Wednesday, June 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰላም የሚሰፍነው ቅራኔን በማስወገድ እንጂ በማባባስ አይደለም!

ሕዝብና መንግሥት ለአገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት በጋራ ሲሠሩ ቅያሜም ሆነ ቅራኔ የሚፈጠርበት ዕድል የጠበበ ይሆናል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ግን ሆድና ጀርባ ሲሆኑ ቅያሜ እየጨመረ ወደ ቅራኔ ያድጋል፡፡ ቅራኔ እየሰፋና ገጽታውን እየቀየረ ሲሄድ ለተቃውሞ ያነሳሳል፡፡ ተቃውሞው እየበረታና አድማሱን ሲያሰፋ ደግሞ ለሁከትና ለብጥብጥ ይዳርጋል፡፡ ሁከትና ብጥብጥ መፍትሔ የሚያጣበት ደረጃ ሲደርስ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ነውጥ ይፈጠርና ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ ግጭቱ እያደገ ሲቀጥል ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያመራል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከየአቅጣጫው የሚሰሙ የቅሬታ ድምፆች መልካቸውን እየለወጡ፣ አገርና ሕዝብን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ምልክቶች ከመጠን በላይ እየታዩ ነው፡፡ ይህንን ሥጋት ያጠላበት አስፈሪ ድባድ፣ ‹‹ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል›› የሚባለውን አሰልቺ ተረት የሚያስተርት አይደለም፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራት በከበደበት፣ በሰላም ወጥቶ መግባት አስተማማኝ ባልሆነበት፣ የኑሮ ውድነት ባልተቻለበት፣ በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ ጎጆዋቸው የፈረሰባቸው ወገኖች እሪታ በሚያስተጋባበትና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች በበዙበት ሁኔታ ውስጥ ነገሮች እየከበዱ ነው፡፡

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አብላጫውን ድምፅ በማግኘት ሥልጣን የያዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት፣ እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በቅደም ተከተል መፍትሔ ለመስጠት ከሕዝብ ጋር በቀጥታ መነጋገር አለበት፡፡ ሕዝብ በበርካታ ጉዳዮች እየደረሱበት ያሉትን ምሬቶች አፍረጥርጦ ተናግሮ የመፍትሔ አካል እንዲሆን ይደረግ፡፡ ወረዳ ከሚባለው ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ጀምሮ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ምሬት የሚፈጥሩ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ የሕዝብን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት የተሳናቸው ሹማምንት ሕዝቡን በጉቦ አቅሉን እያሳቱት ነው፡፡ ከነዋሪነት መታወቂያ ጀምሮ ሌሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶች ያለ እጅ መንሻ መፈጸም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድና በመሳሰሉት ዘርፎች በሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ምክንያት ዜጎች ለፍተው ባገኙት ገንዘብ የቀለሱት ጎጆ ሲፈርስባቸው ተጠያቂ የለም፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ የሚፈለግበትን ግብር በአግባቡ እየከፈለ ጥቂቶች ተሰውረው በሀብት ላይ ሀብት እያከማቹ በሚከብሩባት አገር ውስጥ፣ ቅራኔው ከመጠን በላይ ቢጦዝ ሊገርም አይገባም፡፡

ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ከምርጫው በኋላ ከትግራይ ክልል በስተቀር በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሕዝብ ጋር ያደረገው ውይይት ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከሕዝብ ከተነሱለት ጥያቄዎች በተጨማሪ ለመፍትሔ የሚረዱ ምክረ ሐሳቦች መቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ ከውይይቶቹ በኋላ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ከሕዝብ ጋር ያደረጉት ምክክር ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበር በየተራ መናገራቸውም እንዲሁ፡፡ ይሁንና ለጥያቄዎቹ የተሰጠው ተግባራዊ ምላሽ ምን ያህል ነው ቢባል እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች ወደ ተግባር ለመቀየር የረባ እንቅስቃሴም አልታየም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሰው በመንግሥት ኦፊሴላዊና በፓርቲ ቁጥጥር ሥር ባሉ ሚዲያዎች የሚቀርቡትን ብሶቶች ማስተዋል ይቻላል፡፡ ሕዝቡ በየደረሰባቸው አገልግሎት መስጫ ተቋማት መስተናገድ ተስኖት በአደባባይ ቅሬታውን እየገለጸ ነው፡፡ የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘትና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስተናገድ ጉቦ አምጡ ተባልን የሚለው አቤቱታ የተለመደ ሆኗል፡፡ ችግሮችን ከሚፈታ ሹም ይልቅ የሚያባብስ ተፈቶ የተለቀቀ ነው የሚመስለው፡፡ የመንግሥት ያለህ ተብሎ ጩኸቱ በየአቅጣጫው ሲያስተጋባ አዳማጭ የለም፡፡

