Sunday, June 4, 2023

አነጋጋሪው የሕወሓት የሕጋዊ ሰውነት ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) በሚል ስያሜ የፖለቲካ ፓርቲ ለማደራጀት፣ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀርቦለት የነበረውን ጥያቄ የከለከለበትን መነሻ ምክንያት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 69 መሠረት የምዝገባ ፈቃድ የቀረበበት ፓርቲ ስያሜ ቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ከነበረው ፓርቲ ስያሜ ጋር በመመሳሰል በመራጮች ዘንድ ግርታን የሚፈጥር ሆኖ ከተገኘ፣ ቦርዱ የምዝገባ ጥያቄውን ሊቀበል አይገባም ሲል የመጀመርያውን መነሻ አስታውቋል፡፡

ሁለተኛ ያለውን መነሻ ቦርዱ ሲያስረዳም ጥያቄ የቀረበበት ፓርቲ ስያሜ በኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ በብቸኝነት መንቀሳቀስ የተፈቀደለት ፓርቲ ስም ነበር ይላል፡፡ ግንቦት 1983 ዓ.ም. ፓርቲው ከሥልጣን ሲወርድ ስለሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት የወጣው አዋጅ ቁጥር 3/83 አንቀጽ 8(2)፣ ኢሠፓ የተባለው ድርጅት ፀረ ዴሞክራሲና ወንጀለኛ ነው በሚል እንዲፈርስ ወስኗል፡፡ ይህ አዋጅም ሆነ አንቀጽ እስካሁን አለመሻሩን የሚጠቅሰው ቦርዱ፣ ለኢሠፓ ዕውቅና ዳግም እንዳይሰጥ ሕግ ይከለክለኛል የሚል ጭብጥ ያለው ምላሽ ይሰጣል፡፡ ዕውቅና ብሰጥ ሕግ በመተላለፍ ፓርቲው እንዲቋቋም ቦርዱ አደረገ የሚል አመለካከት በሕዝብ ዘንድ ይፈጠራል ሲል ነበር፣ ኢሠፓ በሌላ ስያሜ ዕውቅና እንዲጠይቅ ምላሽ የሰጠው፡፡

ይህንን ምላሽ ያገኙት የኢሠፓ አደራጆችም ከጥቂት ወራት በኋላ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሌበር ፓርቲ›› በማለት መጠሪያቸውን ቀይረው ዳግም ዕውቅና ጠይቀዋል፡፡ በመስከረም 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሌበር ፓርቲ ዕውቅና ማግኘቱ ይፋ ተደርጓል፡፡

ይህ የኢሠፓ የዕውቅና ጥያቄ ውዝግብ ካስነሳ ከረዥም ወራት በኋላ ደግሞ፣ የሕወሓት ዳግም ህልውና የማግኘት ጥያቄ ከሰሞኑ አዲስ ውዝግብ ይዞ መጥቷል፡፡

ምርጫ ቦርድ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ፣ ሕወሓት የሚባል ፓርቲ ከሕጋዊ ዕውቅና መዝገቡ መሰረዙን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ከፓርቲው መሰረዝ በተጨማሪ አመራሮቹ በዚህ ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ የፓርቲው ንብረቶችም ለዕዳ መክፈያና ለሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውሉ ቦርዱ ውሳኔ አሳልፎም ነበር፡፡

ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕወሓት ዕውቅናዬ ይመለስ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡ ሕወሓት ላቀረበው የህልውና ይመለስልኝ ጥያቄ ግን ቦርዱ ይሁንታ እንደማይሰጥ የገለጸ ሲሆን፣ ዕውቅናውን የከለከለበትን መነሻም ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡

ሕወሓት ኃይልን መሠረት ካደረገ የአመፅ ተግባር ቢቆጠብም፣ ነገር ግን በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 98/1/ረ መሠረት እንደገና ሕጋዊ ሰውነቱን ለመመለስ የሚያስችል ድንጋጌ በአዋጁ የለም በማለት ቦርዱ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በዚህ ምላሽ ለሕወሓት ዳግም ዕውቅና የምሰጥበት የአዋጅ መሠረት የለም ከማለት በተጨማሪ፣ የአመራሮቹን መንቀሳቀስም ሆነ የንብረት ጥያቄ እንዳልተቀበለው ይፋ አድርጓል፡፡ አመራሮቹ እንዳይንቀሳቀሱና ንብረቶቹ እንዲከፋፈሉ የሚሉ ውሳኔዎች፣ ከፓርቲው ህልውና መሰረዝ ጋር በቀጥታ የተገናኙ መሆናቸውን ነው ቦርዱ ያመለከተው፡፡

