የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ውስጥ፣ ለብልፅግና የክልል ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ድጋፍ መሰጠቱ ተጠቅሶ መቅረቡ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 19ኛው መደበኛ ስብሰባ፣ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ለክልል ፓርቲ አመራሮች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በቀረበው ሪፖርት የተነሳው ጉዳይ የፓርቲና የመንግሥትን ጎራ መደበላለቅ የታየበት መሆኑን ማብራሪያ የጠየቁት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጭና የምክር ቤቱ የአማካሪ ኮሚቴ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
የሥነ ሥርዓት ጥያቄ በማለት አፈ ጉባዔው ዕድል እንዲሰጧቸው የጠየቁት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሚኒስትሯ እንደ ዋና ግባቸው አድርገው ከያዙት ተግባር ውስጥ ለክልል ፓርቲ ጽሕፈት ቤቶች የአቅም ግንባታ መስጠት ተብሎ በሪፖርታቸው ተካቷል፡፡ ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል? አንዴ መነሳቱ ስህተት መስሎኝ ነበር፡፡ ሪፖርቱ ውስጥ ግን ሁለትና ሦስት ጊዜ ነው የተጠቀሰው፡፡ አንደኛ በሚኒስቴሩ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አሉ፡፡ ሁለተኛ በአንፃራዊነት ወጣት አመራሮች ባሉበት ተቋም ውስጥ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ ቀላቅሎ የመሥራት ባህላችን አልቀረም ወይ?›› በማለት አክለው ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም አፈ ጉባዔው በዚህ ጉዳይ ላይ ዕርምት እንዲሰጡና ሚኒስትሯም ምክር ቤቱንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ በማለት አስተያየት አቅርበው ነበር፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለተነሳው ሐሳብ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ምክር ቤታችን በአሠራር ሥርዓትና ደንብ ነው የሚመራው፡፡ ማንም አባል የሥነ ሥርዓት ጥያቄ አለኝ ብሎ ካሰበና ካመነበት ሐሳብ ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ 6/2008 የትኛው ሕግ ነው የተጣሰው የሚለውን ማመላከት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በአቋራጭ ገብቶ ሌላ ጥያቄ ማቅረብ ሌላ የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ስለሚያመጣ ደሳለኝ (ዶ/ር) ያነሱት ሐሳብ በዚህ መሠረት መታረም አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በሁለተኛ ዙር ተጨማሪ ጥያቄ ያቀረቡት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ በምክር ቤቱ የአሠራርና የሥነ ሥርዓት ደንብ ውስጥ ተብራርቶ በግልጽ ባለመቀመጡ የፓርቲና የመንግሥት ሥራ ተቀላቅሎ ሲቀርብ ምክር ቤቱ ዝም ብሎ ይቀበላል፣ ወይም አስተያየት ሳይሰጥ ያልፋል ማለት አለመሆኑን ገልጸው ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ‹‹እኔ እዚህ ላይ ማስተካከያ ሳይሆን ምክር የምሰጠው ደሳለኝ (ዶ/ር) ደንቡን እንዲያነቡና የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ሲያቀርቡ አንቀጽ እንዲጠቅሱ አሳስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ተወዳድሮ አሸንፎና አብላጫ ድምፅ አግኝቶ እየመራ ያለ በመሆኑ፣ ሥራችንን ለመደገፍ አንዴ አይደለም በጣም በርካታ ጊዜ ማሠልጠን ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ለሕዝብ የገባነውን ቃል ለማሳካት ይህን ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በፍፁም ከመንግሥትና ከፓርቲ ሥራ መደበላለቅ ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ በቀጣይም ይህንን አጠናክረን እየሠራን እንቀጥላለን፤›› ሲሉ አሰታውቀዋል፡፡