በርካታ ዜጎች ጎጆአቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ እንዳይወድቁ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕጋዊ ያልሆኑ ቤቶችን የገነቡ ወገኖች ጭምር ሥርዓት ባለው መንገድ ችግራቸው መታየት አለበት፡፡ እነሱ ቤቶቹን በገነቡበት ወቅት ካርታና ሕጋዊ የግንባታ ፈቃድ የሰጡ የመስተዳደር አካላት ሳይጠየቁ፣ ሕግ ለማስከበር በሚል ሰበብ በዜጎች ላይ የጭካኔ ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በመንግሥት መዋቅሮች አማካይነት የመሥሪያ ቦታ የተሰጣቸው ወገኖች፣ ምትክ የመሥሪያ ቦታ ሳያገኙ ሥራ አጥ እንዲሆኑ ማድረግ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ በሸራ የተወጠሩም ሆኑ በኮንቴይነር የተሠሩ የዕለት እንጀራ ማግኛ ቦታዎች ለከተማው ውበት ተብሎ እንዲነሱ ሲደረግ፣ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ ሰው ተኮር ካልሆነ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ከመኖሪያቸውም ሆነ ከመሥሪያ ቦታቸው የሚፈናቀሉ ወገኖችን ቀርቦ ችግራቸውን የመፍታት ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የከተማ አስተዳደሮችም ሆኑ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ አመራሮች ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን ግዴታ ሳይወጡ የትኛውን ሕዝብ ነው እናገለግላለን የሚሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሰሞኑን በክረምት በጎ ፈቃድ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች ዕድሳት ማስጀመራቸው ታይቷል፡፡ ችግረኞችን በሕዝብና በባለሀብቶች ዕገዛ ለመታደግ እንቅስቃሴ ሲኖር መልካም በመሆኑ ድጋፍ ይቸረዋል፡፡ ተግባሩም ሰው ተኮር ስለሆነ ያስመሠግናል፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ ከተማን ውብ ለማድረግ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችም ሰው ተኮር እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ቀና ልቦና የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ሲኖሩ ባለቤትነታቸው የሕዝብ ይሆናል፡፡ ዜጎች ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚ የመሆናቸው ጉዳይም በሁሉም ወገኖች ዘንድ መግባባት ይፈጥራል፡፡ ከዚያ ውጪ በድንገት በሚወሰዱ ግብታዊ ዕርምጃዎች ምክንያት የሚፈጠሩ ቅሬታዎችና ቅራኔዎች የተሠራውን መልካም ነገር እንዳልተሠራ ከማድረግ በዘለለ፣ አገራዊ መግባባት እንዳይፈጠርና ቀውስ እንዲበራከት የራሳቸውን አሉታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ መንግሥት ሥራውን ሲያከናውን ሁሉንም ወገን በአንድ ጊዜ ማስደሰትም ሆነ ማስከፋት አይቻለውም፡፡ ነገር ግን ሥራዎቹ ሁሉ ከአድሎአዊነትና ከኢፍትሐዊነት የራቁ እንዲሆኑ ማድረግ ግዴታው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክሩ መሆን ያለበት ሕዝብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ግጭትም ሆነ የግጭት ወሬ ሰልችቶታል፡፡ ይህ ሕግ አክባሪና ትሁት ሕዝብ የሚመጥነው አመራር ይፈልጋል፡፡ አመራሩ በዕውቀት፣ በልምድና በሥነ ምግባር የተገራና አገር ወዳድ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከአገር በፊት የራሱንና የቢጤዎቹን ጥቅም የሚያስቀድምና ለአገር ዕድገትና ህልውና የማይገደው፣ ሕዝብን በታማኝነትና በቅንነት ያገለግላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሕዝባቸውንና አገራቸውን በሙሉ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ያሉትን ያህል፣ በብሔርና በጥቅም እየተሳሳቡ ዝርፊያና ውንብድና ውስጥ የተሰማሩ በብዛት አሉ፡፡ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ብቻ ሕዝብን እያስለቀሱ የሚያፌዙ በመብዛታቸው፣ ኢትዮጵያ የቅራኔ መፈልፈያና ማከማቻ ሆና ንፁኃን ያለ ጥፋታቸው እየተጎዱ ነው፡፡ ከትናንት ስህተቶች መማር የተሳናቸው በዚያው የስህተት ጎዳና ላይ እየተመላለሱ ለሰላም መስፈን ጠንቅ እየሆኑ ነው፡፡ በጣም ቢዘገይም ከመቅረት ይሻላልና ቆም ብሎ አስቦ ድርጊትን ማስተካከል ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየሆኑ ባሉ አስከፊ ድርጊቶች ምክንያቶች ብዙዎች እያለቀሱ ነው፡፡ ይህ ሐዘንና እሮሮ ይዞት የሚመጣው መዘዝ አስከፊ ሊሆን ስለሚችል፣ ቅራኔን በማስወገድ ሰላም ማስፈን ይበጃል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...