- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ትልቁ ወጪያችን ለነዳጅ ግዥ የሚውለው ነው። ክቡርነትዎ እንደሚገነዘቡት የዩክሬን ጦርነት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል።
- ቢሆንም አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ ስለምትገኝ አየር መንገዱ ይህንን ለማቃለል አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል።
- እኛም ይህንን እንገነዘባለን ነገር ግን አብዛኛው ወጪያችን በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል በመሆኑ ነው በሚፈለገው ልክ አስተዋጽኦ ማድረግ ያልቻልነው።
- አቅዳችሁ ከሠራችሁ የሚጠበቅባችሁን አስተዋጽኦ ማሳካት ትችላላችሁ። ዛሬ ባትችሉም ነገ ማድረግ ይቻላል።
- እርግጥ ነው እኛም ትልቁ ወጪያችንን ለመቀነስና ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ በረራ ለማድረግ አቅደን በአገር ውስጥ ነዳጅ ለማምረት ዝግጅት ጀምረናል።
- ነዳጅ ለማምረት?
- አዎ። ከአየር ብከለት ነፃ የሆነ ነዳጅ በአገር ውስጥ ለማምረት የጥናት ዝግጅቱ አልቋል።
- ከአየር ብከለት ነፃ የሆነ ነዳጅ እንዴት ነው የምታመርቱ?
- ነዳጁን ለማምረት በዋነኝነት የምንጠቀመው ግብዓት መኖ ነው።
- ምንድነው ?
- መኖ ነው ያልኩት ክቡር ሚኒስትር።
- መኖ ለአውሮፕላን? እየቀለዱ ነው?
- ተረፈ ምርቱን ማለቴ ነው።
- የአርብቶ አደሩ ከብቶች በድርቅ ምክንያት እያለቁ እንደሆነ አያውቀም?
- ሰምቻለሁ።
- ታዲያ ምን የተረፈ ምርት አለ። ከአርብቶ አደሩ ጋር ልትሻሙ ካልሆነ በስተቀር?
- ከአርብቶ አደሩ የተረፈ መኖ ማለቴ አይደለም።
- ከመኖው ውስጥ ለምግብነት የማይውለውን ነው ለመጠቀም ያሰብነው።
- ያው ሽሚያ ነው።
- እንደዛ አይደለም ክቡር ሚኒስትር። አንደኛ ገና ጥናት ላይ ነው። ሁለተኛ ደግሞ እራሳችን የምናመርተውን መኖ ነው የምንጠቀመው።
- እንደዛ ነው?
- አዎ። እንደውም ለምግብነት የሚውለውን ክፍል ለአርብቶ አደሩ ማቅረብ እንችላለን። በተጨማሪም…
- በተጨማሪ ምን ?
- ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ ነዳጅ ለማምረት የምንጀምረው ፕሮጀክት ስለሆነ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ዕርዳታና ብድር የሚተገበር ነው።
- በውጭ ምንዛሪ ማለት ነው?
- በትክክል። ለዚህ ተብሎ የተቋቋመ ዓለም አቀፍ የካርበን ልቀት ቅነሳ ፈንድ አለ።
- ይኼ በጣም ድንቅ ዕቅድ ነው።
- ይመስለኛል። ፕሮጀክቱን ይሁንታ ካገኘ ፈንዱ ነፃ ፋይናንስና ወለድ የማይከፈልበት የረዥም ጊዜ ብድር ያቀርብልናል።
- አሁኑኑ ይጀመር። በፍጥነት ይመረት።
- ምኑ?
- መኖው፡፡
- ይህ እኮ እ.ኤ.አ. በ2050 ለማሳካት የያዝነው ዕቅድ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አሁኑኑ ይጀመር፡፡
- እ…
- በተጨማሪ ደግሞ…
- በተጨማሪ ምን?
- መንግሥት የሚከታተለው ፕሮጀክት እንደሆነ ይነገር!
|
|