በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአባልነት ወንበር የሌላቸው ላኪዎች ከግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የወጪ ምርቶችን በቀጥታ መገበያየት እንዲችሉ ተፈቀደ። ሊኪዎች ከግንቦት 7 ቀን በኋላ በአገናኝ አማካይነት ከምርት ገበያው ግብይት መፈጸም አይችሉም ተብሏል።
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ለምርት ገበያው በላከው ደብዳቤ መሠረት በምርት ገበያው ግብይት መፈጸም የሚፈልጉ ላኪ ድርጅቶች የሚያስፈልገውን ሥልጠናና መስፈርት በማሟላት ያለ አገናኝ (ወንበር ያላቸው ደላሎች) በቀጥታ በምርት ገበያው ግብይታቸውን ማከናወን እንዲችሉ መፍቀዱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያገበያያቸውን 22 ምርቶች ወደ ውጭ መላክ የሚፈልጉ ድርጅቶች በቀጥታ ግብይት መፈጸም እንዲችሉ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መመርያ ተሰጥቶታል፡፡
በዚህ መሠረት ላኪ ድርጅቶች በምርት ገበያው በሚመራበት ሕግና ደንብ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች ካሟሉ በኋላ ወደ ግብይት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ወደ ምርት ገበያ ሲገቡ ላኪ ድርጅቶቹ በሚቀጥሯቸው ባለሙያዎች ተገቢውን ሥልጠናና መስፈርት በማሟላት ግብይቱን ማከናወን እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ላኪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባሉ አገናኝ አባላት በኩል ሲገበያዩ መቆየታቸውን በመጠቆም፣ ሚኒስቴሩ ላኪ ድርጅቶችን ለማበረታታት በሚል በቀጥታ መገበያየት እንዲችሉ መፍቀዱን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በተፈቀዱት የምርት ዓይነቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ላኪዎች የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አባል ባይሆኑም ወይም ወንበር የሌላቸውን ቢሆኑም በምርት ገበያው አባል የሆነ አገናኝ ሳያስፈልጋቸው፣ በራሳቸው ግብይቱን መፈጸም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
ምርት ገበያ ከዚህ ቀደም ሲያገበያይ የቆየው የአባልነት መቀመጫ ያላቸውን ብቻ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ከግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአገናኝ አባል በኩል ግብይት መፈጸም የማይቻል መሆኑን ለላኪ ድርጅቶች የወጣው ማስታወቂያ ያስረዳል፡፡
ይህም የግብይት ሥርዓት ላኪ ድርጅቶችን ለማበረታት ያለመ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ሲል የቡና ግብይት የሚፈጸመው በምርት ገበያው ወንበር ባላቸው አገናኞች አማካይነት የነበረ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ግን ይህንን አስገዳጅ አሠራር ያስቀረ ሕግ ወጥቷል፡፡
ለሕጉ መውጣት ምክንያት የሆነውም የቡና ግብይት ሥርዓት ረዥም ሰንሰለት በመፈጠሩና በዚህም ምንም እሴት ሳይጨምሩ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት ዋጋ በማናራቸው ነው።
ኢትዮጵያ ቡና ለመላክ የምታወጣው ወጪ በዓለም የቡና ገበያ ከሚወዳደሯት እንደ ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ቬትናም የመሳሰሉ አገሮች ሲነፃፀር ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ፣ በ2010 ዓ.ም. የቡና ግብይት ሕግ መነሻ ነበር።
በዚህም መሠረት ትልቅ የግብይት ማሻሻያ በማድረግ፣ በምርት ገበያው ወንበር ገዝተው በአገናኝነት በሚሠሩ አባላት በኩል ሲካሄድ የነበረው የቡና ግብይት አስገዳጅ መሆኑ ቀርቶ ተገበያዮች ከፈለጉ ብቻ የሚገበያዩበት መንገድ እንዲሆን ተደርጓል።
የቡና ግብይት ተዋናዮች ምርቶቻቸውን ከፈለጉ ብቻ በምርት ገበያ ውስጥ ባሉ አገናኞች መሸጥ የሚችሉ ሲሆን፣ ካላስፈለጋቸው ግን ቡና አቅራቢዎቹ በቀጥታ በምርት ገበያ ውስጥ የራሳቸውን ምርት ለመሸጥ የሚያስችላቸው አሠራር ይፋ ተደርጓል። ይህም፣ በመካከል የነበሩ አገናኞች የቡና ገበያን ተቆጣጥረው በፈለጉት ጊዜ የማቅረብ፣ የማከማቸትና ያሻቸውን የማድረግ አካሄዳቸውን አስቀርቷል።
አዲሱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር መመርያ ከአምስት ዓመታት በፊት በቡና ላይ ተግባራዊ የተደረገውን አሠራር በሁሉም በምርት ገበያው ግብይት በሚደረግባቸው ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ ተፈጻሚ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት ይችላል።
በሌላ በኩል፣ በምርት ገበያው የሚካሄዱ ግብይቶችን ለማቀላጠፍና ኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓትን ለማስጀመር የዲጂታል ግብይት ቴክኖሎጂ በማበልጸግ ላይ እንደሚገኝም አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ማበልጸግ ሥራው በጥቂት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ዲጂታል ግብይት በምርት ገበያው ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ይህም በምርት ገበያው የገበያዩ ድርጅቶች ከየትም ቦታ ሆነው በቀላሉ መገበያየት የሚችሉበትን መንገድን በማመቻቸት፣ ብዙዎችን ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ለማበረታታት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ ምርት ገበያው ከሚያገበያየው 22 ምርቶች በተጨማሪ በቅርቡ የሚቀላቀሉ ማዕድን፣ ሲሚንቶና ጨው ጭምር ለማገበያየት በሒደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