ከ15 ቀናት በፊት የፌዴራል መንግሥትና ‹‹ኦነግ ሸኔ›› በመባል በመንግሥት የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) የሚባለው ኃይል፣ በታንዛኒያ ዛንዚባር የሰላም ድርድር መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ አንዳንዶች ‹ከራስ ጋር ለመነጋገር ዛንዚባር ድረስ መሄድ ያስፈልጋል ወይ?› በሚል ሽርደዳ ድርድሩን በቀቢፀ ተስፋ እንደሚያዩት ሲናገሩም ተሰምቷል፡፡ በርካቶች ግን ለረዥም ዓመታት ሰላም አጥታ ለቆየችው ኢትዮጵያ የሰላም ተስፋ እስከፈነጠቀ ድረስ፣ ከሕወሓት ጋር እንደተደረገው ሁሉ ከኦነሠ ጋርም ድርድር መካሄዱ በጎ ነው በማለት በአዎንታዊ መንገድ ነበር የድርድሩን መጀመር የተቀበሉት፡፡
ከእዚህ ኃይል ጋር ድርድር ለማድረግ መታቀዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር በፓርላማው የተናገሩት፡፡ ለዚህ ወዲያው ማረጋገጫ የሰጠው ኦነሠም ባወጣው መግለጫ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ ነበር፡፡ ድርድሩ ሦስተኛ ወገን ባለበትና በግልጽነት እስከተመራ ድረስ፣ ወደ ድርድር መድረኩ ለመምጣት ዝግጁ መሆኑን በጊዜው አስታውቆ ነበር፡፡
ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ደግሞ ሲጠበቅ የነበረው የፌዴራል መንግሥትና የኦነሠ ድርድር በታንዛኒያ ዛንዚባር መጀመሩ ተነገረ፡፡ ይሁን እንጂ ስለድርድሩ በኢጋድ አደራዳሪነት ከመጀመሩ በስተቀር የተለየ ዝርዝር መረጃ ሲሰጥ አለመሰማቱ በርካታ ታዛቢዎችን ያስገረመ ጉዳይ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ድርድሩ ከተጀመረ ከሁለት ቀናት በኋላ ከኦነሠ ከፍተኛ አማካሪ ከአቶ ጅሬኛ ጉደታ ጠይቄ አጣራሁት ብሎ እንደዘገበው ከሆነ ግን፣ ድርድሩ በፍሬ ነገር ደረጃ የሚደረግ ድርድር አለመሆኑን ነበር ይፋ ያደረገው፡፡
ድርድሩ ሦስተኛ ወገን ባለበትና በግልጽነት የሚደረግ መሆኑን የዘገበው ኦኤምኤን፣ ሁለቱ ተደራዳሪ ኃይሎች የድርድሩ መሠረታዊ ሒደት ላይ ከተግባቡ በኋላ ወደ መደበኛው ድርድሩ እንደሚገቡ ገልጾ ነበር፡፡
ኦኤምኤን ከአቶ ጅሬኛ ሰማሁት ብሎ በድርድሩ መጀመሪያ ላይ እንደዘገበው ከሆነ፣ የታንዛኒያው ግንኙነት ቅድመ ድርድር እንጂ መደበኛ (ዋናው) የድርድር ምዕራፍ አልነበረም፡፡
በጊዜው መንግሥትና ኦነሠ ወደ ድርድር ሊገቡ ነው ከተባለ ጊዜ ጀምሮ በቀጥታ መደበኛው ድርድር ስለመጀመሩ በሰፊው ሲዘገብ ቢቆይም፣ በሒደት ግን የታንዛኒያው መድረክ የድርድር ሒደት ማመቻቻ (ቅድመ ድርድር) ብቻ ሆኖ ነበር የተገኘው፡፡
ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹የድርድሩን› መጠናቀቅ አስመልክቶ በተሰጠ መግለጫ ከሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች ተመሳሳይ አስተያየቶች ነበር የተሰጡት፡፡ የመጀመሪያው ዙር ውይይት አዎንታዊ በሆነ መንገድ ተጠናቋል ያሉት ተደራዳሪዎቹ፣ ‹በተወሰኑ ጉዳዮች ብንስማማም በተወሰኑት ግን ሳንስማማ ተለያይተናል› የሚል ነጥብ አንስተዋል፡፡ ተደራዳሪዎቹ ከዚህ በተጨማሪም በቀሪ ጉዳዮች ለመነጋገር ቀጣይ ዙር ድርድር እንደሚያስፈልግ ከመግባባት ደርሰናልም ብለው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ድርድሩ ተጀመረ እንደተባለበት ወቅት ሁሉ በድርድሩ መገባደጃም ወቅት የተሰጡ መረጃዎች በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሱ እንደሆኑ ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ ተስማምተንባቸዋል ያሏቸው ነጥቦች ምንድናቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡ ቀጣይ ዙር ድርድሮች ለማድረግ ተስማምተናል ቢባልም፣ እነዚህ ይደረጋሉ የተባሉ ድርድሮች መቼና የት እንደሚደረጉ በግልጽ አልተነገረም፡፡ በሌላ በኩል ድርድሮቹ በምን መንገድ እንደሚቀጥሉ ማለትም የድርድሮቹ ቅደም ተከተልና አጀንዳ ምን እንደሆነ ግልጽ ማብራሪያም አልተቀመጠም፡፡
