አትሌቲክስ ባለበት ሁሉ የሁለቱ ከተሞች ስም ሳይነሳ አልፎ አያውቅም። በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከተደረጉ የረዥም ርቀት ውድድሮች ከእነዚህ ትንንሽ የምሥራቅ አፍሪካ ከተሞች የተገኙ አትሌቶች ከ80 በመቶ በላይ በመቶ ይሸፍናሉ።
እነዚህም ከተሞች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የምትገኘው በቆጂና የኬንያዋ ኤልዶሬት ከተማ ናቸው። ከሁለቱ ከተሞች የተገኙት አትሌቶች ለአትሌቲክሱ ያበረከቱት አስተዋኦ የጎላ ነው።
ሁለቱ ከተሞች በተፈጥሮ መልክዓ ምድር የታደሉ መሆናቸውና አትሌቶቹ በገጠራማ ሥፍራ ማደጋቸው፣ በዓለም አደባባይ ደምቀው እንዲወጡ ምክንያት መሆኑ ይነገራል። አትሌቶች ከትውልድ ቀዬአቸው ተነስተው ወደ ትምህርት ቤት ለማቅናት ረዥም ኪሎ ሜትሮችን በሶምሶማ ማቅናት የዕለት ከዕለት ሥራቸው መሆኑና የከተሞቹ ከመሬት ወለል በላይ 2,800 ሜትር ከፍ ያለ ቦታ መቀመጣቸው፣ አትሌቶቹ በተለያዩ ውድድሮች የበላይነት እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል።
በዚህም መሠረት በቆጂ ብቻዋን በፋጡማ ሮባ በማራቶን ወርቅ፣ በጥሩነሽ ዲባባ ሁለት የኦሊምፒክ ወርቅ፣ ቀነኒሳ በቀለ ሁለት ወርቅ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሻምፒዮናዎች በርካታ ሜዳሊያዎች ለአገር ማበርከት የቻሉ አትሌቶችን ማፍራት ችላለች። በቆጂ፣ በበርካታ የልምምድ ቦታዎች የታደለች በመሆኗ፣ በከተማዋ ቱታ ታጥቆ በየጫካው የሚሮጥ መመልከት የተለመደ ነው። የአብዛኛው አትሌት አሠልጣኝ የሆኑት አቶ ስንታየሁ እሸቱ ፊሽካቸውን በአፋቸው ይዘው ያሠለጠኗቸው በርካቶች ነበሩ።
በአንፃሩ ከተማዋ ያሏት የመለማመጃ ሜዳዎች ለነዋሪው መኖሪያ ቤት ሥፍራ እየተላለፉ በመሰጠታቸውና አማራጭ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች አለመኖራቸው፣ ለስፖርቱ ትኩረት አለመስጠት አትሌቲክስ በነበር እየቀረ መሄዱ ይነገራል። ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ጎብኚዎች ወደ አትሌቲክስ መፍለቂያዋ ከተማ እየመጡ ሲጎበኟት የነበረው የማዘወትሪያ ሥፍራ ለሌላ ዓላማ እንዲውል ተደርጓል።
በከተማዋ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ቢኖርም መሠረታዊ ጉዳዮች ያልተሟሉለት፣ እንዲያው ለይስሙላ የተቀመጠ መሆኑን ሪፖርተር በከተማዋ ባደረገው ቅኝት መመልከት ችሏል። በርካታ ታዳጊዎች በሩጫው የታላላቆቻቸውን ፈለግ ለመከተል ሲዳክሩ ይስተዋላል።
ምንም እንኳ ከተማዋ አገራቸውን በዓለም አደባባይ ስም ያስጠሩና ገድል ያደረጉ አትሌቶች ማፍራት ብትችልም፣ ከመንግሥት ትኩረት ባለማግኘቷ በፈራቻቸው አትሌቶች ጭምር መዘንጋቷን የከተማዋ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ። እንደ ነዋሪዎች አስተያየት ከሆነ ከተማዋ ያፈራቻቸው አትሌቶች በኢንቨስትመንቱ መሠማራት ባይችሉ እንኳን፣ ተተኪዎች የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ ወደ ከተማዋ መጥተው ማበረታታት አለመቻላቸው ያስተቻቸዋል።
በአንፃሩ በኬንያ የምትገኘው የኤልዶሬት ከተማ ዛሬም እንደ ትናንቱ በአትሌቶች የታጨቀች መሆኗ ይነገራል። በከተማ ከታዳጊ እስከ አዋቂ አትሌቶች ትዘወተራለች። የበርካታ ሻምፒዮኖች መናኸሪያ መሆኗ ይነገራል። በአገሪቱ ካሉ አትሌቶች በዘለለ፣ የተለያዩ አገሮች አትሌቶች መኖሪያቸውን በከተማዋ አድርገው ልምምዳቸውን ያደርጋሉ። አገሪቱ አትሌቲክሱ ያለውን አቅም በመረዳት እያስፋፋችው ከመሄዷም ባሻገር፣ ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ አድርጋ እየሠራች እንድምትገኝ ይገለጻል።
ኤልዶሬት የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቱን ኤሉድ ኪፕቾጌን ጨምሮ በርካታ የኬንያ ሻምፒዮኖችን ያፈራች ከተማ በመሆኗ ለረዥም ርቀትና ለመካከለኛ ርቀት የሚያገለግል 10 ሺሕ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየም ገንብታለች። የዓለም አትሌቲክስ በኤልዶሬት ሁለት ዘመናዊ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላትን ገንብቷል። ከዚህም ባሻገር እ.ኤ.አ. ከ2019 ጀምሮ በኤልዶሬት ከተማ የሚስተናገድ የማራቶን ውድድር ሲኖር 35,000 ዶላር ሽልማት አለው። በኬንያ የአትሌቶች መፍለቂያ ዓለም አቀፍ የትጥቅ አምራቾች፣ ማናጀሮች፣ የአትሌቲክስ አማካሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት መሰብሰቢያ ከሆነች ሰንብታለች።
ምንም እንኳ በቆጂና ኤልዶሬት በአትሌቲክሱ ያበረከቱት ስማቸው የጎላ ቢሆንም በቆጂ በነበረችበት ቆማለች። በዚህም ምክንያት ከተማዋ ወደ ነበረችበት ዝና እንድትመለስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዓመታዊ የሩጫ ውድድር በበቆጂ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ አካሂዷል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኤልዶሬት ከተማ ጋር የመግባቢያ ሰንድ ተፈራረርሞ በበቆጂ ታላቁ ሩጫ ያሸነፉ አትሌቶች በኤልዶሬት እንዲሳተፉ እንዲሁም በኤልዶሬት የማራቶን ውድድር የተሳተፉ አትሌቶች በበቆጂ ታላቁ ሩጫ እንዲካፈሉ ተደርጓል።
ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የተከናወነው የታላቁ ሩጫ፣ በኤልዶሬት የከተማው ሕዝብ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ክለብ አትሌቶች እንዲሁም ከኬንያ ኤልዶሬት የመጡ አትሌቶች ተካፋይ ነበሩ። 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ውድድሩ ከ1,200 በላይ ተሳትፈውበታል።
ውድድሩ የታዳጊዎችን ጭምር ያካተተ ሲሆን፣ ተራራ ላይ የመውጣት መርሐ ግብርንም አካቷል፡፡ በዓመታዊ ውድድሩ ከተማዋ በአትሌቲክሱ ዳግም እንድታንሰራራ ከማስቻሉም በላይ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መታቀዱን የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ ተናግረዋል።