ከ20 ዓመታት በላይ ሥራ ላይ የቆየውን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አዋጅን ለማሻሻል ከሁለት ወራት በፊት ቀርቦ የነበረው ረቂቅ አዋጅ እንደገና ማሻሻያ ተደርጎበት ለውይይት ቀረበ፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተቃውሞ ሲያሰማ የነበረው የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዘርፍ ምክር ቤት ተሻሽሎ የቀረበውን አዲሱን ረቂቅ እንደሚደግፍ አስታውቋል።
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት ባለድርሻ አካላትን በማካተት ሲሰናዳ የቆየው ረቂቅ እንደገና ተሻሽሎ የቀረበው ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ከሁለት ወር በፊት ቀርቦ የነበረው ረቂቅ አዋጅ የዘርፍ ምክር ቤቶችን፣ በተለይም አምራቾችን ያገለለ ነው በሚል ከኢትዮጵያ አገር አቀፍ ማኅበራት የዘርፍ ምክር ቤት ተቃውሞ ቀርቦበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ባለፈው ቅዳሜ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሻሽሎ ባቀረበው አዲስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ሲደረግ የዘርፍ ምክርቡቱ ተቃውሞ ሲያነሳበት የነበረው ዋነኛ ጉዳይ ማስተካከያ ተደርጎበት በመቅረቡ ተቃውሞውን ማንሳታቸውን የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዘርፍ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ የሚወክልቻውን አምራች ዘርፎች ባገለለ ሁኔታ የቀረበ በመሆኑ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አበባየሁ፣ አሁን ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ ግን ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ የሰጠ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡ ከአዋጁ ስያሜ ጀምሮ ማስተካከያ ተደርጎና አዳዲስ አንቀጾችንም ተካተውበት ዳግም በመቅረቡ መደሰታቸውን የሚገልጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አዲሱን ረቂቅ አዋጅ እንድንደግፍ አድርጎናል ይላሉ፡፡
ቀደም ሲል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ‹‹የንግድ ምክር ቤት›› የሚለው መጠሪያ አንዲሻሻልና እርሳቸው የሚወክሉት አምራች ዘርፍ እንዲካተት ሲያደርጉ የነበረው ውትወታ ተቀባይነት አግኝቶ የአዋጁ ስያሜ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት›› ተብሎ መስተካከሉን አመልክተዋል፡፡ አገር አቀፉ የዘርፍ ምክር ቤት ቀደም ሲል ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት›› በሚል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ዘርፉን ወይም ኢንዱስትሪውን የዘነጋ ሆኖ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ስለኢንዱስትሪው የሚጠቀስ አንቀጽ እንኳን እንዳልነበረው ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም የተነሳ ተቃውሟቸውን በተለያዩ መድረኮች ለማሰማት ተገደው እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ግን ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአገር አቀፉን የዘርፍ ምክር ቤት አመራሮች በማነጋገር አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን አቶ አበባየሁ አስረድተዋል፡፡ በተለይ የአገር አቀፉ ዘርፍ ምክር ቤት አመራር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ጋር ባደረገው ውይይት በተፈጠሩት ክፍቶች ዙሪያ በመነጋገር መግባባት ላይ በመድረሱን፣ በዚህም ረቂቅ አዋጁ ዘርፎችን ወይም ኢንዱስትሪውን አካቶ እንዲከለስ ማስቻሉም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ተቃውሞ ያቀረቡበት ረቂቅ አዋጅ የማይሻሻል ከሆነ ተቃውሟቸውን ለመቀጠል አማራጭ ዕቅዶችን ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ በቅዳሜው የውይይት መድረክም ሆነ ከሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ውይይት ውጤታማ በመሆኑ ወደ የተቃውሞ ዕቅዶቻቸውን አስቀርቷል።
ረቂቅ አዋጁ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ አዋጅ ሆኖ ስለመውጣቱ ምን ያህል እርግጠኛ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አበባየሁ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በተለይ ከሚኒስትሩ ጋር ያደረግነው ውይይትና የተሰጠን ምላሽ እርግጠኛ እንድንሆን አድርጎናል ብለዋል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አቶ ገብረ መስቀል የሰጠናቸውን አስተያየቶች ከግምት በማስገባት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ የእኛንም ሐሳብ ተረድተው ያቀረብነው ሐሳብ ገዥና አንኳር ሐሳብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተቀባይነት ስላገኘ ይህ ረቂቅ ለኢንዱስትሪው ትኩረት ሰጥቶ ይወጣል ብለን እናምናለን›› ብለዋል። በሚወጣው አዋጅ ውስጥ ዘርፉንና ኢንዱስትውን የሚመራው አካል እንዲወከል የሚያደረግ መሆኑን ሚኒስትሩ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
‹‹ሚኒስትሩ ቃል በቃል የገለጹልንም በዚህ አዋጅ ውስጥ ኢንዱስትረው ‹‹ቬቶ ፖወር›› እንዲኖው ይደረጋል በሚል በመሆኑ ኢንዱስትሪው የሚጠቅም አዋጅ ይሆናል። ይህም፣ የነበረንን ሥጋትና ተቃውሞ እንድናነሳ አስችሎናል፤›› ብለዋል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ስለሺ በልሁ በተመራው የውይይት መድረክ የዘርፍ ምክርቤቱ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ 100 በመቶ መስማማቱን እንዳስታወቀም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