የሕወሓት ዕውቅና መነፈግ ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ ሕወሓት ዕውቅናው እንዳይመለስ ከተወሰነ በኋላ ምን ዓይነት አማራጮችን ሊከተል ይችላል የሚለው አንዱ ሐሳብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሕወሓት ዕውቅና የተከለከለው በሕግ አግባብ ብቻ ላይሆን ይችላል የሚል መላምትም እያስነሳ ነው፡፡ ሕወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ከልክሎ ለማዳከምና በሌላ ለመተካት፣ ወይም የፓርቲውን ሀብትና ንብረት ለመቀራመት የተደረገ ሽረባም ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም ይሰማል፡፡

ሕወሓት ሲያከማች የቆየውን ሀብትና ንብረት ብልፅግናን በመሠረቱ የፖለቲካ ኃይሎች መወረሱ፣ ይህንንም ለሕወሓት መልሶ የመስጠት ፍላጎት ባለመኖሩ ነው የሕወሓት ዕውቅና የተነፈገው የሚለው ጉዳይ በሰፊው እየተነሳ ነው፡፡

ሕወሓትን ቢቻል አዳክሞ ከጨዋታ ውጪ የማድረግ ፍላጎት መኖሩን የሚናገሩ ወገኖች፣ ካልሆነም በሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ድርጀቶች የመተካት ፍላጎት መኖሩን በሰፊው እየተናገሩ ነው፡፡

ከሰሞኑ ብቻ በትግራይ ለሚንቀሳቀሱ (የትግራይ ሕዝብን እንወክላለን ለሚሉ) ከሦስት ላላነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ምርጫ ቦርድ ዕውቅና መስጠቱን እንደ ምሳሌ ያወሳሉ፡፡ ከዚህ በመሳነትም አንዳንድ ወገኖች በሕወሓት ላይ የተወሰደው ዕርምጃ፣ ድርጅቱ በትግራይም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ደግሞ ህልውና እንዳይኖረው ከመፈለግ የመነጨ ውሳኔ ሊሆን እንደሚችል እየገመቱም ነው፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የሰጠው የተምቤን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎችም የትግራይ ፓርቲዎች ቅድመ ዕውቅና በተከታታይ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ትንሳዔ ሰብአ እንደርታ ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ፣ ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና)፣ አክሱማይ ዋእላ፣ እንዲሁም አሲምባ የተባሉ የትግራይ ክልልን ማዕከል ያደረጉ ፓርቲዎች የቅድመ ዕውቅና ፈቃድ ሲሰጣቸው ታይቷል፡፡

ለእነዚህ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች ዕውቅና ሰጥቶ በትግራይ ከፍተኛ ተቀባይነትና ሕዝባዊ መሠረት አለው ተብሎ ለሚታመነው ለሕወሓት ዕውቅና መንፈግ፣ የሕወሓትን ተፎካካሪነት ሆን ብሎ ለማዳከም የተደረገ ነው የሚል ስሞታ እየተነሳ ነው፡፡

መንግሥትም ሆነ ቦርዱ ሕወሓትን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሰነብት ፍላጎት አጥተዋል ከሚለው ቅሬታ ጎን ለጎን ግን፣ ሕወሓትም ቢሆን ኃጥያቱ ነው ለዚህ ያበቃው፡፡ ዕውቅና መነፈጉ ሲያንሰው ነው የሚል ሐሳብ የሚያነሱ በርካታ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ከጫካ ትግል ተነስቶ አገር ለመምራት ዕድል ያገኘው ሕወሓት ይህን የታሪክ አጋጣሚ ያለተቀናቃኝ ለ30 ዓመታት ቢያገኝም፣ ዕድሉን በአግባቡ ሊጠቀምበት ባለመቻሉ በሕዝብ ተጠልቶ በተቃውሞ ከሥልጣን መውረዱን ያወሳሉ፡፡ መንግሥት ከመምራት የክብር ማማ ወርዶ ወደ ጫካ አማፂነት ራሱን መቀየሩንም እንደ ውድቀት ይቆጥሩታል፡፡

በዚህ እልህ ሥልጣን በኃይል ዳግሞ ለመያዝ መነሳቱን፣ ይህ ካልተሳካ ደግሞ አገር በማፍረስ የራሱን ነፃ አገር የመፍጠር አጀንዳ ይዞ መነሳቱን እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ፡፡

ለዚህ ዓላማው መፈጸምም ሕወሓት የመከላከያ ሠራዊትን ማጥቃቱንና የፌዴራል መንግሥቱን መውጋቱን ያነሳሉ፡፡ አገሪቱ በቅርብ ዓመታት ለገባችበት ጦርነትና ቀውስ ሕወሓትን በዋና ችግር ፈጣሪነት ተጠያቂ ሲያደርጉ የሚታዩት እነዚህ ወገኖች፣ ሕወሓት እስከ ዛሬም በሕይወት መቆየቱም ሆነ ከሽብርተኝነት መዝገብ መፋቁ በራሱ ትልቅ ዕድል ማግኘት እንደሆነ ነው የሚያስረዱት፡፡

