Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመጀመርያውን የአማርኛ ቴሌፕሪንተር የቅርስ ባለሥልጣን ተረከበ

የመጀመርያውን የአማርኛ ቴሌፕሪንተር የቅርስ ባለሥልጣን ተረከበ

ቀን:

በኢትዮጵያዊው መሐንዲስ ተረፈ  የራስወርቅ የተሠራውና በ1950ዎቹ ከጀርመኑ ሲመንስ ፓተንት ያገኘው የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን፣ ቤተሰቦቻቸው ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ  ቅርስ ባለሥልጣን አበረከቱ::

ተወዳጅ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንደገለጸው፣ ከዓመት በፊት ያረፉት ኢንጂነር ተረፈ የራስ ወርቅ፣ በ25 ዓመት ዕድሜያቸው በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን  የአማርኛ ቴሌፕሪንተር  የተሰኘ አዲስ ቴክኖሎጂ ለአገራቸው ያስተዋወቁና በራሳቸውም ጥረት ወደ ጀርመን አቅንተው ለአዲስ ግኝታቸው የአዕምሯዊ ንብረት ፓተንት ለማግኘት የቻሉ ነበሩ፡፡

ይህ ከስድስት አሠርታት በፊት የተሠራውን ታሪካዊ የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ቤተሰቦቻቸው ባሉበት ለቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ያስረከቡት ልጃቸው አቶ ኢዛና ተረፈ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢንጂነር ተረፈ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ ለ10 ዓመት፣ በዓለም አቀፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት በአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊነት ከ40 ዓመት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የነበረውን የአንኮበር ቤተ መንግሥት ሎጅንም የቀድሞ ይዞታውን ሳይለቅ ዳግም በማሠራት የአገር ቅርስ እንዲጠበቅ በማድረጋቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

‹‹ፊደላችን የራስ ወርቃችን›› የሚል ዕሳቤ የነበራቸው የመሐንዲስ ተረፈ የራስ ወርቅ ዜና ሕይወትን በኦዲዮም በቪዲዮም እስከ ኅትመት የሰነደው፣ በእዝራ እጅጉ የሚመራው ተወዳጅ ሚዲያ፣ ስለኢንጂነሩ ቴሌፕሪንተር እንደሚከተለው ዘርዝሯል፡፡

‹‹…የኪቦርዱን ቅርፅ ካስተካከልኩት በኋላ በዚያን ጊዜ የአዕምሯዊ ንብረት ሕግ የፈጠራ ውጤቴን በይፋ አስመዘገብኩ፡፡ በኋላም ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከብኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም. መኪናው (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ አገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የሥራ ተበረታችነት ተሰማኝ፡፡

‹‹ወዲያው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ፡፡ በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተ መንግሥት ተደረገ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ በወቅቱ የኤርትራው ገዥ ልዑል ራስ አሥራተ ካሳ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲስ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር፡፡››

ከኢትዮጵያ ባለፈ በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ባለሙያዎች ዘንድ ከበሬታን ያተረፉትና ያሳለፉትንም ሕይወት ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጄኔቫ›› ብለው መጽሐፍ ያሳተሙት ኢንጂነር ተረፈ የራስወርቅ፣ በተወለዱ በ86 ዓመታቸው ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. አርፈው፣ ግንቦት 4 ቀን የተቀበሩ ሲሆን፣ ሙት ዓመታቸውም ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን ታስቦ ውሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...