የሸማቾች ተግዳሮቶች የዋጋ ንረትና የኑሮ መወደድ ብቻ አይደለም፡፡ ገንዘባቸውን ከፍለው ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማግኘትም ይቸገራሉ፡፡ የአንዱን ምርት ትክክለኛነት አውቆ ከመግዛት ይልቅ በእምነት የሚያደርገው ግብይት ጎልቶ ይወጣል፡፡ ሁሌም በእምነት የሚደረገው ግብይት ግን ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል፡፡
በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ህፀፆች በርካታ ከመሆናቸው አንጻር ሸማችና ተገልጋዮችን ለአደጋ የሚያጋልጡበት ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ከሚያደርጉት አንዱ ሸማቹ ደረጃውን የጠበቀ ምርት መሆኑን ለማወቅ ለማረጋገጥ የሚችልበት ዕድል ጠባብ መሆኑ ነው፡፡ ሸማቹ ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስችሉ አሠራሮች ደካማ መሆን ተጋላጭነቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ገበያ ውስጥ እንደ ልብ ይቸበችባሉ፡፡ ከትክክለኛ ልኬታቸው በታች ታሽገው የሚሸጡ ምርቶች ቁጥር ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በተለይ በሸቃባ የልኬት መሣሪያዎች (ሚዛን) የሚሠራው ሸፍጥ ሸማቾችን በእጅ እየጎዳ ነው፡፡ እነዚህን የልኬት መሣሪያዎች በየተወሰነ ጊዜው በመፈተሽ ትክክለኛ አገልግሎት እየሰጡ ነው አይደለም በሚል በሕግ የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው መንግሥታዊ አካል አሁን ላይ ሥራውን እየሠራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም ቢያንስ የአንዳንድ መደብሮችና የልኬት መሣሪያ የሚጠቀሙ ድርጅቶች ዘንድ ጎራ ብለው በመፈተሽ ትክክለኛ የልኬት መሣሪያ መሆኑን የሚያረጋግጥ ምልክት ያስቀምጡ ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ የለም፡፡ በየመደብሩ ያሉ የልኬት መሣሪያዎች ተቆጣጣሪ ስለሌላቸው ሸማቹ ይሸቀባል፡፡ በተለይ የልኬት መሣሪያ ሌብነት ነግሦ የሚታይባቸው እንደ ሥጋ ቤት ያሉ ድርጅቶች ጥብቅ ክትትል የሚያሻቸው ቢሆንም ተቆጣጣሪ በማጣታቸው ከእያንዳንዱ ኪሎ የሚሸቀበው ሥጋ ሸማቹን እያማረረ ነው፡፡ የመሸጫ ዋጋቸው ግነት ሳያንስ ቅሸባቸው የሸማቹን ሸክም እያከበደው ነው፡፡ ስለዚህ የሸማቾች ችግር የዋጋ ንረት ብቻ ሳይሆን ውድ በተባለ ዋጋ የሚገዟቸው አንዳንድ ምርቶች መጠን እየተቀሸበ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆነበት ነው፡፡ ወደ ወፍጮ ቤት ጎራ ብሎ እንደ ጤፍ ያሉ መሠረታዊ ያውም ውድ የሚባሉ ምርቶችን የገዛ ሸማች ወጣ ብሎ ትክክለኛ ሚዛን ፈልጎ ሲያስለካ በአብዛኛው ትክክለኛውን መጠን አያገኝም፡፡ ከአንድ ኩንታል ሁለት ሦስት ኪሎ መበላቱን ያረጋግጣል፡፡ ጭካኔው የበረታበት ሻጭ ደግሞ አምስትና ስድስት ኪሎ ሊቀሸብ የሚችልበት አጋጣሚ የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆንበት አንደኛው ምክንያት እንዲህ ያለው ክፉ አመል የተጣባቸው ሻጮች አልጠግብ ባይነት መንሰራፋቱ ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የልኬት መሣሪያዎችን መፈተሽና ማረጋገጥ ያለበት መሥሪያ ቤት ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ ካለመውጣቱ ጋር ይያያዛል፡፡
እንደ ዘይት ያሉ ፈሳሽ ምግብ ነክ ምርቶችም ቢሆኑ ችግሩ የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡ ልኬታቸው ትክክል መሆን አለመሆናቸው ቢፈተሽ አጀብ ሊያስብል ይችላል፡፡ 25 ሊትር ወይም 5 ሌትር ነው ወይ? ከተባለ ላይሆን የሚችልበት አጋጣሚዎችን በአንዳንድ ምርቶች ላይ እናያለን፡፡ ሸማች ግን የተጻፈን ቁጥር እያየ ብቻ ይገዛል፡፡
ከልኬት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች ብዙ ምርቶች ላይ መታየቱ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ገበያ ውስጥ የሚታዩ ምርቶች የተመረቱበትን ጊዜ የማያሳውቁ ናቸው፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚያበቃው መቼ እንደሆነ እንኳን ያልተቀመጠባቸው መሆኑ ራሱ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡
ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ጉዳይም አሳሳቢ የሚባል ነው፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በኮንትሮባንድ ገብቶ የማይሸጥ የምርት ዓይነት አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ በኮንትሮባንድ የሚገቡ የተለያዩ መድኃኒቶች ሳይቀር በገበያ ውስጥ መገኘታቸው ነው፡፡ ለሕዝብ ደኅንነትና ጤንነት ግድ የማይሰጣቸው አንዳንድ የመድኃኒት ቤት ባለቤቶችና ባለሙያዎች በኮንትሮባንድ የገቡትን መድኃኒቶች በድፍረት እየሸጡ ነው፡፡
በዚህ ማረጋገጫ የሚሆን በለስ ሳይቀናቸው በጉምሩክ ተያዙ ከሚባሉ ዕቃዎች ውስጥ አንዱ መድኃኒት መሆኑ ነው፡፡ ከሰሞኑም በኮንትሮባንድ ከተያዙ ዕቃዎች ውስጥ ለተለያዩ ሕመም ፈውስ ይሰጣሉ የተባሉ የመድኃኒት ዓይነቶች ይገኛሉ፡፡
እነዚህ መድኃኒቶች በኮንትሮባንድ ከገቡ በኋላ መዳረሻቸው የትም ሊሆን አይችልም፡፡ ፋርማሲዎች ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ የገቡ መድኃኒቶች ደግሞ ትክክለኛ ፈውስ የሚሰጡ ይሆናሉ ተብሎ ስለማይታመን የሸማቾች አበሳ ምን ድረስ እየሆነ እንደመጣ ሊያመላክተን ይችላል፡፡
እዚህ ላይም እንዲህ ያለው መድኃኒት በአንደ ፋርማሲ ውስጥ ሲገባ በትክክል የተቆጣጠረ ባለሥልጣን ዕውቅና አግኝቶ የገባ ነው ብሎ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ያለ አይመስልም፡፡ ቢኖርም ብዙዎችን እየደረሰ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡
ከትክክለኛ አስመጪ ሕጋዊ ሒደቱን ተከትሎ መግባት አለመግባቱን በትክክል የሚቆጣጠር ስለሌለ አንዳንድ ደንታ ቢስ የፋርማሲ ባለቤቶች መደብራቸውን በኮንትሮባንድ በገቡ መድኃኒቶች ጭምር የሚሞሉ እየሆኑ ነው፡፡
ሸማቹ ግን በእምነት እነዚህን መድኃኒቶች ገዝቶ ይጠቀማል፡፡ አይታወቅ እንጂ እንዲህ ባለው ድርጊት ስንቶች እስከ ወዲያኛው እንዳሸለቡ ቤት ይቁጠረው፡፡ ከእምነትና ከሸመታ ጋር በተያዘ ሌላው እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለውና ብዙ ጊዜ ችግር የማታይበት የጤፍ ዱቄትና የእንጀራ ግብይት ነው፡፡
ከሰሞኑ ፖሊስ እንዳስታወቀው የጤፍ ዱቄትን እንደ ሠጋቱራ ካሉ ባዕድ ነገሮች ቀላቅለው ሲያዘጋጁና ሲሸጡ መያዛቸው ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦች ይህንን ድርጊት ለዓመታት ይከውኑ ነበር፡፡ ሸማቹም አምኖ ገዝቶ ሲጠቀም እንደነበር እንረዳለን፡፡ ድርጊቱ የስንቶችን ጤና እንዳናጋ መገመት ይቻላል፡፡ ለእነዚህ ትክክለኛ ላልሆኑ ምርቶች ሸማች ያልተገባ ዋጋ ማውጣታቸው ሲታሰብ ችግሩን ድርብርብ ያደርገዋል፡፡ በገንዘባቸው በሽታ እንደሸመቱ ይቆጠራል፡፡
በነገራችን ላይ የጤፍ ዱቄትን ከተለያዩ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለገበያ የሚያቀርቡ ሰዎች በአጋጣሚ ተያዙ እንጂ በተመሳሳይ ድርጊት የተሰማሩ ብዙ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ግብዓት እንጀራ ጋግረው የሚያቀርቡ በየመንደሩ የተሸሸጉ ሕገወጦችም በተመሳሳይ የሚታዩ ናቸው፡፡ ሸማቹ በእምነት የሚገበያያቸው ጥቂት የማይባሉ ምርቶች እንዲሁም የልኬት ችግር የጥራት ችግር ያለባቸው ምርቶች እየጨመሩ የመምጣታቸውን ያህል ጥብቅ ቁጥጥር ያለመደረጉ ችግሩን እያገዘፈው መጥቷል፡፡
በተለይ ከባዕድ ነገሮች ጋር የሚቀላቀሉ አንዳንድ ምርቶች ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ከመሆኑ አንጻር ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አውቆ ቁጥጥርን ያለማጥበቁ ጉዳይ ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ተግባር ተያዙ የሚባሉ ሕገወጣች እጅ ከፍንጅ መያዛቸው እየተገለጸ ፍርድ ቤት ቀርበው ተፈረደባቸው ሲባል አለመሰማቱ ደግሞ ለሁኔታው መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለዙህ ሸማቹን ከመታደግ አንጻር እየባባሱ ያሉ እንዲህ ያሉ ሕገወጥ ሥራዎችን በጥብቅ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ነገሩ ቸል በተባለ ቁጥር ሕገወጥ ሥራው እየሰፋ ብዙዎች ለአደጋ እየተጋለጡ ነውና የመፍትሔ ያለ ማለቱ ተገቢ ነው፡፡