በሪል ስቴትና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራው ፍሊንትስቶን ሆምስ ኩባንያ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አሥር ሚሊዮን አክሲዮኖችን ለሕዝብ ክፍት በሆነ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የሽያጭ መጠኑን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የኩባንያው መሥራች ፀደቀ ይሁኔ (ኢንጂነር)፣ የአክሲዮን ባለቤትነት ከ20 ሺሕ ብር የማያንስ ከሁለት ሚሊዮን ብር የማይበልጥ እንደሆነና የአንድ አክሲዮን ዋጋ ደግሞ አንድ ሺሕ ብር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለሽያጭ የቀረበው አነስተኛ የአክሲዮን መጠን 20 ሺሕ ብር ከፍተኛው ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር የሆነበት ምክንያት፣ ብዙኃኑን ማሳመንና ማርካት የሚያስችል ኩባንያ እንዲሆን ታቅዶ ነው ብለዋል፡፡
ፍሊንትስቶን ሆምስ ኩባንያ የአክሲዮን ሽያጭ ለሕዝብ ክፍት በሆነ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱ የተገለጸው፣ የኩባንያው መሥራች ፀደቀ (ኢንጂነር) ከአምስት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
ከአክሲዮኖቹ ሽያጭ ምን ያህል ገቢ ለመሰብሰብ እንደታቀደ እንዲያስረዱ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ፀደቀ (ኢንጂነር)፣ አምስት ቢሊዮን ብር ለማግኘት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኩባንያውን አሁን ካለበት ደረጃ ያደረሱትን አመራሮች ቦታ የሚያሳጣ የአክሲዮን ግብይት መልሶ ድርጅቱን ለአደጋ አያጋልጥም ወይ ለሚለው ጥያቄም፣ ሥጋቱ ተገቢ ቢሆንም በአመራሩ ብርታት በመተማመን በቅድሚያ አክሲዮን የሚገዙ ሰዎች በተተኪው አመራር አዲስ ሐሳብ፣ ጉብዝና፣ በሒደት ብዙኃንን የሚወክል አዲስ አመራር እያበጁለት እንደሚሄዱ ስለሚገመት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአንድ ግለሰብ በስድስት ሺሕ ብር ካፒታል የተጀመረ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዋጋ ያላቸው ሥራዎችን መሥራት ከቻለ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ገንዘብና በጎ አስተዳደር የበለጠ ዘመን ተሻጋሪ ከፍተኛ ሥራ ማከናወን ያስችላል የሚል ተስፋ እንደተጣለበትም ገልጸዋል፡፡
የአክሲዮን ሽያጩ ያስፈለገው በዋናነት ድርጅቱን ከአምስት ሰዎች የሽርክና ባለቤትነት ወደ ሕዝብ ንብረት ለመለወጥ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ካፒታል ለማግኘት ነው ተብሏል፡፡ ኩባንያው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አሥር ሺሕ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እንዳቀደም ተመላክቷል፡፡
ፊሊንትስቶን ሆምስ በተለያዩ ክልሎች ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚገኝ ፀደቀ (ኢንጂነር) ጠቁመዋል፡፡ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በሥራቸው ላይ ምን ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳደረሰባቸው ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በክልል ከተሞችና በገጠራማ አካባቢዎች የሪል ስቴት ግንባታ ለማስፋፋት የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች በተለይ በገጠር ከተሞች የሪል ስቴት ግንባታ ለማስፋፋት ዕቅድ እንደነበራቸው የገለጹት ፀደቀ (ኢንጂነር)፣ የፀጥታው ችግር ዕቅዳቸውን እንዳያሳኩ ቢያደርጋቸውም ሰላም ሲሰፍን ዕቅዳቸውን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ቤቶችን ገንብተው በወቅቱ እንደሚያስረክቡ ደንበኞች በተደጋጋሚ የሚያነሱትን ቅሬታ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸው ፀደቀ (ኢንጂነር)፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት የገነቧቸው ቤቶች በወቅቱ ለደንበኞች ያልደረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለመጓተቱ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ደግሞ ገንዘብ ተቆጥቦ የሚሠራ ቤት ጊዜ ስለሚፈጅ፣ ኩባንያው ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ስለሚገጥመውና የሲሚንቶና የብረት ዋጋ መናር መሆናቸው አስረድተዋል፡፡
የአክሲዮን ሽያጭ ለማቅረብ የታቀደውም በተለይ በፋይናንስ ችግር የሚጓተተውን የቤቶች ግንባታ ችግር ለመቅረፍና ለደንበኞች በወቅቱ ለማስረከብ ታልሞ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ኩባንያው የተቋቋመው በ1984 ዓ.ም. እንደሆነ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ ተቋራጭነት ሲሠራ ቆይቶ ከ15 ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቤቶች ገበያን እንደተቀላቀለ፣ በዚህም ሱቆችን ጨምሮ አምስት ሺሕ ቤቶችን ለደንበኞች እንዳስረከበ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው 3,500 ያህል ቤቶች በግንባታ ሒደት ላይ እንዳሉት፣ 6,500 የሚሆኑ ቤቶች ደግሞ ግንባታቸው ተጠናቆ ለገበያ ሊቀርቡ እንደሆነ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአጠቃላይ አሥር ሺሕ ቤቶችን ለደንበኞች ለማስረከብ መታቀዱን ፀደቀ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