በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሲሚንቶ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ መላክና መንገድን በሲሚንቶ ኮንክሪት መሥራት ይጀመራል ሲሉ የማዕድን ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማዕድን ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ገምግሟል፡፡
የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ሪፖርታቸውን ለኮሚቴው ሲያቀርቡ፣ በሲሚንቶ ምርት የአገሪቱ ዓመታዊ ፍላጎት 36 ሚሊዮን ቶን ቢሆንም፣ ፋብሪካዎች አሁን ለይ አያመረቱ ያሉት ከሰባትና ስምንት ሚሊዮን ቶን እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው እስከ 14 ሚሊዮን ቶን ድረስ ማምረት የሚችሉ ቢሆንም፣ በፀጥታ ችግር እንዲሁም በግብዓትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት በሚጠበቅባቸው ልክ ማምረት አልቻሉም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል በሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጭ በግንባታ ላይ ያለው ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በመጋቢት 2016 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት እንደሚገባ፣ በረንታ የተሰኘው የሲሚንቶ ፋብሪካ ሲኖማ ከተሰኘው የቻይናው ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር ለመሥራት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ እንዲሁም ሥራ አቁሞ የነበረው የመሰቦ ፋብሪካ፣ ለፋብሪካው የሚያስፈልጉ መገጣጠሚያዎችን እንዲያስገባ በብሔራዊ ባንክ ዕገዛ በመደረጉ ፋብሪካው ወደ ማምረት መግባቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የተጠቀሱት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ሲገቡ፣ ‹‹እንዲያውም አንድ ወቅት ጀምረን እንደነበረው ፋብሪካዎቹ ገዥ እንዳያጡ፣ መንገድ በሲሚንቶ ኮንክሪት የምንሠራበት ጊዜ ይመጣል ብለን ነው የምናስበው፣ ከዚያ ውጭ ደግሞ ወደ ውጭ ገበያ መላክ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ እነዚህ ፋብሪካዎች በድንጋይ ከሰል እጥረት ምክንያት ማምረት እንዳያቆሙ አሁንም የበለጠ ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በሚጠበቀው ልክ ከተሠራ በሁለት ዓመት ውስጥ አሁን የሚታየው የሲሚንቶ ችግር በሙሉ ይፈታል ብለዋል፡፡
መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሲሚንቶ ዋጋን ለማረጋጋት የተለያዩ ዓይነት ዕርምጃዎች ቢወስድም፣ ዋጋው በፊት ከነበረበት እያሻቀበ ምርቱንም በገበያ ላይ በተፈለገው መጠን ማግኘት ከባድ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
በዘጠኝ ወራት ውስጥ በማዕድን ዘርፍ ከ147 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵውያን በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ፣ እንዲሁም በኩባንያ ደረጃ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ሀብታሙ (ኢነጂነር) አስታውቀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ወደ ብሔራዊ ባንክ የተላከው ወርቅ 2.6 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው 35 በመቶ የሚሆነው ብቻ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