ከአራት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (አፍኮን) ለማዘጋጀት፣ ስድስት አገሮች ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ማስታወቃቸውን፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታወቀ፡፡
የካፍ ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በቀረበው ጥሪ መሠረት ፍላጎታቸውን ካሳወቁ ስድስት አገሮች መካከል ሦስቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ኬንያ፣ ዑጋንዳና ታንዛንያ በጋራ ለማዘጋጀት ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው፡፡ ሌሎቹ አልጄርያ፣ ቦትስዋና እና ግብፅ ናቸው፡፡
አባል ማኅበራት የአዘጋጅነት ጥያቄ ካላቸው፣ ከተሟላ ሰነድ ጋር ማቅረብ የሚገባቸው የመጨረሻው ቀነ ገደብ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. መሆኑን ያስታወቀው ካፍ፣ ለአዘጋጅነት ማመልከቻቸውን ባስገቡ አገሮች በመገኘት የመስክ ምልከታ የሚደረገው ከግንቦት 24 ቀን እስከ ሐምሌ 8 ቀን ድረስ መሆኑን ገልጿል፡፡
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ከ33 ውድድሮቹ ሦስቱን 3ኛ፣ 6ኛ እና 10ኛውን ውድድር ያዘጋጀችው የአፍሪካ ቀንድ አገሯ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለ2027ቱ ዋንጫ አዘጋጅነት የሚወዳደሩት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባሎቹ ኬንያ ታንዛንያና ዑጋንዳ ካሸነፉ ከቀጣናው የመጀመርያዎቹ ይሆናሉ፡፡