Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ዜጎች ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ዜጎች ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በሱዳን ጦርነት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ የተለያዩ አገሮች ዜጎች፣ ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ፣ እንዲሁም የጤናና የትራንስፖርት ወጪን ጨምሮ፣ ሌሎች ድጋፎች ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እየተመቻቸላቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡

በሱዳን በተቀሰቀሰው ግጭት ከ18 ሺሕ በላይ ስደተኞች በመተማ በኩል ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ሲሆን፣ ድንበር አቋርጠው ከገቡ ስደተኞች መካከል ሁለት ሺሕ ያህሉ ከ67 የተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ዜጎች መሆናቸውን፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተሟላ ድጋፍና ክትትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበል ገልጸዋል፡፡

ፍሪደም ፈንድ ኢትዮጵያ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ጋር በመሆን ዓርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን በመከላከል ረገድ የሚዲያ አካላት ያላቸውን ሚና ማሳደግ›› በሚል ዓውደ ጥናት ላይ ነው የተገለጸው፡፡

በሱዳን ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው ሲኖሩ የነበሩና በተለያዩ ሥራዎቸ ተሰማርተው የነበሩ ዜጎች በቅርቡ ሱዳን ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት በመተማ በኩል አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ጠቁመው፣ መንግሥት ባደረገው ዓለም አቀፋዊ ስምምነት መሠረት በሱዳን ሲኖሩ የነበሩ የተለያዩ አገር ዜጎችን በመቀበል ተገቢውን እንክብካቤ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አሥራ ስድስት ሺሕ ኢትዮጵያውያን ከሱዳን በመተማ በኩል መግባታቸውን፣ እነዚህ ዜጎችም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ወደ አካባቢያቸው እንዲሄዱ ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ሲሉ አቶ ደረጄ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ አገሮች ተሰደው በመንግሥትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚኖሩ ስደተኞች ቁጥር አንድ ሚሊዮን እንደሚሆን አክለው አስረድተዋል፡፡

የፍሪደም ፈንድ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል መለሰ የፍትሕ ሚኒስቴር በየጊዜው የሚያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፣ በየዓመቱ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በመታለል ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ለስደት እንደሚዳረጉ ያስረዳሉ፡፡

የሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ቁጥር መጨመሩንም ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱ በኤጀንሲዎች ጭምር የሚፈጸም በመሆኑ፣ እንዲሁም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ለችግር ያጋለጣቸውን ሰው ጉዳት ያደርስብናል ብለው በማሰብ አሳልፈው እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡ ይህም ችግሩን በአግባቡ ለመቆጣጠርና ወንጀለኞችን በሕግ ለመጠየቅ አዳጋች ያደርገዋል ብለዋል፡፡  

መንግሥት ከሌሎች አገሮች ጋር ስምምነት በመፍጠር ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ አገር ያለ ምንም ክፍያ እየላከ ቢሆንም፣ አሠራሩን ወደ ጎን በማለት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በመታለል አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየጊዜው በሕገወጥ መንገድ እንደሚሄዱ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በስፋት ከሚከናወንባቸው ክልሎች አማራ ክልል ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ሲሆን፣ 41 በመቶ የሚሆኑት ሕገወጥ ተጓዦች ከዚሁ ክልል የወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል 33 በመቶ፣ እንዲሁም ከትግራይ ክልል 20 በመቶ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

በግንዛቤ እጥረትና ወቅታዊ መረጃዎች ባለማግኘታቸው በሕገወጥ ደላሎች ገንዘባቸውን፣ አካላቸውን፣ እንዲሁም ሕይወታቸውን እስከማጣት ለሚደርሱ ዜጎች መገኛኛ ብዙኃን ተገቢውን መረጃ በማድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ተብሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...