- በካርቦን ልቀት ላይ ታክስ ሊጣል እንደታሰበ ተጠቆመ
በዓለም ላይ እየከፋ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያም ከማኅበራዊ ቀውስ ባሻገር በኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር፣ ከአጠቃላይ የአገራዊ ጥቅል ምርቷ (GDP) ከ3.6 በመቶ እስከ 6.1 በመቶ እያሳጣት መሆኑ ተገለጸ፡፡
በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ አገራዊ ጥቅል ምርት (Gross Domestic Product – GDP) በአሁኑ ጊዜ ከ111 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥም ከዚሁ አገሪቱ አሁን ካላት ጥቅል ምርት ላይ ነው በከፍተኛ መጠን እያሳጣት እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በወዳጅነት አደባባይ ይፋ በሆነው የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የካርቦን ልቀትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማት ስትራቴጂ ላይ እንደተገለጸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አማካይነት ተዘጋጅቶ ይፋ ስለሆነው ስትራቴጂ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትር ደኤታው አቶ ሳንዶካን ደበበ ሲሆኑ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከሦስት እስከ ስድስት በመቶ የሚሆነውን አገራዊ ጥቅል ምርት እንደሚታጣ አስረድተዋል፡፡
‹‹የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ አለው፤›› ያሉት አቶ ሳንዶካን፣ በማኅበራዊ ሕይወትም የአየር ንብረት ያስከተለውን ተፅዕኖ ለተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ከ30 እስከ 35 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተፈጠሩ የድርቅ ክስተቶችን በመቃኘት፣ ‹‹ዋነኛ ተብለው ሊወሰዱ የሚችሉ ከአሥር በላይ ድርቆች በኢትዮጵያ ተከስተዋል፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ክስተቶችም በዋናነት የአየር ንብረት ለውጥ ሰበብ ተደርገው እንደሚወሰዱ ነው ያስረዱት፡፡
በአሁኑ ጊዜ እየተከሰተ ያለው ድርቅም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕዝብን አስከፊ ችግር ውስጥ እንደከተተ፣ ‹‹አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች እንዳያመርቱና ያመረቱትንም በአጭር ጊዜ እንዲያጡት›› የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑን አቶ ሳንዶካን ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ሰባት ክልሎች በጎርፍ በመጠቃታቸው ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት እንደሆነ በመርሐ ግብሩ ላይ ተወስቶ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም. በፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ በተደረገው የአየር ንብረት ለውጥና የካርቦን ልቀት ቅነሳ ስምምነትን መሠረት ተዘጋጅቶ ይፋ የሆነው ስትራቴጂ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የስትራቴጂው ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2050 ዓ.ም. አጠቃላይ የካርቦን ልቀትን ወደ ‹‹ኔት-ዜሮ›› ለማድረስ ነው፡፡ ለዚህም ስትራቴጂ ተግባራዊነት ኢትዮጵያ 157 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ተገልጿል፡፡
ስትራቴጂው ይፋ በሆነበት መድረክ ላይም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና የፕላንና ልማት ማኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ጨምሮ ሰባት ተሳታፊዎች የተገኙበት የፓናል ውይይትም ተካሂዶ ነበር፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን በገንዘብ መደገፍና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ርዕሶች ላይም ተወያዮች አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም (ዶ/ር) ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ሰነዱን እንዳዘጋጁትና በጋራ ተግባራዊነቱ ላይም እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድም በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ የፋይናንስ ሥራዎችን ስትሠራ መቆየቷን፣ በቀጣይም የአየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችን እንደምታጠናክር ገልጸዋል፡፡
ከአዳዲስ ሥራዎች ውስጥም የገንዘብ ሚኒስቴር ወደፊት የካርቦን ልቀት ላይ ታክስ ለመጣል እያሰበ መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የጋዝ መጠን በሚለቁ የትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ታክስ ለመጣል መታቀዱን አክለዋል፡፡