡ ለካ ታላላቅ ሰዎች አጥተን ነው አይረቤ የሆንነው!

ምሁሩን የባሻዬ ልጅ አግኝቼ የገጠመኝን ነገር በመገረም ስነግረው፣ ‹‹ከበፊት ጀምሮ በርካታ ታላላቅ ሰዎች እንደነበሩን ከበርካታዎቹ ንባቦቼ አውቃለሁ፡፡ ለገንዘብና ለዝና ሳይሆን፣ ለአገራቸው ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ብቻ ሳይሆን፣ ልጆቻቸውን ጭምር በዚህ መልካም መንገድ ለመቅረፅ የለፉ ብዙ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የዓድዋ ዘመቻ ሲጠራ እስከ ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው የዘመቱ ጀግኖች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ አስበው እንግዲህ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ያሳተፉም በጣም ብዙ ነበሩ፡፡ አገራቸውን ከራሳቸው ሕይወት በላይ ያከበሩ ጀግኖቻችንን ሳስብ፣ በዚህ ዘመንም እነሱን መሰሎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ችግሩ ሌባውና ወንበዴው የመገናኛ ዘዴውን ተቆጣጥሮት ነው እያደር እያነስን ያለነው…›› ብሎኛል። እሱ እኮ እንዴት አድርጎ ታሪክን እንደሚያጣቅሰው ነው የሚደንቃችሁ። ‹‹ታሪክን በወጉ ተረድቶ በአግባቡ መተረክ ያቃተው፣ የራሱን የሚያኮራ ታሪክ መሥራት ያዳገተው፣ ከራሱና ከቢጤዎቹ ጥቅም ውጪ የአገር ጉዳይ የማይገደው እየበዛ ሲሄድ ነው ተስፋችን ጭጋግ የሚወርሰው…›› የሚሉኝ አባቱ ባሻዬ ናቸው፡፡ እንዲያ ነው እንግዲህ!

ሰሞኑን ከወጉ ጎን ለጎን ትንሽ ሠርቼ የሸቀልኳትን ባንኬ በሞባይል ስልኬ ሲያሳውቀኝ፣ መጀመርያ እንደማደርገው ለሽሮ፣ ለበርበሬና ለአጠቃላይ የወር አስቤዛ ልቆርጥ ማንጠግቦሽ ዘንድ ብቅ አልኩ። በእንዲህ ያለው ቀን እኔና ማንጠግቦሽ እንኳን ሃያ ዓመት አብረን የኖርን ሃያ ደቂቃ የምንተዋወቅ አንመስልም። የዋጋ ግሽበቱ ናላችንን አዙሮት በአስቤዛ ወጪ ፍልስጤምና እስራኤል ሆነን ነው ቁጭ የምንለው። ታዲያ አሁንም ‹‹እንዴት ዋልሽ?›› ብዬ ቤቴ ዘው ስል፣ ለምን በዚያ ሰዓት እንደሄድኩባት ገብቷት አፍንጫዋን በመንፋት የመጀመርያውን ያለ መግባባት ሮኬት ተኮሰች። እንደ ወትሮው የአስቤዛ ገንዘብ ያሳንሰኛል ብላ ነው ብዬ ከጭቅጭቅ ለመዳን ጨመር አርጌ ብሰጣትም ፊቷ አልተፈታም። ‹‹ምን ሆነሻል?›› ማለት ኮስተር ብዬ። ‹‹የኑሮ ወድነቱ ብሶበታል፣ የአስቤዛ ወጪም በእጥፍ መጨመር አለበት…›› አለች ከሃያ ዓመታት በላይ በሁለት ሰው ወርኃዊ የሆድ ወጪ ስትጨቃጨቅ የኖረች ባለቤቴ። ‹‹ይኼ እንዴት ዛሬ ትዝ አለሽ? እንደ አገር መሆን ነዋ…›› ስላት መድከሜን በግልጽ እያሳየሁ፣ ‹‹ውድ አቶ አንበርብር ምስኪን ወላጆችንና ልጆችን ከምግባችን የማካፈል የፈጣሪ ትዕዛዝ እንዳለብን አትርሳ…›› ብላኝ ፍርጥም ስትል ደነገጥኩ፡፡ ስለራሳችን ብቻ እያሰብን የኖርነውን ዕድሜ በተዘዋዋሪ ስታስታውሰኝ ደግሞ ጭራሽ አንጎሌን በጥብጣው አረፈችው። እሷን የመሰለች አስተዋይ ሚስት የሰጠኝን አምላኬን አመሠገንኩ፡፡ መጪው የአገር ተስፋ ዋናው መሠረቱ የዛሬ መልካም ሥራና ትጋት መሆኑም ሲታወሰኝ፣ ለውዷ ባለቤቴ አስፈላጊውን ገንዘብ ሰጥቼ በምሥጋና ጉንጮቿን ሳምኳቸው። ርኅራኄና ሰብዓዊነት ቤቴ ድረስ ከተፍ ሲሉልኝ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡ ጭካኔ የበዛው ርኅራኄና ሰብዓዊነት ጠፍተው ነው እላለሁ፡፡ መገንባት አቅቶ ማፍረስ የሚበዛው ሰብዓዊነት ሲጠፋ ነው፡፡ ከማፍረስ መገንባት ላይ ቢተኮር እንዲህ አንጨካከንም ነበር፡፡ የማፍረስ አባዜ ይብቃ! መልካም ሰንበት!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት