Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹በተበታተነ መልኩ የተከበረው›› የዓለም ሙዚየም ቀን በአዲስ አበባ

‹‹በተበታተነ መልኩ የተከበረው›› የዓለም ሙዚየም ቀን በአዲስ አበባ

ቀን:

‹‹የሙዚየም ቀን በተበታተነ መልኩ በመከበሩ በመጀመሪያ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ማኅበሩ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ዘርፉን ከመደገፍ አንፃር የዛሬውን ቀን ጨምሮ እያደረጋችሁ ላለው እንቅስቃሴ እናመሰግናለን።››

ይህን ኃይለ ቃል፣ የዓለም ሙዚየም ቀን በኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር አማካይነት ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም.  ሲከበር  ያስተጋቡት የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ናቸው።

ግንቦት 10  (ሜይ 18) ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን ሆኖ በየዓመቱ እንዲከበር ዓለማቀፉ የሙዚየም ምክር ቤት በደነገገው መሠረት ዘንድሮ በየአገሮቹ የተከበረው ‹‹ሙዚየሞች ለዘላቂነትና ለተሻለ ሕይወት››  (Museums, Sustainability and Wellbeing) በሚል መሪ ቃል ነው።

ክብረ ቀኑ በየዓመቱ በሚዘጋጀው መሪ ቃል መሠረት በየአገሮቹ ብሔራዊ ሙዚየሞች አማካይነት  ይከበራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ- “ቢፒአር” ሰበብ ህልውናው ከስሞ በቅርስ ባለሥልጣን ሥር ወደ መምሪያ (ዳይሬክቶሬት) ደረጃ ከወረደበት ከ2004 ወዲህ ክብረ ቀኑ ከዓመት ወደ ዓመት ትኩረት ሲነፈገው ቆይቷል። 

በዓሉን ማክበር በጀመረችበት ዘመን ስታከብር የነበረው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በሚባለው ተቋሟ አማካይነት ነበር፡፡ በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ቅጥጥባ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በ2003 ዓ.ም. በተተገበረው በቢፒአሩ አደረጃጀት መሠረት ባለሥልጣኑ በተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች ሲዋቀር በዋና ሥራ አስኪያጅ ይመራ የነበረው ሙዚየሙ የባለሥልጣኑ አንድ ዳይሬክቶሬት ሆኖ ተደራጅቷል፡፡ ስሙም ከብሔራዊ ሙዚየምነት ወደ ‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት›› ተለውጧል፡፡ ኃላፊውም በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሥር ሆኖ ዳይሬክተር ተብሏል፡፡

ይህ አዲሱ ስያሜ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮና ከሙዚየሞች ወካይነት አኳያ ብዙም የማያስኬድ ስያሜ በመሆኑ በየጊዜው በመድረኩ ትችትና ተቃውሞ እየተሰነዘረበት መጥቷል፡፡

ነባሩ ሙዚየም በአሁን አጠራሩ ‹‹… ዳይሬክቶሬት›› ስለ ሰው ዘር አመጣጥና ሌሎችም የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል የሚያንፀባርቁ እነ ሉሲ፣ ሰላም፣ አርዲ፣ ወዘተ ቅርሶች የሚጎበኝበት ቢሆንም፣ ብሔራዊ ሙዚየም የሚለውን ዕውቅና የማጣቱ ጉዳይ የበርካቶች መጋገሪያ ከመሆን አላመለጠም፡፡

በየዓመቱ ግንቦት 10 ቀን (ሜይ 18) የሚከበረውን የዓለም ሙዚየም ቀን ኢትዮጵያ ስታከብር፣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሔራዊ ሙዚየም ስያሜ ጉዳይ ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ለምን? ተብሎ ሲጠየቅም ‹‹እየተጠና ነው›› የሚል ምላሽም ሲሰማበት ኖሯል፡፡ ዘንድሮም ጥያቄው ጥያቄን እየወለደ ቀጥሏል፡፡

እንዲያውም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሚለው መጠርያ ሳይኖራትና የሙዚየምነት ዕውቅና ሳትሰጥ የሙዚየም ቀንን በየዓመቱ ማክበሯን ተቃርኖ (ፓራዶክስ) ነው የሚሉም አልታጡም፡፡

በተለይ የዓለም ሙዚየም ቀን በሚታሰብበት ዕለት ጎልቶ ይሰማል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ቀኑን  ባለሥልጣኑ እንደወትሮው ሲያከብረው ባይታይም፣ ቀኑን ግን በዚያው ዓመት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢባቱጋማ) ከአዲስ አበባ ሙዚየም ጋር በመተባበር ማክበሩ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮም ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር ጋር በመሆን ሲያከብር ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም›› ዳግም ዕውን እንዲሆንም ጥሪውን ለሦስተኛ ጊዜ አቅርቧል፡፡

