የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ስለ ሕወሓት የሰጠው ውሳኔ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የገለጸው ሕወሓት፣ወሳኔው በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ተቃኝቶ እንዲስተካከል ጥያቄ አቀረበ።
ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወ.ሓ.ት) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ያስተላለፈውን ውሳኔ ዳግም በማጤን፣ የሕወሓት ህጋዊ ሰውነት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ ድርጅቱና ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንዲችሉ፣ የተወረሱ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲመለሱ ጥያቄ ማቅረቡን ትናንት ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውሷል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ያስተላለፈው ዉሳኔ በኤለክትሮኒክስ ሚድያ የተገለፀ ቢሆንም ለድርጅቱ የተሰጠበት ቀን ግን ግንቦት 07 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑን ጠቁሟል።
በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ቅቡልነት የሌለው፣ በፕሪቶርያ የተደረሰውን ስምምነትና ህግን መሰረት ያላደረገ መሆኑ መገንዘቡንም በመግለጫው ጠቁሟል።
ሕ.ወ.ሓ.ት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየውን አፋኝ ስርዓት በመገርሰስ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩና ታሪካቸው እንዲያሳድጉ የሚያስችል ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲረጋገጥ በማድረግ በኩል ደማቅ ኣሻራ ያለው ኣንጋፋ ድርጅት መሆኑ ጠቁሞ፣ከቅርብ ኣመታት ወዲህ ግን የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ ፣ዲሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ መንገድ መፈታት ባለመቻሉ በ2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ደም አፋሳሽ ግጭት ተፈጥሮ እስከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወራቶች ድረስ መዝለቁን አብራርቷል።
ይህን ደም አፋሳሽ እልቂት በተቻለ መልኩ ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶችን ሲደረግ ቆይቶ በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ እና በአሜሪካን መንግስት አሸማጋይነት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካና በኬንያ መንግስታት አመቻችነት ከፌደራል መንግስቱ ጋር ድርድር ተደርጎ እአአ ሕዳር 23 ቀን 2022 በፕሪቶሪያ ከተማ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊፈረም መቻሉን አስታውሷል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት በመሰረታዊነት ማዕከል ያደረገው : ሰላም፣ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ተጠያቂነት እና ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መመለስ ነው። ከስምምነቱ መፈረም ጀምሮም ሕወ.ሓ.ትና ኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት በጋራና በተናጠል የገቡትን ግዴታና የስምምነቱን ዓላማዎች እየፈፀሙ ይገኛሉ።
ለዚህም አበረታች የሚባል ውጤትና ለቀጣይ ስራዎች ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣቱ ስምምነቱ ዓለም አቀፍዊ እና አገራዊ እውቅና ተሰጥቶታል። የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተለያዩ አገራት መንግስታት እውቅና እና ድጋፋቸውን ሰጥተውታል።
በሌላ በኩል የፌደራሉ መንግስት ህግ አውጪ አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. : ጠቅላይ ኣቃቢ ሕግ፣ የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮች ለስምምነቱ እውቅናና ድጋፍ የሰጡ ህገ-መንግስታዊ አካላት ናቸው ብሏል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ድርጅቱን ከአሸባሪነት ስያሜ የመሰረዝ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ ኣስተዳደር እንዲመሰረት በፕሪቶርያው ስምምነቱ አንቀፅ 10(1) በተገደነገገው መሰረት የትግራይ ኣካታች ጊዜያዊ ኣስተዳደር በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ተመስርቷል” የፕሪቶሪያው ስምምነት ዓላማ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ክልሉን እና የክልሉን ህዝብ ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መመለስ ነው።
በዚህም መሰረት የስምምነቱ ይዘት ተፈፃሚ እንዲሆን የትግራይ ህዝብና ድርጅታችን ህወሓት እንዲሁም ሃላፊነት ያላቸው የፌደራል መንግስት አካላት ግዴታቸውን ሊወጡ የሚገባ ቢሆንም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን የድርጅታችን ህጋዊ ሰውነት የመሰረዝ ውሳኔ እንዲነሳ የቀረበለትን ጥያቄ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የተሰረዘ የፖለቲካ ፓርቲ ተመልሶ ህጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት ድንጋጌ ስለሌለ የድርጅታችን ህጋዊ ሰውነት ሊመለስ እንደማይቻል ከፕሪቶርያ ስምምነት ውጪ በሆነ መንገድ ውሳኔውን እንዳሳወቀው ሕወሓት በመግለጫው ተናግሯል።
በቦርዱ የተላለለፈውን ውሳኔ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የማይቀበል፣ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነት ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ከጦርነቱ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ለሚገቡ ሃይሎች መደገፍ እና ማበረታታት ሲገባ ድርጅቶችን በማፍረስ ቀጣይ ሰላም እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ መሆኑ፣ ለህዝቦቻችን የማይመች እና ለሌሎች ሃይሎችም ተስፋ የማይሰጥ ነው ብሎ ሕወሓት እንደሚያምን አስታውቋል።
በኣጠቃላይ ሕወሓት ውሳኔውን እንደማይቀበለው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይበት ፣ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንደገና በማየት የፕሪቶርያ ስምምነትና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያስተላለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ እንዲያስተካክል ይጠይቋል፡፡
“የሰላም ስምምነቱ ባለቤት የሆናችሁ መላው የድርጅታችን ኣባላት፣ የትግራይ ህዝብና ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህንን ውሳኔ የሰላም ሂደቱ ኣደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ ተገንዝባችሁ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ድርጅታችን ህ.ወ.ሓ.ት ጥሪውን ያቀርብላችኋል” ብሏል።
የፌደራል መንግስትም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ በተጀመሩት አወንታዊ የሰላም እና የመደጋገፍ ጥረቶች ላይ ሊያሳድረው የሚችል አላስፈላጊ ጫና እንዲሁም የፌደራል መንግስቲ ህጋዊ ውሳኔዎችንና ሓርነት ትግራይ ስምምነቶች በሁሉም የመንግስት ተቋማት እና አካላት እንዲከበሩ የማድረግ ሀላፊቱን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቦርዱ ውሳኔ እንደገና ታይቶ ከሕ.ወ.ሓ.ት ህጋዊ ሰውነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉትን ህጋዊና ፖለቲካዊ አማራጮች ተጠቅሞ ነገሮች ቅድመ-ጦርነት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ በማያደርግ ቀና አካሄድ እንዲፈቱ፣ የፕሪቶርያ ስምምነት በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እንዲደረግ እና የተጀመረውን የሰላም ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲሳካ “ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ የነበራችሁ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት፣ በተለይ ሂደቱን የሚያደናቅፍ እና አደጋ ውስጥ የሚከት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ተቃኝቶ እንዲስተካከል የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን” ብሏል።