Friday, June 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ከድጋፍ በተጨማሪ ተቃውሞንም ማስተናገድ ይልመድ!

አገር የመምራት ዕድል ያገኘ መንግሥት ዋነኛ ተልዕኮው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማስከበር፣ ሕግና ሥርዓት ማስፈን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ በዜጎች መካከል ልዩነት እንዳይፈጠር መሥራት፣ ለግጭት አነሳሽ የሚሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶችን ማስወገድ፣ ብልሹ አሠራሮችን ማክሰም፣ ጉልበተኞች ደካሞችን እንዳያጠቁ መከላከል፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ማድረግ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን፣ ኢፍትሐዊ ተግባራትን ማስወገድና የመሳሰሉት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ በምርጫ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ የፖለቲካ ፓርቲም ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ተግባራትን በብቃት መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በተለይ መንግሥት ከደጋፊዎቹ ከሚቀርቡለት ሙገሳዎችና ማሞካሸቶች ባልተናነሰ፣ የሚቃወሙትን ወገኖችም በአንክሮ የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለደጋፊዎቹ የሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድ ያለ ስስት ሲሰጥ፣ ቅሬታ ወይም ተቃውሞ ለሚያሰሙ ወገኖችም በዚያው ልክ መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች ሲቀርቡለትም በአግባቡ ምላሽ መስጠት ግዴታው ነው፡፡ ከድጋፍ በስተቀር የተቃውሞ ድምፅ አልሰማም ማለት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጫለሁ ከሚል መንግሥት አይጠበቅም፡፡

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጋራ ከሚጋሯቸው መልካም እሴቶቻቸው መካከል አንዱ ሕግ አክባሪነት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ለመንግሥት የሚሰጡት አክብሮትና ላቅ ያለ ሥፍራ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በየዘመናቱ የተፈራረቁ መንግሥታት ይህንን የመሰለ አኩሪ እሴት መንከባከብ አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝባችን በተፈጥሮ በበለፀገች አገር ውስጥ ያለ ኃጢያቱ በድህነት ይቀጣል፣ ፍትሕ ተነፍጎ ሲያለቅስ ይኖራል፣ ጥጋበኞችና ዕብሪተኞች በሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች ሕይወቱን ያጣል፣ ንብረቱ ይውድምበታል፣ ጥቂቶች ተደራጅተው ሲበለፅጉ በረሃብ ይማቅቃል፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ዕድሉን ሲረግም ኖሮ ያልፋል፡፡ ለደረሰበት በደል አቤቱታ ሲያቀርብ ሰሚ አጥቶ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰማ ይደበደባል፣ ይታሰራል፣ ይሳደዳል፣ ወይም ይገደላል፡፡ ሰላማዊው መንገድ ጨርሶ ተዘግቷል የሚሉ ወገኖች ደግሞ የትጥቅ ትግል ይጀምሩና አገር ትታመሳለች፡፡ ይህንን የተለመደ አሳዛኝ አዙሪት ማስቆም የሚቻለው በእልህና በግትርነት ሳይሆን፣ ለሕጋዊና ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር በሩን ወለል አድርጎ በመክፈት ነው፡፡ ያኔ ድጋፍና ተቃውሞ ጎን ለጎን መሄድ ይችላሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የአምስት ዓመታት ጉዞ፣ እጅግ በጣም ከባድና ፈታኝ የሆኑ ክስተቶች የታዩበት ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሕግ መስኮች የተጀመሩ የለውጥ ዕርምጃዎች አይዘነጉም፡፡ ኢትዮጵያውያንን በአንድ የጋራ ብሔራዊ አጀንዳ ዙሪያ ሊያሠልፉ የሚችሉ በርካታ ክንውኖችም ነበሩ፡፡ እነዚህ የጋራ አገራዊ ጉዳዮች በመጡበት ግለት ቢቀጥሉ ደግሞ፣ ላቅ ያሉ ተግባራት ይከናወኑ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጸሙ ጅምላ ጥቃቶችና ግጭቶች በተጨማሪ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ይዘዋቸው የመጡ ተቃርኖዎች የጋራ ራዕይና ዓላማ እንዳይኖር ጥላቸውን አጥልተዋል፡፡ መንግሥት እንደ ወቅቱ ሁኔታ ወዶም ሆነ ተገዶ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ምክንያት፣ የሚከፉ ወገኖች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ዜጎች በመንግሥት አሠራር ቅሬታ ሲሰማቸው የውሳኔውን አመክንዮ በተረጋጋ መንፈስ ከማስረዳት ይልቅ፣ እነሱንም ሆነ ቅሬታቸውን ማጥላላትና ያልተገባ ስም መለጠፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ለመንግሥት ቁመናም አይመጥንም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች በመንግሥት ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ የድሮ ብልህ ነገሥታት ወይም መሪዎች ሕዝቡ ውስጥ የሚሰሙ ቅሬታዎችን፣ በእረኞች ወይም በአዝማሪዎች አማካይነት ለመረዳት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ዕድሜ ለመደበኛው ሚዲያና ለማኅበራዊ ትስስር ገጾች ብዙ ነገሮች በቀላሉ ይሰማሉ፡፡ አርሶ አደሮች፣ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ መምህራን፣ ሐኪሞች፣ ተማሪዎች፣ የመንግሥትና የግል ተቀጣሪዎች፣ ወዘተ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመንግሥት የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች አሏቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራትና የመሳሰሉት ብዙ ጥያቄዎች ይኖሯቸዋል፡፡ በመንግሥት አሠራርና ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች ድምፃቸውን ማሰማት ይፈልጋሉ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ያልተመቻቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲሁ፡፡ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት የሚታሰሩ ዜጎች ቤተሰቦች ወይም ሌሎች ወገኖች የመንግሥትን ዕርምጃ ሊተቹ ወይም ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በሙሉ ሕጋዊና ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ መብት እንዳላቸው መታወቅ አለበት፡፡ መብቶቻቸውም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነዶችም ሆነ፣ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት የተረጋገጡ ናቸው፡፡

