Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት እንዳልቆመ የጋምቤላ ክልል ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት እንዳልቆመ የጋምቤላ ክልል ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ

ቀን:

ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች፣ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ወደ ክልሉ በመግባት የሚያደርሱት ጥቃት እንዳልቆመ፣ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያን ድንበር በመሻገር ጥቃት ያደርሳሉ የተባሉት ታጣቂዎቹ፣ ሰሞኑን ወደ ጋምቤላ ክልል ተሻግረው ከብቶችን እንደዘረፉ፣ የክልሉ መንግሥት ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኦቶው ኦኮት ተናግረዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በተለይ በጋምቤላ ክልልና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ በቅርበት በሚገኙ ወረዳዎች በሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት እንደሚያደርሱ፣ ሕፃናትን አፍነው እንደሚወስዱና ከብቶች እንደሚዘርፉ ክልሉ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር፡፡ ሰሞኑን ተፈጸመ በተባለው ጥቃት ምንም እንኳ እንደ በፊቱ ሕፃናት ታፍነው ባይወሰዱም፣ ከብቶች ግን ተዘርፈው እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡

ታጣቂዎቹ አደረሱት በተባለው ጥቃት ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸው ወይም አለመውሰዳቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹አሁን የተወሰደ አንድም ሕፃን የለም፡፡ በቅርብ ጊዜ ከብቶቹ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ተወስደው ነበር፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ወደ ክልሉ ዘልቀው በመግባት ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. 131 ከብቶችን እንደ ዘረፉ፣ ከተዘረፉት መካከል ስድስቱ በመንገድ ላይ እንደ ሞቱና 125 ከብቶች ደግሞ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ርብርብ ከታጣቂዎቹ ማስመለስ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ታጣቂዎቹ የኢትዮጵያን ድንበርን ተሻግረው በመግባት ጥቃት እንደሚያደርሱና ጥቃቱ መቆም እንዳልቻለም ተጠቁሟል፡፡

ታጣቂዎቹ በየጊዜው ወደ ክልሉ ድንበር ጥሰው በመግባት አፍነው የወሰዷቸውን ሕፃናት ማስመለስ ተችሎ እንደሆነና እንዳልሆነ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር የጠየቃቸው ምክትል ኃላፊው አቶ ኦቶው፣ በታጣቂዎች ተወስደዋል የተባሉ በርካታ ሕፃናትንና ከብቶችን መመለስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ሕፃናትን በየወቅቱ አፍነው ከመውሰድ ባሻገር በንፁኃን ላይ ግድያ እንደሚፈጽሙ ያስረዱት ነዋሪዎች፣ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድንበር ጥሰው በክልሉ ጎግ ወረዳ በአተቲ ቀበሌ ኡትዮ መንደር ሁለት ሰዎች እንደገደሉ፣ በአንድ ግለሰብ ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንዳደረሱ፣ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. ታጣቂዎቹ በጂካኦና ላሬ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት ዘጠኝ ሺሕ ነዋሪዎች ለመፈናቀል መገደዳቸውን አውስተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ሕፃናትን አፍነው የሚወስዱት በደቡብ ሱዳን ለሚገኙና ልጅ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ሸጠው የገቢ ምንጭ ለማግኘት መሆኑን አስረድተው፣ ሕፃናቱ በሕይወት እንዳሉ መስማታቸውንና መንግሥት ጉዳዩን በጥልቀት ተከታትሎ እንዲያስመልስላቸው ጠይቀዋል፡፡

ታጣቂዎች በየወቅቱ የሚሰነዝሩትን ጥቃት ለማስቆም ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ መደረሱንና በጉዳዩ ላይ ጥናቶች መደረጋቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል፡፡ ታጣቂዎቹ ወደ ክልሉ ዘልቀው በመግባት ሦስት ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸውን በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተፈጥሯዊው መምህር

ችግር ተፈጥሮአዊ መመህር ነው፡፡ ችግር የታላቅ ህይወት በር ነው፡፡...

ቻርልስ ደሞ ያበዛዋል

የመንደር ወሬ የማያመልጣቸው ስኮትላንዳዊው አያ ላዘንበሪ የሰሙትን ወሬ ለቡና...

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለቅድመ ማጣሪያ ውድድር ለ14 አትሌቶች ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና በ10 ሺሕ ሜትር...

ለአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በተመደበው ኢትዮጵያዊ ዳኛ ላይ ሥጋት እንዳለው የግብፅ ክለብ አስታወቀ

ክለቡ ዳኛው ‹‹የጡረታ መውጫው የመጨረሻ ጨዋታ›› መሆኑ አሳስቦኛል ብሏል የ2023...