Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስት የቦርድ አባላትን ሾመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሥሩ ከሚገኙት የመንግሥት ኩባንያዎችና ልማት ድርጅቶች አንዱ ለሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስት አዳዲስ የቦርድ አባላትን ሾመ፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ የተሰየሙት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ነገራ፣ የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴና የመረጃ መረብ ደኅንነት አገልግሎት (INSA) ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ሀምድ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ ከነበሩት መካከል የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ይገኙበታል፡፡

አቶ ማሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባልነታቸውን ወዲያው የለቀቁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባላት ሹመት ምክንያቶች አንዱ በአቶ ማሞ ምትክ አዲስ የቦርድ አባል ለመሰየም ነው፡፡ 

ከአዲሶቹ ተሿሚዎች መካከል አቶ ወንድማገኝ ነገራ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በማገልገል የሚታወቁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ ምክትል ፕሬዚዳንት ደረጃ በኃላፊነት ያገለገሉ ናቸው፡፡

ከዚያም በኋላ አቶ ወንድምአገኝ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ አሁን ወዳሉበት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ተሾመዋል፡፡ የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ የገቢዎች ሚኒስቴር ከመሆናቸው ቀደም ብሎ በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለሁለት ዓመትም የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲም ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እንዳገለገሉም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ናቸው፡፡

ቀሪዎቹ በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዘጠኙ የቦርድ አባላት ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ኢንጂነር)፣ የፕላንና ኢኮኖሚ ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ያስሚን ዎሀብሪብ፣ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ አቶ አሕመድ ቱሳ፣ አቶ ነብዩ ሳሙኤል፣ አቶ አዲሱ ሀባ፣ አቶ ጌታቸው ነገራ እና ታዋቂው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሥሩ ለሚገኙ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የቦርድ አባላትን ጨምሮ የልማት ደርጅቶቹን ዋና ሥራ አስጻሚዎች የመሾምና የመሻር ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ ኢንቨስትመንት ሆልዲንጉ ደግሞ በቀጥታ ተጠሪነቱ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች