Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሰሞኑ ትኩሳት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ

የሰሞኑ ትኩሳት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ

ቀን:

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አኗኗር እያንኮታኮተ ይገኛል፡፡ ኑሮው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ዜጎች ብቻ ሳይሆን፣ በመካከለኛ ደረጃ ለሚገኙትም ቢሆን ፈታኝ ሆኗል፡፡

የሸቀጣ ሸቀጦችም ሆነ የቤት ኪራይ ክፍያ አቅም በሚፈትንበት በዚህ ወቅት፣ በመንግሥት በኩል ይህ ነው የሚባል የደመወዝ ማሻሻያ አለመደረጉ አብዛኛውን የመንግሥት ሠራተኞች ችግር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡

ችግሩ ለመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን በግል ድርጅት ተቀጥረው ለሚሠሩት፣ ለቤትና ለተለያዩ አገልግሎቶች በየመሥሪያ ቤታቸው ድጎማ ለማያገኙትም ተመሳሳይ ነው፡፡  

የብዙኃኑ ገቢ ባልጨመረበት በዚህ ወቅት በአብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ እንዲደረግ ሐሳብ መቅረቡ ወላጆች ቅሬታ እንዲያነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከሁሉም በላይ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን ክፍያ መጨመር የሚችሉት ከወላጆች ጋር መክረው መሆኑንና ትምህርት ሚኒስቴርም ነፃ ገበያ በሚል ዕሳቤ ጭማሪን በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጠው ገደብ አለመኖሩ፣ የግል ትምህርት ቤቶች እነሱ በሚያዋጣቸው መንገድ ብቻ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ዕድል ሰጥቷል፡፡

ለ2016 የትምህርት ዘመን አብዛኛው የግል ትምህርት ቤቶች ከወላጆች፣ ከወላጆች ኮሚቴ ጋር መክረናል በሚል የጭማሪ መጠናቸውን እያሳወቁም ነው፡፡

የቀጣይ የትምህርት ዘመን የትምህርት ክፍያ ጭማሪን አስመልክቶ በርካታ ወላጆች ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን፣ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተደረጉ ስብሰባዎች ባለመግባባት ተበትነዋል፡፡

ባልተገባው ጭማሪ ላይ ቅሬታ ካሰሙት ወላጆች መካከል አቶ ዘካሪያስ ሙሉጌታ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ዘካሪያስ ሁለት ልጆቻቸውን በሳውዝ ዌስት አካዴሚ ማስተማር ከጀመሩ ስድስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በትምህርት ቤቱም ልጆቻቸውን ማስተማር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ለትምህርት ክፍያ ጭማሪ እንደሚደረግ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሁለት ልጆቻቸው ምንም ሳይጎድልባቸው የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ቀን ከሌሊት እንደሚሠሩ የሚናገሩት አቶ ዘካሪያስ፣ በጊዜ ሒደት ግን የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ክፍያ ብቻ ሳይሆን፣ የቤት ኪራይ እንኳን ለመክፈል መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ልጆቻቸውን ለማስተማር ቀርቶ የዕለት ጉሳቸውን ለመሙላት እንደከበዳቸው ያስረዳሉ፡፡

አንደኛው ልጃቸው የስድስተኛ ክፍል፣ ሌላው ደግሞ አምስተኛ ክፍል ተማሪ መሆናቸውን፣ ለሁለቱ በየተርሙ የሚከፈለው ተመሳሳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እስካሁን ለእያንዳንዳቸው በአንድ ወር 2,500 ብር እንደሚከፍሉ የተናገሩት እኚህ አባት፣ ለ2016 የትምህርት ዘመን በፊት ከሚከፍሉት የክፍያ መጠን ከፍተኛ ጭማሪ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ የ2016 የትምህርት ዘመንን አስመልክቶ ባደረገው ጭማሪ አብዛኛው ወላጆች አለመስማማታቸውን፣ ነገር ግን መንግሥት ይህንን በተመለከተ ምንም ዓይነት መመርያ ባለማስቀመጡ ወላጆች ጭማሪውን ለመክፈል እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡    

የመምህራን ክፍያ፣ የቤት ኪራይና የሌሎች ግብዓቶች ዋጋ መናር ትምህርት ቤቶች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን፣ ነገር ግን በአንድ ጊዜ 32 በመቶ ያህል ጭማሪ አድርጉ ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በአብዛኛው በግል ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ወላጆች መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ናቸው የሚሉት እኚህ አባት፣ መንግሥት የራሱ የሆነ መመርያ በማውጣት ዘርፉን መታደግ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በመካከለኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወላጆች ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ቤት ለማስተማር ቢፈልጉም፣ አቅማቸው ስለማይችል ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ለማስገባት መገደዳቸውንና እሳቸውም ይህንን አማራጭ መውሰዳቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በ2016 የትምህርት ዘመን ሁለቱንም ልጆቻቸውን ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ለማስገባት ዕቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ዘካሪያስ፣ መንግሥት የግል ትምህርት ቤቶች ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ካልቻለ፣ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አጠናክሮ በሩን ክፍት አድርጎ መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል ውስጥ ሁለት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወላጅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ግልጽ የሆነ መመርያ ባለማስቀመጡ ትምህርት ቤቶች እንደ ልባቸው ጭማሪ እያደረጉ ነው፡፡

ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ እንደ ልባቸው ጭማሪ ማድረጋቸው ችግሩን እንዳባባሰው፣ የክፍያ ሁኔታ ሲወሰንም በአብዛኛው ወላጆች እንደማይገኙ ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ከዚህ በፊት በነበረው ክፍያ ላይ 32 በመቶ ጭማሪ እንዲደረግ ከወላጆች ጋር መስማማቱንና አብዛኛውም ወላጆች ስብሰባ ላይ ሳይገኙ መወሰኑን አክለዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ባለፉት ዓመታት በሦስት ወራት ውስጥ 25,000 ብር ይከፍሉ እንደነበር፣ ለ2016 የትምህርት ዘመን ደግሞ በአንድ ተርም 33,000 ብር መክፈል እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል፡፡  

በአብዛኛው የግል ትምህርት ቤቶች የሚደረገው የክፍያ ጭማሪ እጅግ የተጋነነና በመካከለኛ ገቢ ላይ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያላገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በግል ትምህርት ቤቶች ለ2016 የትምህርት ዘመን የተደረገው የተማሪዎች ክፍያ ጭማሪ ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛው ወላጅ ልጆቹን ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ሊያስገባ እንደሆነና እሳቸውም ይህንን እንደሚያደርጉ አክለው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የግል ትምህርት ቤቶች  ማኅበር ሊቀመንበር አቶ አበራ ጣሰው  ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እያንዳንዱ የግል ትምህርት ቤት ካለው ነባሪያዊ ሁኔታ  አንፃር ከወላጆች ጋር በመመካከር ያዋጣኛል የሚለውን ጭማሪ ማድረግ ይችላል፡፡

አብዛኛው ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ግብዓቶች መናር የተነሳ ፈተና ውስጥ መግባታቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ትምህርት ቤቶች በአሁኑ ወቅት እያስከፈሉ ባለው ክፍያ መቀጠል እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ ከወሰኑ፣ ትምህርት ቤት ከመዘጋቱ ከሦስት ወራት በፊት ለወላጆች የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸውና ይህም በመመርያ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

መመርያው የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ሲያደርጉ በትክክለኛው መንገድ ለወላጆች የማሳወቅ ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ቢያስቀምጥም፣ የክፍያ ሥርዓቱ ላይ ትምህርት ቤቶች መወሰን እንደሚችሉ ያሳያል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1,500 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን፣ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በግል ትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚማሩም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ሥልጠና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ እንደገለጹት፣ በከተማዋ ከሚገኙት 1,558 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1,253 የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ 1,112,745 ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳኛው፣ እነዚህንም ተማሪዎች ለማስተማር 556 የመንግሥት 1,558 የግል ትምህርት ቤቶች ፈቃድ አግኝተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት እነዚህ የግል ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ ከወላጆች ጋር በመስማማት ወርኃዊ ክፍያ ጭማሪ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አክለዋል፡፡

