ኒያላ ሞተርስ አክሲዮን ማኅበር የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ገለጸ፡፡
ማኅበሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የኒሳን ተሽከርካሪዎችን መገጣጠሚያ ፋብሪካ ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅቱን እያጠናቅቀ መሆኑን፣ የኒያላ ሞተርስ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ቦጋለ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአገር ውስጥ የተሽከርካሪዎችን ሞተርስ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት፣ በሸገር ከተማ ዙሪያ ካሉት የገላን ከተማ አስተዳደር 80 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ወስደናል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ሥራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ሲመጣ ግቢያችን ጠቦናል፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ዘመናዊ ወርክሾፕ ለመገንባት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንና ከዚህ በኋላ በቅርብ ጊዜ የተሽከርካሪ የመገጣጠም አገልግሎት ባደረጉት ጥናት መሠረት እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡
በምን ያህል ካፒታል የመገጣጠሚያ ፋብሪካውን እንደሚገነቡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው፣ የተሽከርካሪ የመገጣጠም ጅማሮውን በተመለከተ ግን ሒደቱን እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡
ኒያላ ሞተርስ አክሲዮን ማኅበር ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል 50ኛ ዓመት በዓሉን አክብሯል፡፡
‹‹50ኛ ዓመት በዓላችንን ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. አክብረናል፤›› ያሉት አቶ መስፍን፣ ‹‹50 ዓመት ረዥም ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ ያንን አልፎ ኒያላ ሞተርስ ለዚህ በዓል ደርሷል፡፡ ይህንን በዓል ስናከብር እንደ ካምፓኒ ስንጀምር ከነበረን ጊዜ ጀምሮ እያደግን መጥተን አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ለዚህም ትልቁ አስተዋጽኦ ከእኛ በፊትም የነበሩ የማኔጅመንት አባላት፣ ሠራተኞች፣ እንዲሁም አሁን ያሉት የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሚና አለው፤›› ብለዋል፡፡
ከ50 ዓመታት በፊት 1973 ዓ.ም. ሶማሌ ተራ ሥራ የጀመረው ኒሳን ሞተርስ፣ የሚያመርተውን ዳትሰን ተሽከርካሪ ሥራ መጀመሩንና ለ50 ዓመታት ለኒያላ ሞተርስ ከኒሳን ሞተርስ ኮርፖሬሸን ጋር ያለው ፓርትነርሽፕ አፍሪካ ውስጥ ካሉ የኒሳን ቀዳሚ ዲለር አንዱ ኒያላ ሞተርስ መሆኑን አክለዋል፡፡
በክልሎች ያላቸው ተደራሽነት ምን እንደሚመስል እንዲያስረዱ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹ኒያላ ሞተርስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ መኪና አስመጪ ኦፊሻል ዲለሮች ውስጥ በኔቶርክ በአገሪቱ ውስጥ ባለው የቅርንጫፍ ሥርጭት ከፍተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ድርጅት ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በመቀሌ፣ በባህር ዳር፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳና በጅማ የራሳችንን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ከፍተን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተለያዩ ከተሞች በሐዋሳ፣ በደሴና በሰመራ ደግሞ ኤጀንቶች ቀጥረን እየሠራን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም፣ አዲስ አበባ ውስጥም ዘመናዊ ሾው ሩም ፍላሚንጎ አካባቢ ከፍተን አገልግሎት እየሰጠን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኒያላ ሞተርስ አክሲዮን ማኅበር 50ኛ ዓመት በዓል ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፣ ድርጅቱ የኤሌክትሮኒክስ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት እንዲጀምር ጠይቀው፣ ይህን ካደረገ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው፣ ኒያላ ሞተርስ በትራንስፖርት ዘርፍ የራሱን ከፍተኛ አሻራ ማሳረፉን ተናግረዋል፡፡
ኒያላ ሞተርስ የተመሠረተው በ1973 ዓ.ም. እንደሆነና በ50 ሺሕ ብር መነሻ ካፒታል የኒሳን ሞዴል ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት እንደሚታወቅ በመርሐ ግብሩ ተነግሯል፡፡