የሰው ልጆች የምንሰቃየው አዳም ባመጣው ኃጢአት ነው የሚሉ ወገኖች ይኖሩ ይሆናል፡፡ አዳም የተከለከለው ዕፀ በለስ በመብላቱ ወደ ምድር ተሰደድን ይሉ ይሆናል፡፡ ለኔ ግን አዳም ዕፀ በለስ መብላቱ ለበጐ ነው፡፡ አዳም ዕፀ በለስ ባይበላና እስከአሁን በገነት የምንኖር ብንሆን ምን ዓይነት ሕይወት ነበር የምንኖረው? በጣም አሰልቺ ሕይወት ነበር የሚሆነው፡፡ የሰው ልጅ ምንም ነገር ሣይሠራ መኖር ምን ያህል አሰልቺ እንደሆነ ከሕይወት ልምዳችን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ከሥራ ፈትነት የገላገለን ግን አዳም ነው፡፡ ምንም ዓይነት ሥራ በሌለበት ዓለም ምንም ዓይነት ጣፋጭ ሕይወት ሊኖር አይችልም፡፡ እርስ በእርሳችን እንኳን ምንም ነገር ማውራት ሐሳብ ለሐሳብ መጋራት አንችልም፡፡ ሥራ ከሌለ ምንም ዓይነት ሐሳብ አይኖርም፡፡ የሐሳብ ልዩነት ከሌለ ደግሞ የሐሳብ መጋራት የለም ማለት ነው፡፡
- አብርሃም ሐዱሽ ‹‹ነገር በምሳሌ …›› (2005)