Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአገራዊ ምክክር የዳያስፖራው ተሳትፎ በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ማሳሰቢያ ተሰጠ

በአገራዊ ምክክር የዳያስፖራው ተሳትፎ በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዳያስፖራውን በአገራዊ ምክክር ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙ ከሰሞኑ ይፋ ሲያደርግ፣ ተሳትፎው ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጠው፡፡ የትኛው የዳያስፖራ ክፍል በውይይቶች እንደሚሳተፍ ከመለየት ጀምሮ፣ በምን ዓይነት አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይ ኮሚሽኑ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው የፓርላማው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉና የድርሻቸውን ለማበርከት ከሚፈልጉ የዳያስፖራ አባላት ጋር ምክክር ለማድረግና ግብዓት ለመሰብሰብ እየሠራ መሆኑን፣ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ያለውን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ለማነጋገር ዝግጅት መደረጉን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ በመረጃ መረብ (በሳይበር) ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚጀምርም አስታውቆ ነበር፡፡

‹‹በአገራዊ ምክክር የውይይት መድረኮች እንሳተፍ›› የሚለው የዳያስፖራው ጥያቄ ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር)፣ ዳያስፖራውን ማሳተፍ በኮሚሽናቸው ጠቃሚነቱ እእንደታመነበት አስረድተዋል፡፡

‹‹በአገራዊ ምክክር ዕውቀትና ልምድ ያላቸው እንዲሁም ለአገር በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ የዳያስፖራ አባላት አሉ፤›› ሲሉ የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ እንደ አስፈላጊነቱ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ለውይይቶቹ ጠቃሚ እንደሚሆን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ያነሱት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ግን ‹‹ዜግነት ያለው ነው ወይስ ዜግነት የሌለው ዳያስፖራ በውይይቶቹ መሳተፍ ያለበት የትኛው ነው፤›› በማለት ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

የዳያስፖራ አባላት በምክክሮቹ ይሳተፉ ቢባል እንኳን፣ በምን ዓይነቶቹ የምክክር ጭብጦችና አጀንዳዎች ላይ መወያየት እንደሚገባቸው በጠራ ሁኔታ መቀመጥ እንዳለበትም ተጠይቆ ነበር፡፡

በዳያስፖራው ወገን የአገሪቱ ችግር እንዲፈታም ሆነ ወደ መግባባትም ሆነ ወደ አንድነት እንድትመጣ ፍላጎት የሌላቸው ጥቂቶች እንደሚታዩ የጠቀሱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በስመ ዳያስፖራ ሁሉንም በውይይቶቹ ማሳተፍ አሉታዊ ውጤት ሊኖራው እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

የቋሚ ኮሚቴውን ምክረ ሐሳብ የተቀበሉት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችም ጉዳዩ በጥንቀቄ እንደሚታይ ነው ያስረዱት፡፡

በተያያዘ ዜና አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረገው፣ ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ አካታችና አሳታፊ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በ56 አገሮች ከ8,300 በላይ አባላትን ያቀፈውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ማኅበር (Ethiopian Global Youth Group) እና በየተለያዩ አደረጃጀቶች ሥር ከሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጋር ውይይት መጀመሩን፣ ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...