ለ2016 የትምህርት ዘመን 1,253 ተቋማት ጭማሪ ማድረግ እንደሚፈልጉ ከሦስት ወራት በፊት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ 301 የሚሆኑ ተቋማት ደግሞ ምንም ዓይነት ጥያቄ አላቀረቡም ብለዋል፡፡

ይህንንም አስመልክቶ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጭማሪ ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ ተቋማት ጋር ተሰብስቦ ማብራሪያ በመስጠት መግባባት ላይ መድረሱን አስታውሰዋል፡፡

ጭማሪ ለማድረግ የሚፈልጉ ትምህርት ቤቶች ኢኮኖሚያዊ ምክንያታቸውን በሚገባ በመዘርዝር፣ ለወላጆች እንዲያቀርቡና ከወላጆች ጋር የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም በ2016 የትምህርት ዘመን ላይ ማንኛውም የግል ትምህርት ቤት ከወርኃዊ ክፍያ ውጪ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉና ጭማሪም ሲያደርጉ የተገኙ ተቋማት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

የክፍያ ጭማሪውን በተመለከተ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች ከወላጆች ጋር የሚያደርጉትን ስምምነት ለመከታተል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የራሱን ሠራተኞች በማሰማራት ስብሰባውን እንዲታዘቡ ማድረጉን አክለዋል፡፡

በአብዛኛው ተቋማት ወላጆች ለስብሰባ ባለመገኘታቸው የተነሳ ስብሰባ ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ተይዞ በድጋሚ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ስብሰባውንም አድርገው የተስማሙና ያልተስማሙ ተቋማት እንዳሉ የገለጹት አቶ ዳኛው፣ የትኛውም ትምህርት ቤት ከወላጆች ጋር በቂ ስምምነት ሳይደርሱ ለ2016 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

በ2016 የትምህርት ዘመን ወርኃዊ ክፍያ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1,031 ተቋማት መግባባት ላይ መድረሳቸውን፣ 226 ተቋማት ደግሞ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከትምህርት ቤቶች ጋር መግባባት ላይ ያልደረሱ 226 ተቋማት ከስምምነት እንዲደርሱ ባለሥልጣኑ ውይይት የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል፡፡

በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲያስተምሩ የነበሩ ወላጆች በቀጣይ ጊዜያት ወርኃዊ ክፍያ መክፈል አቅቷቸው ችግር ውስጥ የሚገቡ ከሆነ ልጆቻቸው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተቀባይነት እንደሚያገኙ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከወላጆች ጋር ተስማምተዋል ከተባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሃምሳ አንዱ 20 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ያቀዱ ሲሆን፣ ከ21 እስከ 40 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ከወላጆች ጋር መስማማታቸው የገለጹ ትምህርት ቤቶች ብዛት 394 ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ከ41 እስከ 60 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ፕሮፖዛል ያቀረቡ ትምህርት ቤቶች 427 ናቸው፡፡ ከ61 እስከ 80 በመቶ የክፍያ ጭማሪ ለማድረግ ያቀዱት ትምህርት ቤቶች 126 ሲሆኑ፣ ከ81 እስከ 99 በመቶ ጭማሪ ማድረግ ያቀዱ ትምህርት ቤቶች 24 መሆናቸው ተገልጿል፡፡

መቶ በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ከወላጆች ጋር መስማማታቸው የተነገረላቸው ትምህርት ቤቶች አምስት ብቻ ሲሆኑ፣ ሌሎች አምስት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከመቶ ፐርሰንት በላይ ጭማሪ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ይቅርብኝ!  

ዓይኔ አይይ ይቅርብኝ ማየቴ ካልረዳኝ፣ የመጥፎ ድርጊት ጦር ጨረሩ ከጐዳኝ፡፡ አላውራ...

ለድሀ በእውነት የሚፈርድ

በእውቀቱ ሥዩም አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ቦሌ መድኃኔዓለም እሚገርመኝ ሰፈር...

ተፈጥሯዊው መምህር

ችግር ተፈጥሮአዊ መመህር ነው፡፡ ችግር የታላቅ ህይወት በር ነው፡፡...

ቻርልስ ደሞ ያበዛዋል

የመንደር ወሬ የማያመልጣቸው ስኮትላንዳዊው አያ ላዘንበሪ የሰሙትን ወሬ ለቡና...