Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነትን ሥርዓት ለመወሰን የወጣው አዋጅ ተግባራዊ እንዳልሆነ ተገለጸ

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነትን ሥርዓት ለመወሰን የወጣው አዋጅ ተግባራዊ እንዳልሆነ ተገለጸ

ቀን:

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በመካከላቸው፣ እንዲሁም የክልል መንግሥታት በጣምራ በተሰጣቸው ሥልጣንና የሚያገናኙዋቸው ጉዳዮችን እንዲያግዝ የወጣው ‹‹የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት›› አዋጅ በተሟላ መንገድ ተግባራዊ አለመደረጉ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ በመንግሥታት ግንኙነት ጽንሰ ሐሳብና ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ ላይ፣ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በግራንድ ኤሊያና ሆቴል ባደረገው የፖሊሲ ማብራሪያ መድረክ ላይ ነው፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሥዩም መስፍን (ዶ/ር)፣ በኢፌዴሪ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ 1231/2013 ላይ ስድስት የግንኙነት መድረኮች ተደንግገው ወደ ሥራ ይገባሉ የሚል ዕሳቤ ቢኖርም፣ እስካሁን በተሟላ መንገድ ወደ ተግባር አለመግባቱን የሰላም ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት አረጋግጧል ብለዋል፡፡

‹‹አዋጁ በተሟላ መንገድ አልተተገበረም›› ሲባል በአንፃራዊነት ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ችግሮችን ለመፍታት፣ ክልሎችና የፌዴራል መንግሥት በትብብር ለመሥራት፣ እንዲሁም የጎንዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ፣ ክልሎች በጋራ ወደ ግጭትና ሁከት ወይም ወደ መግለጫዎች ከመሄድ ችግሮቻቸውን ቁጭ ብለው መደበኛ በሆነ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህል የሚለውን የሚመለከት እንደሆነ ሥዩም (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

‹‹በተደጋጋሚ እንዳየነው በርካታ ያለመተማመን ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህም በክልሎች መካከል፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልል፣ እንዲሁም በሕዝብ ደረጃም ቢሆን ሰፊ አለመተማመን እየነገሠ ነው የመጣው፤›› በማለት ያስረዱት ሚኒስትር ደኤታው፣ ‹‹ብዙ ግጭቶች በክልሎች መካከል ወሰንን መሠረት በማድረግ ይካሄዳሉ፡፡ ግጭት ወደፊትም የሚኖርና ሙሉ በሙሉ የሚቀር ባይሆንም፣ ነገር ግን በሠለጠነ መንገድ በውይይት፣ በሕግና በአሠራር ሥርዓት መሠረት መፈታት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች ያደገ የውይይት ባህል ስለሌለ፣ ሁሉም የራሱን ችግር የሚናገርና የሌላውን ችግር የማያዳምጥ በመሆኑ መዋቅሮች ሲዋጉ ይታያል፤›› ያሉት ሥዩም (ዶ/ር)፣ የክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎችን ጨምሮ ሌሎች መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች ሲጋጩና ሲዋጉ ሕዝብ ሲፈናቀል በተደጋጋሚ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ የሠለጠነ ውይይት ባህል አለመኖርና ባልተጨበጠ የሴራ ፖለቲካ ምክንያት፣ ማኅበረሰቡ ወይም ክልሎች አለመተማመን ደረጃ ላይ መድረሳቸው ያመጣው ችግር እንደሆነ አክለዋል፡፡

ይህ ችግር እንዲቀረፍ ጠንካራ የሆነ የግንኙነት ሥርዓት በመፍጠር የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት በጋራ ሆነው እየተወያዩ ችግራቸውን የሚፈቱበት፣ ፖሊሲያቸውን፣ አዋጆቻቸውንና ዕቅዶቻቸውን የሚያስፈጽሙበት፣ ክልሎች አለመግባባቶች ካሉ በውይይትና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ባህል ለማዳበር፣ ‹‹የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት›› በተለይም ለፌዴራል ሥርዓት ወሳኝ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥትና የፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዳይሬክተርና ተመራማሪ ኃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር)፣ የአዋጁን አተገባበርና ያጋጠሙ ችግሮችና መወሰድ የሚገባቸውን ዕርምጃዎች በተመለከተ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