‹‹ዘንድሮም የሙዚየም ቀንን ስናከብር በድጋሚ ሳናቀርብ የማናልፈው ጥያቄ የረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ከታላቅ ክብር እንዳትጎድል አዋጁ የፈረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ዳግም በአዋጅ ተቋቁሞ፣ ኢትዮጵያ እንደሌላው ዓለም ሁሉ ብሔራዊ ሙዚየም የሚባል ሕግ እሚያውቀው ተቋም እንዲኖራት በድጋሚ እንጠይቃለን፡፡››

‹‹የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን›› ይባል የነበረውና በቅርቡ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የተሰኘው ተቋሙ፣ ዘንድሮ ቀኑን ‹‹ሙዚየሞች ለዘላቂነትና  ሁለንተናዊ  ደኅንነት›› በሚል መሪ ቃል ባልደረቦቹና ታዳሚዎች በተገኙበት ግንቦት 10 ቀን  2015 ዓ.ም. በውይይት፣ በሙዚየም ጉብኝትና  በዓውደ ርዕይ  ማክበሩን ገልጿል፡፡ በክብረ ቀኑ ዲስኩር ያሰሙት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው፣‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በአዋጅ ባይቋቋምም ሁኔታዎች ሲመቻቹ በአዋጅ እንዲቋቋም ጥረቶች ይደረጋሉ፤›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን›› ሙዚየምን መተካት ይችላልን?

ከዓለም አቀፉ የሙዚየም ድርጅት (አይኮም) የሙዚየም ትርጓሜ በመነሳት ‹‹የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት›› ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹የሙዚየምና ተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ዳይሬክቶሬት›› በምን ስሌት ነው የሙዚየምን ጽንሰ ሐሳብና ተልዕኮ በምልዓት ሊተካ የሚችለው? የሚሉ ጠያቂዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

መንግሥት የኢትዮጵያ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን በ1992 ዓ.ም. ያቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 209/1992 ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የሚናገር ነው፡፡     በአዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 12 ድንጋጌ ሙዚየምን እንዲህ ተርጉሞታል፡፡ ‹‹ሙዚየም ማለት ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ያልሆነ ቅርሶችን የሚሰበስብ፣ የሚጠብቅና የሚጠግን፣ ለምርምርና ለጥናት፣ ለማስተማሪያና ለመዝናኛነት ስብስቦችን በሚገባ አዘጋጅቶ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡›› ለዚህ የሙዚየም ትርጓሜ መሠረት ነው ተብሎ የሚታሰበው በቀዳሚው የአይኮም ድንጋጌ ላይ የወጣው የሙዚየም ምንነት ነው፡፡

‹‹ሙዚየም ማለት ዓላማው በትርፍ ላይ ያልተመሠረተ ለማኅበረሰብ ዕድገት አገልግሎት የሚያበረክትና ለኅብረተሰቡ ክፍት የሆነ፣ ለጥናት፣ ለትምህርትና ለህሊናዊ ዕርካታ ሊውሉ በሚችሉበት ሁኔታ የሰው ልጅና የአካባቢውን ቁሳዊ መረጃዎች የሚያሰባስብ፣ የሚያከማችና የሚንከባከብ ምርምር የሚያካሂድ በኤግዚቢሽን ወይም አግባብነት ባለው መንገድ የሚያስተዋውቅ ተቋም ነው፡፡››

እ.ኤ.አ. በ1946 የተመሠረተው አይኮም የሙዚየም ትርጓሜን በየዓረፍተ ዘመኑ ማሻሻሉን አልተወም፡፡ በኦስትሪያ ቪየና ነሐሴ 18 ቀን 1999 ዓ.ም. ባደረገው 22ኛው ጠቅላላ ጉባዔው ነባሩን ድንጋጌ እንዲህ አድርጎ ዘርዘር በማድረግ አሻሽሎታል፡፡

‹‹ሙዚየም ማለት ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ለኅብረተሰብ አገልግሎትና ለልማቱ የተሰማራ፣ የሰው ልጆች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን (Tangible and Intangible Heritage)  የሚጠብቅ፣ የሚንከባከብ ምርምርና ጥናት የሚያደርግ፣ ለሕዝቡ ክፍት ሆኖ በዓውደ ርዕይ የሚጎበኝ ብሎም ለትምህርት፣ ለጥናትና ለተድላ ደስታ (ለመዝናኛ) የሚያውል ቋሚ ተቋም ነው፡፡››

