Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዳግም የሚካሄደው የቱርክ ፕሬዚዳንት ምርጫ

ዳግም የሚካሄደው የቱርክ ፕሬዚዳንት ምርጫ

ቀን:

በቱርክ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተጠናቀቀው ያለማንም አሸናፊነት ነው፡፡

ቱርክን ላለፉት 20 ዓመታት የመሯት ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ታይፕ ኤርዶሃንና ተቀናቃኛቸው ከማል ኪሊዳሮግሉ አንገት ለአንገት በተያያዙበትና ደጋፊዎቻቸውም ውጥረት ውስጥ በገቡበት ፕሬዚዳንዳዊ ምርጫ፣ ኤርዶሃን ከተቀናቃኛቸው ልቀው 49.4 በመቶ ድምፅ ቢያገኙም፣ በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት ለማሸነፍ 50 ሲደመር አንድ በመቶ ድምፅ ማስመዝገብ ባለመቻላቸው በመጀመርያው ዙር ምርጫ የፕሬዚዳንትነት መንበሩ ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

ተቀናቃኛቸው ከማል ኪሊዳሮግሉ 44.96 ከመቶ ድምፅ ያገኙ ሲሆን፣ የሁለቱም ተፎካካሪዎች ውጤት ለመሪነት የማያበቃ በመሆኑ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ዳግም ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑን የቱርክ ከፍተኛ የምርጫ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

የጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፓርቲ (ኤኬ) መሪና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን እንዲሁም የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ (ሲኤችፒ) መሪ ኪሊዳሮግሉ ዳግም እንዲካሄድ የተወሰነውን ምርጫ መቀበላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ኤርዶሃን ባለፈው እሑድ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በ20 ዓመታት የመሪነት ዘመናቸው ገጥሟቸው የማያውቅ ዓይነት ፈተና የገጠማቸው ሲሆን፣ ለዚህም በአገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ዋጋ መናር፣ የኢኮኖሚው መዳከም፣ ከሁለት ወራት በፊት የተከሰተውና የ50 ሺሕ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የመሬት መንቀጥቀጥና ፕሬዚዳንቱ ለዚህ የሰጡት ምላሽ አፋጣኝ አለመሆን በምክንያትነት ተነስቷል፡፡

በርካቶች ከሁለት ወራት በፊት በቱርክ ደቡብ ምሥራቅ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የኤርዶሃንን ዕውቅና ሸርሽሮታል ብለው ያምናሉ፡፡ በመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳ በአገሪቱ የግንባታ ሕግና ቁጥጥርን በማስፈጸም ረገድ ክፍተቶችን ችላ ብለዋል በማለት ሲተቹ የከረሙት ኤርዶሃን፣ በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ ለሞቱት ከ50 ሺሕ ለሚልቁ ሰዎች ኃላፊነት አለባቸው ሲባሉም ከርመዋል፡፡

የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው የደረሰው የእሳቸው ጠንካራ ደጋፊዎች ባሉበት ግዛት መሆኑና የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ ባለመሆኑ በደጋፊዎቻቸው ፊታቸውን ያዞሩባቸው አሉ የሚሉ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡

በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሥልጣን ከያዙ ወዲህ በመጀመርያው ዙር ከማሸነፍ ይልቅ ወደ ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንዲሄዱ ያስቻለ ውጤት ያስመዘገቡት ኤርዶሃን፣ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚያሸንፉ ተስፋ መሰነቃቸውም ተሰምቷል፡፡ ሆኖም ቀጣዩ ምርጫ የ20 ዓመታት የሥልጣን ወንበራቸውን የሚያሳጣና በቱርክ የፖለቲካ ሥርዓቱን የሚቀይር ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየትም ይሰነዘራል፡፡

ቱርካውያን በቀጥታ ፕሬዚዳንታቸውን ሲመርጡ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ኤርዶሃን ቀድሞ የበሩትን ሁለቱንም ምርጫዎች በመጀመርያው ዙር ነበር ያሸነፉት፡፡

በአሁኑ ምርጫ ሦስተኛው ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሲናን ኦጋን፣ 5.17 በመቶ ድምፅ በማግኘት ከ40 በመቶ በላይ የሚልቋቸውን ዕጩዎች እየተከተሉ ሲሆን፣ የሆምላንድ ፓርቲው ሙሃረም ደግሞ 0.44 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ሙሃረም ለምርጫው ሦስት ቀን አስቀድሞ ራሳቸውን ከውድድሩ ቢያገሉም፣ ምርጫው ውስጥ ተካተዋል፡፡

5.17 በመቶ ድምፅ ያገኙት የኤቲኤ አሊያንስ ፓርቲው ኦጋን፣ ምርጫው ዳግም እንዲካሄድ ያደረጉ ቁለፍ ሰው ናቸው ሲል ሲኤንኤን ይገልጻል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በኋላ በሚደረገው ምርጫም፣ የፓርላማውን ሥልጣን ለመቆናጠጥ እሳቸው የሚያደርጉት ጥምረት ወሳኝ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ማንም ይሁን ማን 600 መቀመጫ ያለው የቱርክ ፓርላማ፣ የሚፀናውም በጥምረት ነው፡፡

የቱርክ የዜና ወኪል እንዳስፈረም፣ የኤኬ ፓርቲ 266 መቀመጫዎችን ያገኘ ሲሆን፣ የሲኤችፒ ፓርቲ 166 መቀመጫ አግኝቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከሰባት አሠርታት በፊት የነበረው የአርሲ አለባበስ የአርሲ ሴቶች ከልጆቻቸው ጋር...

ይቅርብኝ!  

ዓይኔ አይይ ይቅርብኝ ማየቴ ካልረዳኝ፣ የመጥፎ ድርጊት ጦር ጨረሩ ከጐዳኝ፡፡ አላውራ...

ለድሀ በእውነት የሚፈርድ

በእውቀቱ ሥዩም አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ቦሌ መድኃኔዓለም እሚገርመኝ ሰፈር...

ተፈጥሯዊው መምህር

ችግር ተፈጥሮአዊ መመህር ነው፡፡ ችግር የታላቅ ህይወት በር ነው፡፡...