‹‹እኛ ቀደም ብሎም ቢሆን አዋጁ ተጠናክሮ ይውጣ የሚለውን በመግለጫችን ሳይቀር አንድ ጠንከራ ምክር ቤት ይሁን የሚል አቋም ይዘን ነው የወጣነው። ሐሳባችን በመሰማቱ ደስተኞች ነን። ይህ ደግሞ ለእኛም ለመንግሥትም ለሁሉም የሚበጅ በመሆኑ ተቀውሟችንን አንስተን፣ ይህ ረቂቅ በቶሎ ይፀደቅ ወደሚል ውትወታ ገብተናል›› ብለዋል፡፡
እኛም ይህንን ደግፈን አዋጁ በቶሎ እንዲወጣ የሚሹ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ዘርፍ ምክር ቤቱ ወይም ኢንዱስትሪው በምክር ቤቱ ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ እንዲኖረው ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝም፣ ጎን ለጎን ደግሞ በአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያና ደንብ የሚመለሱ ጉዳዮች እንደሚኖሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ አገር አቀፍ የዘርፍ ምክር ቤት ረቂቁ ከዚሁ ቀደም በነበረው መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ሰላማዊ ሠልፍ በማካሄድ ጥያቄውን እንደሚያቀርብ፣ በዚህ መንገድ ምላሽ ካልተገኘም የራሱን የኢንዱስትሪ ምክር ቤት እስከመስረት እንደሚሄድ መግለጹ ይታወሳል፡፡ አሁን ግን ጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ በማግኘቱ ሊወስዷቸው ያሰቧቸውን ዕርምጃዎች ማጠፋቸውን አመልክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ ረቂቅ ሕግ ውስጥ በመንግሥት ይሠሩ የነበሩ አንዳንድ ሥራዎችን ለንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቱ ለማስተላለፍ የሚቻልበት አሠራር እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡ በረቂቁ በግልጽ እንደተቀመጠውም፣ ከሚኒስቴሩ (ንግድና ቀጣናዊ ትስስር) ውክልና ሲሰጠው የአምራች አገር የምስክር ወረቀትና የምርቶች ዋጋ ማረጋገጫንና ሌሎች ተመሳሳይ በውክልና የሚሰጡ ተግራባትን እንደ አዲስ የሚያቋቋመው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚያከናውን ይሆናል።
አቶ አበባየሁ እንደገለጹት፣ የተወሰኑ የመንግሥት ሥራዎችና ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች እንዲያከናውኗቸው የሚሰጣቸው መሆናቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ ኢምፖርት የሚደረጉ ዕቃዎችን ኢቫሉዌት የማድረግና የጥራት ደረጃቸውን የመለየት ሥራ የንግድ ምክር ቤቶች የሚሆን መሆኑንም በመልካም የሚታይ ነው ይላሉ፡፡
ገቢ ዕቃዎች ላይም በተወሰነ ደረጃ መንግሥት ይሠራቸው የነበሩ አንዳንድ ሥራዎች ለንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች የሚሰጥ በመሆኑ ረቂቁ አዳዲስ ነገሮች እንዳሉት ያመለክታል ተብሏል፡፡
በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ለንግድና ኢንዱስትሪ ንግድ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ላይ ያልነበሩ አዳዲስ ተግባራት የሚኖሩት ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ አገር አቀፉ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ይሠራቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ተግባራትና ከተሰጠው ሥልጣን መካከል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች በየደረጃው እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ ድጋፍ ያደርጋል፣ ያስተባብራል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት አጀንዳዎችን፣ እንዲሁም የሕግና ፖሊሲ ነክ ማሻሻያዎችን በጥናት በመለየት ለመንግሥት ያቀርባል የሚለው አንዱ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ንግድና ኢንቨስትመትን የሚመለከቱ የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና አስፈላጊ መረጃዎችን ወደ አባላት በማስተላለፍ ስለተግባራዊነታቸው ድጋፍ ማድረግም ይጠበቅበታል፡፡ ከዓለም አቀፍና ከተለያዩ አገሮች የንግድ ምክር ቤቶች እንዲሁም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ንግድና ኢንቨስትመንትን ከሚያስፋፋ አካላት ጋር የሥራ ግንኙነት ያደርጋል፣ የንግድ ትርዒቶች፣ ባዛሮችና ሌሎች ትዕይንቶችን በአገር አቀፍና ሚኒስቴሩን በማስፈቀድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በውጭ አገሮች ያዘጋጃል፣ ይሳተፋል፣ ያስተባብራል፡፡ የንግድ ዕቃዎች አገልግሎቶችና ሒደቶች የአመራር፣ የቴክኖሎጂና የጥራት ሽግግር እንዲኖራቸው ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር የሚሠራ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለግ ሥራም ለንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቱ ከተሰጡ ኃላፊነቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ‹‹ንግድ ነክ የጥናትና የምርምር ተግባራትን ያከናውናል፣ እንዲሁም ጥናቶችን መሠረት በማድረግ የኢኮኖሚ ስታስቲካዊ የገበያ መረጃዎችን የማደራጀት የመተንተንና የማሠራጨት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት መካከል የሚካሄደው የጋራ የምክክር መድረክ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመሆን የማዘጋጀትና የማስተባበር ሥራው ከተሰጡት ኃላፊነቶች ማካከል የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ ሌላው በዚህ ረቂቅ እንደ አዲስ የተሰጠው ሌላው ኃላፊነት በንግድ ሥራ ላይ ሕጋዊና ውጤታማ ሥራ የሚሠሩ ነጋዴዎችን በተዘጋጀ መሥፈርት በመለየት በሚኒስቴሩ የማበረታቻ ሽልማት እንዲሰጣቸው ማድረግ የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡ የንግዱን ማኅበረሰብ መብትና ጥቅም ያስከብራል፣ ግዴታውን እንዲወጣ የሚያበረታታ መሆኑን ጭምር ረቂቁ ያመለክታል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ብቻ እንደሚኖርም ያመለክታል፡፡