አይኮም ያደረገውን የትርጉም ማሻሻያ ኢትዮጵያ አለመመልከቷ ወይም አለማሻሻሏ የሚያሳየው፣ በቀደመው ትርጉም ብቻ በመመሥረት ብሔራዊ ሙዚየምን የተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማትና ኤግዚቢሽን ዳይሬክቶሬት ብላ መሰየሟ ነው፡፡ ዳይሬክቶሬቱ የማይንቀሳቀሱ (የሚዳሰሱ) እንዲሁም የማይዳሰሱ ቅርሶችን  አይመለከትም ማለት ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የሙዚየም ድርጅት ከአሥራ ሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ የሙዚየምን ትርጉም ዳግም አሻሽሎታል፡፡  የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ በሐምሌ 2011 ዓ.ም. በፓሪስ ባደረገው 139ኛው ስብሰባው በደረሰበት ውሳኔ አዲሱን የሙዚየም ብያኔ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ሙዚየሞች ዲሞክራሲያዊ፣ ሁሉን አካታች ስላለፉት  ዘመናትም ሆነ ስለመጪው ዘመን የሚያወሱ፣ የሒሳዊ (ክሪቲካል) ውይይቶች መድረክ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ያሉትን ግጭቶችና ተግዳሮቶች በመገንዘብ በመፍትሔነት በማኅበረሰቡ ውስጥ እምነት የሚያሳድሩ የዕደ ጥበባት ውጤቶችንና ናሙናዎችን ይይዛሉ፡፡ ለመጪው ትውልድ ብዝኃ ትውስታዎችን በመጠበቅ ለሁሉም ሕዝብ ያለ ልዩነት በእኩል መብቶችና በእኩል ተደራሽነት ያስተናግዳሉ፡፡ ዋስትናም ይሰጣሉ፡፡

‹‹ሙዚየሞች በትርፍ ላይ ያልተመሠረቱ አሳታፊና ሥራቸው ግልፅ የሆነ ነው፡፡ እንዲሁም ለሰው ልጅ ክብርና ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ለዓለም አቀፍ እኩልነትና ለዓለም ደኅንነት ንቁ አስተዋጽዖ የሚያደርጉት ብዝኃነትን ባማከለ መልኩ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን ቅርስ የመሰብሰብ፣ የመጠበቅ፣ ጥናትና ምርምር የማድረግ፣ የመተርጐም፣ በዓውደ ርዕይ በማሳየት ነው፡፡

ይህ አዲሱ ማሻሻያ ከመውጣቱ ከአሥራ ሦስት ዓመታት በፊት የዓለም ሙዚየም ቀን በኢትዮጵያ «ሙዚየሞች ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት አጋዥ ኃይሎች» በሚል መሪ ቃል ሲከበር በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ፣ የሙዚየም ተልዕኮ መስፋት እንደሚገባው በኢትዮጵያውያን ምሁራን ተንፀባርቆ ነበር፡፡

በወቅቱ የታሪክና አርኪዮሎዢ ምሁሩ ካሳዬ በጋሻው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ሙዚየም ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ሥራው መሰብሰብ፣ መሰነድ፣ መጠበቅ፣ ጥናትና ምርምር በየዕለቱ ማከናወን ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሙዚየም ምን ሆኖ መገኘት ይገባዋል፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል የሚለው ተተኳሪ ነጥብን አንስተዋል፡፡

 ሙዚየሞች ምን ሆነው መገኘት አለባቸው? የሙዚየም ብያኔ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ይዳስሳል ወይ፣ ነባሩ ብያኔ ግማሽ ምዕት ዓመት አሳልፏል፡፡ አሁን የምንለውን መሸከም ይችላል ወይ? ሙዚየሞች የመገናኛ ቦታ፣ ሐሳብ መለዋወጫ ችግርን የመቅረፊያ መድረኮች ናቸው፡፡ ባላቸው ስብስብ በመገናኘትና ታሪክና ባህልን ብቻ በማሰባሰብ ሳይወሰኑ ሌሎች ዘርፎችን እንደ ማዕድን፣ ኢነርጂን ማካተትና ገንዘብን የማስገባት ለቱሪዝም ዕድገት የሚበጁ መሆናቸውን ማወቅ ይገባል ይላሉ ምሁሩ፡፡

ሙዚየም የአገሪቷን ችግር በኤችአይቪ፣ በሥነ አካባቢ፣ በፖለቲካ ቀውሶች ላይ የሚነጋገሩበት መድረክ መሆን እንደሚገባው የሌሎችን አገሮችን ተሞክሮ በምሳሌነት በማቅረብ ያብራራሉ፡፡

ለማኅበራዊ ለውጥ በምናስብበት ጊዜ ሕንፃውን፣ ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን የሚያንቀሳቅሰው ክፍልንም ጭምር ነው፡፡ በሁለተኛነት የሚያሳየው ሙዚየሙ ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም አለው ወይ፣ ራሱስ ሳይለወጥ ሌላውን መለወጥ ይችላል ወይ፣ ለለውጥስ ተዘጋጅተዋል ወይ፣  ይኸንን የሚሸከም ኅብረተሰብ አለ ወይ፣ መንግሥትስ ይህን ሐሳብ ይገነዘባል ወይ? እነዚህን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ምሁሩ በወቅቱ አጽንዖት ሰጥተውበት ነበር፡፡