አዋጁ ከወጣ ጀምሮ ለማስተዋወቅና ለመተግበር አጋዥ የሚሆኑ ደንቦችን ለማዘጋጀት የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተደረጉ ጥረቶችን በበጎ ጎኑ የገለጹት ኃይለኢየሱስ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን በአዋጁ ዙሪያ ተገቢው ግንዛቤ አለመፈጠሩን፣ በአዋጁ መሠረት መደራጀት ያለባቸው ተቋማት ለአብነትም አገር አቀፍ ሴክሬታሪያት ወደ ሥራ አለመግባቱ ያጋጠመ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዋጁ በሚያስቀምጠው መሠረት የሪፖርት፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ አለመሆኑን፣ አገር አቀፍ የጎንዮሽ የመንግሥታት ግንኙነቶች መድረክ አለመፈጠሩን ባቀረቡት የዳሰሰ ጥናት አቅርበዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከክልል መንግሥታት ጋር ያለው ግንኙነት የተዋረድ የመንግሥት ግንኙነት ሲሆን፣ አንድ ክልል ከሌላ ክልል ጋር የሚያደርገው ግንኙነት የጎንዮሽ ግንኙነት ይባላል ብለዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የመንግሥታት ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ አቶ ግርማ ቸሩ፣ አዋጅ ቁጥር 1263/2013 መውጣቱን ተከትሎ አፈጻጸሙ፣ በተለይም በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ዘንድ ምን ይመስላል በሚለው ላይ በተመረጡ 32 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ላይ የተደረገውን ጥናት ተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ በግኝቱም፣ ግንኙነቱ ከአዋጁ አስቀድሞ በነበረበት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የቀጠለና አዋጁ ውስጥ በተቀመጡ የግንኙነት መርሆዎች መሠረት አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዴስክ ኃላፊው እንዳስረዱት፣ የመንግሥታት ግንኙነት በዋናነት የሚያስፈልግበት ምክንያት፣ ሁለቱ መንግሥታት የየራሳቸውን ሥልጣን ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ የሚያገለግሉት አንድን ማኅበረሰብ እንደ መሆኑ መጠን፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀምጠው በጋራ ማመቻቸት አለባቸው የሚለውን ለመመለስ ነው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ በአግባቡ እንዲመራ፣ ክልሎች በተሰጣቸው ሥልጣን ወሰን ሲንቀሳቀሱ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ፣ ቢፈጠሩም እንኳን በአግባቡ የሚፈቱበት ራሱን የቻለ ሥርዓት፣ ‹‹ለመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት›› ዕድል እንደሚሰጥ አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

በተደረገው ጥናት የተቀመጠው ምክረ ሐሳብ እንደሚያስረዳው የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ ሁሉንም ነገሮች ማለትም፣ ‹‹ምን ዓይነት ፎረሞች መቋቋም አለባቸው?›› ከሚለው አንስቶ፣ ‹‹መንግሥታት ምን ይሠራሉና እንዴት ይገናኛሉ?›› የሚሉትን ዝርዝር ጉዳዮችን ስለያዘ፣ አዋጁ ያቋቋማቸው አገራዊ ሴክሬተሪያትን ከማቋቋም ጀምሮ ሁሉም ዘርፎች አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡            

ከስድስቱ ፎረሞች የፌዴራል የሥራ አስፈጻሚ ዘርፍና ዘርፋዊ ግንኙነት ጥሩ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ያስረዱት ሥዩም (ዶ/ር)፣ ይህም የሥራ አስፈጻሚ ዘርፉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራና ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደጋጋሚ ሰፊ የሆነ ግንኙነቶችን በማድረግና ውሳኔ ለማሳለፍ ተግባራዊ እያደረገና ይህንንም እየገመገመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...