መንግሥት የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር ኃላፊነት ሲኖርበት፣ ዜጎችም መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን በእኩልነት ለመወጣት መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት ሥራውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ እንዲወጣ ማድረግ የሚቻለው፣ ዜጎች ከመኖሪያቸው ጀምሮ እስከ ተሰማሩበት ሥራ ቦታ ድረስ ለሕግ መከበርና ለሥርዓት መኖር አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ነው፡፡ ዜጎች በእኩልነት የምታስተናግዳቸው አገር መኖር የምትችለው፣ ከአድሎአዊና ከኢፍትሐዊነት የፀዳ ሥርዓት እንዲታነፅ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ነው፡፡ በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት መሳሳቦችና መገፋፋቶች ምክንያት ጥቃት ከመፈጸም ወይም ከመጠቃቀም ከንቱ አስተሳሰብ መውጣት መቻል አለበት፡፡ ለመንግሥት የሚደረገው ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ከስሜት ይልቅ ምክንያታዊነት ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ ድጋፍና ተቃውሞን ከደም ወይም ከጥቅም ጋር በማገናኘት ለመንቀሳቀስ መሞከር፣ ከጥፋት በስተቀር የሚያስገኘው አንድም ትርፍ የለም፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመንግሥታት ውድቀት ተብለው የሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋነኞቹ የሚባሉት የመረጃ መዛባት፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ቢሮክራሲ፣ ሙስና፣ እንዲሁም ብቃት አልባነት ናቸው፡፡ መንግሥት ለውሳኔ የሚረዳ በቂ መረጃ ሳይኖረው ሲቀር ብዙ ነገሮች ይበላሻሉ፡፡ የመረጃ እጥረት ከሚፈጠርባቸው ምክንያቶች መካከል በቂ ሀብት አለመመደብ፣ የልምድ ዕጦትና የግልጽነት አለመኖር ስለሚሆኑ ለተቃውሞ በር ይከፍታሉ፡፡ መንግሥት የተለየ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሲፈጸምበት፣ ከሕዝብ ፍላጎት ተፃራሪ የሆኑ ውሳኔዎች እየተላለፉ ቅራኔው ይከራል፡፡ የመንግሥት ቢሮክራሲ ቀርፋፋና ኋላቀር ሲሆን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መተግበር ስለማይችል ለተቃውሞ ያነሳሳል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሙስና ሲስፋፋ የሕዝብ ሀብት ስለሚመዘበር፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን አይኖርም፡፡ ይህም ለተቃወሞ መነሳት ምክንያት ይሆናል፡፡ መንግሥት አገር የማስተዳደር ብቃት ሳይኖረው ሲቀር ደግሞ ሕግ ተጥሶ ሕገወጥነት ይንሰራፋል፣ የዜጎች መብቶች ይደፈጠጣሉ፣ በተዛቡ ውሳኔዎች ምክንያት ኢኮኖሚው ይጎዳል፣ የኑሮ ውድነት ይባባሳል፣ ሥራ አጥነት ይስፋፋል፣ ግጭት ተቀስቅሶ ንፁኃን ይገደላሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ሕይወታቸው ሲኦል ይሆንባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተቃርኖ እየበዛ የከፋ ጉዳት ይከተላል፡፡ መንግሥት ከድጋፍ በተጨማሪ ተቃውሞንም ማስተናገድ መልመድ ይጠቅመዋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...