በ2009 ዓ.ም. የዓለም ሙዚየም ቀን፣ ‹‹ያልተነገሩና አሻሚ ታሪኮች በሙዚየም›› (Museums and. contested histories: Saying the unspeakable in museums) በሚል መሪ ቃል ሲከበር ሙዚየምን በተመለከተ ያልተነገሩ ሐሳቦችን ወደ አደባባይ ማምጣት እንደመሆኑ በወቅቱ የነበሩ የውይይት ተሳታፊዎች ያለ ብሔራዊ ሙዚየም የሙዚየም ቀንን ማክበር ፋይዳ እንደሌለው ማመልከታቸው ይታወሳል፡፡

ከብሔራዊ ሙዚየምነት ወደ ተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ኤግዚቢሽንነት መለወጡን ያስተዋሉ አንድ ባለሙያ ድርጊቱን ‹‹ብሔራዊ ሙዚየምን ማንኳሰስ፣ ማንነትን ማንኳሰስ ነው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሙዚየም ባለሙያ ‹‹ብሔራዊ ሙዚየሟን ከመዋቅር የሠረዘች አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት›› በማለት ጎረቤት አገር ኬንያ ለአገራዊ ሙዚየም የሰጠችውን ቦታ በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡

በኬንያ የብሔራዊ ሙዚየሞችና ቅርስ ድንጋጌ (ሕግ) ራሱን ችሎ የቆመ ነው፡፡ የኬንያ ብሔራዊ ሙዚየሞች (The National Museums of Kenya-NMK) መንግሥታዊ ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ በኬንያ የሚገኙ ሙዚየሞች፣ መካነ ቅርሶችንና ሐውልቶችን ያስተዳድራል፡፡

በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዎሎጂና ቅርስ አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን ቡርቃ (ዶ/ር)፣ ባቀረቡት ጥናታቸው በቢፒአር ምክንያት  ህልውናውን ያጣው ሙዚየሙ፣ በራሱ የሚንቀሳቀስ ነፃ ተቋም መሆን እንደሚገባውም ይመክራሉ፡፡ ሙዚየሙ ያሉበት ጥያቄዎች በአፋጣኝ መልስ አግኝተው፣ በየአካባቢው ላሉ ሙዚየሞች ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም መሆን እንደሚያሻው ነው፡፡

እንደ ምሁራን አገላለጽ ሙዚየሞች የመገናኛ ቦታ፣ ሐሳብ መለዋወጫና ችግርን የመቅረፊያ መድረኮች ናቸው፡፡ ባላቸው ስብስብ በመገናኘትና ታሪክና ባህልን ብቻ በማሰባሰብ ሳይወሰኑ ሌሎች ዘርፎችን ማካተት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሙዚየም በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለምሳሌ በኤችአይቪ፣ በሥነ አካባቢ፣ በማኅበረ ፖለቲካ  ዙሪያ የሚነጋገሩበት መድረክም እንዲሆንም ይጠበቃል፡፡

ሙዚየም ኅብረተሰብን የማገናኘት በማኅበረሰቡ ውስጥም አንድነትና ግንኙነት ማድረግ ትልቁ ተግባሩ በመሆኑ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚኖረው ተቋም ተገቢ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ በአዲስ አቀራረብ፣ በአዲስ ርዕይና ሐሳብ መታጠቅ እንደሚገባውና ለዚህም ባለሙያዎች መነሳሳት ይገባቸዋል ሲሉም ያክላሉ፡፡

በአንድ ጥናታዊ ጽሑፋቸው አንጋፋው አርኪዮሎጂስት ብርሃኔ አስፋው (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ ሙዚየም እንደ ትምህርት ቤት የሚታይ የመረጃ ማዕከል ነው፡፡ ዋና ሥራው ቅርሶችንና ታሪካዊ እሴቶችን ጠብቆ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ዜጋን የሚቀርጽ፣ ባህልን የሚያስተምር፣ ታሪክን የሚያስረዳ ተቋም ነው፡፡ ከሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋሞች የተለየ የሚያደርገው ሙዚየም ጊዜን የጠበቀ መረጃ ማቀበል መቻሉ ነው፡፡

ብሔራዊ ሙዚየም ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ታሪክ፣ ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከኤትኖግራፊ (የሕዝብ ባህል) አንፃር ቁስ አካላዊና ቁሳዊ ያልሆኑ እሴቶችን በማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ከተመራማሪዎች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...