በባንኮች በኩል ተከፋይ የሚሆነውን የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ወደ ቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት ለማሸጋገር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አሁን በባንኮች የክፍያ ሥርዓት በጥቅል (በበልክ) እየተከፈለ ያለውን ሒደት በቀጣይ ወደ ቴሌ ብር ለማሸጋገር ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ድርሻን ለማሳደግና ቀልጣፋ ለማድረግ እስካሁን የ159 ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴ እንዲተገብሩ መደረጉን ያስታወቀው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ለአብነትም በተያዘው ዓመት የዘጠኝ ወራት 79.2 ቢሊዮን ብር ክፍያ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መከፈሉን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የመንግሥት የኤክትሮኒክስ ክፍያ ድርሻ ለመወጣት እንዲያስችለው የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነና ለአብነትም የታክስ ክፍያ አሰባሰብ ሥርዓቱ በቴሌ ብር እንዲከፈል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡
በባንኮች በኩል ተከፋይ የሚሆነውን የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በቀጣይ በቴሌ ብር እንደሚሆን መገለጹን ተከትሎ ኩባንያው የሚጠብቀው ቅድመ ዝግጅትና ያለው ዓቅም ምን ይመስላል? በሚለው ዙሪያ የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በመንግሥት የተያዙት ጉዳዮች ወቅቱን ጠብቀው ቢገለጹ እንደሚሻል ተናግረው፣ ነገር ግን ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማቅረብ የሚያስችል በቂ ዝግጅትና አቅም እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
ተቋሙ በሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎቱ እስካሁን ከ32 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አገልግሎት እየሰጠ እንደመገኘቱ መጠን የዘረጋው ሲስተም አገልግሎቱን በቀላሉ ለመስጠት ያስችለዋል ሲሉ አቶ መሳይ አክለዋል፡፡ የትኛውም ውሳኔ ከሚመለከተው አካል ከመጣ መሥራት እንደሚቻል አክለዋል፡፡
ደመወዝ በቴሌ ብር መከፈሉ የተቋማትን ቅልጥፍና በመጨመር የሚያደርገውን አስተዋጽኦ በመግለጽ፣ በዕረፍትና በበዓላት ወቅት የሚውል የደመወዝ ክፍያ ቀንና ተዛማጅ ጉዳዮች ለደመወዝ ከፋዩም ሆነ ተከፋዩ በሚያመች ለመክፈል እንደሚያስችል አቶ መሳይ ይናገራሉ፡፡
እስካሁን ባለው አገልግሎቱ እንደ ደመወዝ ዓይነት የጅምላ (በበልክ) ክፍያ በሚከፈልበት ወቅት ሠራተኞች የደመወዛቸውን እስከ 35 በመቶ ያለምንም ዋስትና መበደር እንደሚችሉ የገለጹት ቺፍ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰሩ፣ ኩባንያው በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ አማራጮች እንደሚያቀርብ አብራርተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ከሚመለከተው አካል የመጣ አቅጣጫ አለመኖሩን አቶ መሳይ አስምረውበታል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊ እንዲህ መባሉን መረጃ የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ባንኩ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ በእርሱ በኩል የሚከፍል ሲሆን፣ ለዚህ አገልግሎቱ ምንም ዓይነት ክፍያ የማይጠይቅበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በቴሌ ብር በኩል ደመወዝ ይከፈል ከተባለ ግን አሁንም ኢትዮ ቴሌኮም የሚጠቀመው ከባንኮች ጋር በመተሳሰር መሆኑ አይቀርም ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ዝውውርን ይፋ ካደረገበት ጊዜ አንስቶ እስከተያዘው የግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ 32.2 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳፈራ፣ በአገልግሎቱም እስካሁን ከ375.2 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ግብይቶች (ትራንዛክሽንስ) እንደተፈጸመ አስታውቋል፡፡ እንዲሁም የነዳጅ ክፍያ በአስገዳጅነት በቴሌ ብር እንዲፈጸም ከተደረገበት ከሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ 2.7 ቢሊዮን ብር ግብይት መፈጸሙ ታውቋል፡፡