ሕወሓት ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ቢነፍገውም ችግር የለውም የሚሉ አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው፣ ፓርቲው ማንነቱን (ስሙን) በሌላ በመቀየር መንቀሳቀስ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ አሁን ሕወሓት ራሱን በሌላ ማንነት ለማደራጀት ይፈልጋል የሚል ጥርጣሬ ቢነሳም፣ ነገር ግን ራሱን ቲዲኤፍ (TDF) ወይስ ሌላ ማን ብሎ ሊመጣ ይችላል? የሚለው ጥያቄ ፍንጩ ገና አልታወቀም፡፡ ሕወሓትን ዳግም በሌላ ማንነት ለመከሰት የሚያስገድደው የምርጫ ቦርድ ዕውቅና መንፈግ ወይስ የራሱ ፍላጎት? የሚለው ጉዳይ ምላሹ ለጊዜው አይታወቅም፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) በሌላ ማንነት ማለትም የኢትዮጵያ ሌበር ፓርቲ ተብሎ እንዲደራጅ መወሰኑን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአደራጅ ኮሚቴ አባል አቶ ዮሐንስ ታደሰ፣ ‹‹በኢሠፓ ብንደራጅ ነበር ለእኛ የሚሻለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተቻለ መጠን አባላት በቀላሉ ለማሰባሰብ እንድንችልና ለመደራጀት እንዲቀል ሕግን ተከትለው በሆደ ሰፊነት ቢፈቅዱልን ተገቢ ነበር፤›› በማለት ያስረዱት አቶ ዮሐንስ፣ ፍርድ ቤት ሄዶ በኢሠፓ ስም ካልተደራጀን የሚል ሙግት መክፈቱ ሊኖረው የሚችል የጊዜ፣ የጉልበትም ሆነ ገንዘብ እንግልትን በመፍራት አማራጩን እንደተውት ገልጸዋል፡፡

ልክ እንደ ኢሠፓ ሁሉ በፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 መሠረት ሕወሓትም ሁለት አማራጮች እንዳሉት ነው የሚገመተው፡፡ አንዱ ጉዳዩን በፍርድ ቤት ሞግቶ ሕወሓት የሚለውን ህልውና ማስመለስ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ሕወሓት ለሚለው ስም ቀረብ ያለ ወይም ሌላ ስያሜ በማውጣት ዕውቅና መጠየቅ የሚሉ አማራጮች እንዳሉት ነው አንዳንዶች የሚናገሩት፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ግን ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ ነው የሚሉ ወገኖች፣ የሕወሓት ህልውና ጉዳይም የሚመለሰው በፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነ ነው የሚያነምኑት፡፡

ይህንኑ ውሳኔ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር የሚያገናኙ አንዳንድ ወገኖች በበኩላቸው፣ ሕወሓትን ህልውና መንፈግ የሰላም ስምምነቱንም ህልውና መንፈግ ነው ይላሉ፡፡ ሕወሓትን እንደ አንድ የትግራይ ሕዝብ ወኪል እንደሆነ የፖለቲካ ኃይል ዕውቅና በመስጠት መንግሥት ሲደራደረው እንደቆየ፣ በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካም ባደረጉት የሰላም ስምምነት ግጭቱ መቆሙን ይገልጻሉ፡፡ አሁን ሕወሓት በሚል ስም የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል እንዳይኖር መከልከል ደግሞ፣ ከሕወሓት ጋር የተደረገውን የሰላም ስምምነት በተዘዋዋሪ ዕውቅና መንፈግ ነው እያሉም ነው፡፡

ጉዳዩ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ጋር ጨርሶ እንደማይገናኝ የሚናገሩ  ወገኖች በበኩላቸው፣ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በሕጋዊ መንገድ መመሥረቱን በዋቢነት ያቀርባሉ፡፡ አሁን የፕሪቶሪያው ስምምነት ትግበራን መንግሥት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እንደሚጨርስም ይጠቅሳሉ፡፡ አሁን ሕወሓት ህልውና ይኑረው ቢባል እንኳ በትግራይ እንደሚንቀሳቀስ አንድ ፓርቲ ከመታየት በዘለለ፣ ልክ እንደ ትግራይ መንግሥት የሚቆጠርበት አንዳችም የሕግ አግባብ አለመኖሩን በመጥቀስም ጉዳዩ ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር አይገናኝም ይላሉ፡፡

ከ1963 ዓ.ም. የትግራይ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር (ትዩተማ) መመሥረት ጋር አነሳሱ የሚቆራኘው ሕወሓት፣ በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ ካስቆጠሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ማኅበረ ገስገስቲ ትግራይ (ማገብት) መመሥረትም ለሕወሓት መመሥረት መሠረት መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ ረዥም ታሪክ ያለው ፓርቲ አሁን ያቀረበው የህልውናዬ ይመለስ ጥያቄ በምን ይቋጫል የሚለው በቀጣይ አጓጊ የሚሆን ይመስላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -