የአፍሪካ ኅብረትን የወለደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) በአዲስ አበባ ከተማ ከተመሠረተ ዘንድሮ 60 ዓመት ሞላው፡፡ በ1955 ዓ.ም. ወርኃ ግንቦት በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት የተሰባሰቡ የአፍሪካ መሪዎች ለአፍሪካውያን ኅብረት መሠረት የጣለውን አአድ ዕውን አድርገውታል፡፡
የዚህን አኅጉራዊ ድርጅት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር የ60 ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያንና ቀራፂያን የሥነ ጥበብ ሥራዎች የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ ካዛንቺስ በሚገኘው በታሪካዊው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዳራሽ ውስጥ አዘጋጅቷል፡፡ ‹‹የአፍሪካ ቀን አፍሪካዊ ማንነት የሥዕል ትርዒት›› የሚል ርዕስ ያለውና ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚከፈተው ዓውደ ርዕይ የሚያበቃው የአፍሪካ ቀን በሚታሰብበት ግንቦት 17 መሆኑ ተገልጿል።
የሥዕል ትርዒቱ ማስተዋወቂያ ሰሌዳ ሆኖ የቀረበው በአፍሪካ አዳራሽ መግቢያ በግዝፈት የሚታየው፣ ‹‹አፍሪካ ትናንት ዛሬና ነገ›› የተሰኘው የእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ታሪካዊ ሥራ ነው፡፡