- ሦስት ሚሊዮን ነዋሪዎች የከፋ ድህነት ውስጥ ናቸው ተብሏል
- ከአጠቃላይ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት መጎዳታቸው ተገልጿል
በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።
ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ተቋማቸው በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተካሄደው ጦርነት የደረሰውን ጉዳትና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት (Damage and Needs Assessment) በማከናወን፣ የጥናት ውጤቱን ለመንግሥት እንዳቀረበ ተናግረዋል።
በጥናት ግኝቱ መሠረትም ያጋጠመው አጠቃላይ ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ሪፖርታቸው አመላክቷል። ይህም በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ነው።
ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ከተቀመጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ‹‹22 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 20.4 በመቶ የሚገመት ጉዳት›› ደርሷል።
በዚሁ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ፣ ‹‹ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 5.5 በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ (Economic Loss)›› መድረሱን ሪፖርቱ ያመለክታል።
ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በጦርነቱ በቀጥታ የተጎዱ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት የከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸውንም አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተቀመጠው የጉዳት መጠን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከውጭ አበዳሪዎች ለኢኮኖሚ ልማት ተበድራ ካልመለሰችው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ጋር እኩል መሆኑን መረዳት ይቻላል። የገንዘብ ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱ ይፋ በሚያደርገው የዕዳ ሁኔታ መግለጫ መሠረት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለባት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን 28 ቢሊዮን ዶላር ነው።
በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ እንዲቻል ለአምስት ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2028 ድረስ) የሚቆይ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ አገራዊ የዕቅድ ማዕቀፍ (Ethiopia Resilient Recovery and Reconstruction Planning Framework) መዘጋጀቱን አስረድተዋል። ለዚህ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ በዕቅድ ማዕቀፉ መመላከቱንም ገልጸዋል።
በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በተደረገ የዕርዳታ ስምምነት፣ ፕሮግራሙን ወደ ሥራ ለማስገባት እንደ መነሻና መንደርደሪያ የሚሆን 300 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥም የደረሰውን ጉዳት መጠንና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ አክለዋል።
የተለያዩ የውጭ የልማት አጋሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎችን ለማቋቋም የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ይሁንታ እየሰጡ ሲሆን፣ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር የሚገኙ ኤጀንሲዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጉዳት በደረሰባቸው ክልሎች በመገኘት ከክልሎቹ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ማኅበረሰቦች ለማቋቋምና ለመደገፍ የሚውል 2.3 ቢሊዮን ዶላር በጀት ለመመደብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በጀቱ ለሁለት ዓመታት የሚተገበሩ የማገገሚያ ፕሮጀክቶችን ለማከናናወን የሚውል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አመዛኙ በጀት በትግራይ ክልል ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ወጪ እንደሚደረግም ታውቋል።
የፕሮጀክት ትገበራውን በመጪው ወር ለመጀመር የወሰኑ ሲሆን፣ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስፈልግ 250 ሚሊዮን ዶላር በጀት ከተመድ የፋይናንስ ምንጮች ለማስፈቀድ ንግግር ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
|
|