ድርድሩ ግልጽነት የጎደለውና ሒደቱም ያልተብራራ ነው ከሚለው ጎን ለጎን ደግሞ በድርድሩ አንዳችም በጎ ውጤት ሊገኝ አይችልም የሚለው ቀቢፀ ተስፋ በተደጋጋሚ በመነሳት ላይ ነው፡፡ የመንግሥትንና የኦነሠን በመካከላቸው ሊኖር የሚችል ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት የሚያነሱ አንዳንድ ወገኖች ሁለቱ ኃይሎች በምን መንገድ ልዩነቶቻቸውን አስታርቀው ሊግባቡና ሊቀራረቡ ይችላሉ የሚለውን ጉዳይ እየጠየቁ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድመ ድርድር ሲባል የከረመውን የመጀመሪያ ዙር ድርድር መጠቃለል አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ መርህን ተከትሎ ግጭቱን ለመፍታት የፀና አቋም እንዳለው ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ መንግሥት እከተለዋለሁ የሚለው ሕገ መንግሥታዊ መርህ ግን በኦነሠ በኩል ተቀባይነት ይኖረዋል ወይ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡
የኦነሠ ይፋዊ ድረ ገጽ ላይ ፓርቲው የምታገልለት መሠረታዊ ዓላማ ብሎ እንዳስቀመጠው ‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን ጉዳይ ቀዳሚው መሆኑን አመልክቷል፡፡ ፓርቲው የኦሮሞን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መሠረታዊ መብት ለማስመለስ ለዘመናት ሲታገል መኖሩን የሚናገር ሲሆን፣ ይህንን መብት ማረጋገጥ ‹‹ለኦሮሞ ሕዝብ ፍትሕ፣ ክብርና ነፃነት መረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፤›› በማለትም ገልጾታል፡፡
በመንግሥትና በኦነሠ መካከል የተጀመረው ድርድር ይቀጥል ቢባል በምን መርህ ላይ ተመሥርቶ ነው ሊቀጥል የሚችለው የሚለው ጥያቄ ያሳሰባቸው ወገኖች፣ ሁለቱ ተደራዳሪ ኃይሎች በመሠረታዊ ጥያቄዎቻቸው ላይግባቡ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ኦነሠ እንደሚለው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (የመገንጠል) ጥያቄን ገፍቶ ወደ መድረኩ ቢያመጣ፣ ድርድሩ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ሊቀጥል ይገባል የሚለው መንግሥት በምን መንገድ ነው ተቀብሎ የሚያስተናግደው የሚለው ላያግባባቸው ይችላል የሚል ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡
ድርድሩን በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ፣ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶችም በድርድሩ እንዲካተቱ መጠየቁ ድርድሩን ሌላ አቅጣጫ እንዳያስይዘው እየተሠጋ ነው፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ ከመገዳደል ወደ መደራደር ፖለቲካ እንድትመጣ ከተፈለገ፣ ሁሉንም አካታች የሆነ የድርድር መድረክ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ድርድሩ እንዲሳካ ግፊት ማድረግና ስምምነት ከተፈረመ በኋላም ሥራ ላይ እንዲውል መቆጣጠር የሚችሉ ኃይሎች አሉ ብለው እንደማያምኑ መረራ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡ የውጭ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪዎች በድርድሩ ውስጥ ሊኖሩ እንደሚገባ የጠቀሱት የኦፌኮ መሪ፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ይህንኑ ሐሳብ ያጠናከሩት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰንም፣ በመንግሥትና በኦነሠ መካከል የተጀመረው ድርድር አካታች ሊሆን ይገባል የሚል አስተያየት መስጠታቸው ከሰሞኑ በሰፊው እየተዘገበ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም በመንግሥትና ትጥቅ ባነገበው ኦነሠ መካከል ተጀመረ የተባለው ድርድር በቀጣይ ዙሮች በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያካተተ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ከወዲሁ እያሰጠ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከብሔራዊ (ክልላዊ) የምክክር መድረክነት በምን ያንሳል ሲሉ ይጠቅሱታል፡፡
በድርድሩ ሊካተቱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ጉዳዮችም ቢሆን ከወዲሁ እያወዛገቡ ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ክልል የሚፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ መነሳት አለመነሳቱ ከሚጠበቁ ጉዳዮች አንዱ ስለመሆኑ የተለያዩ ግምቶች እየተሰጡ ይገኛል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የዛንዚባር ድርድር ግንኙነት በኦነሠ በኩል የሽግግር ጊዜ አስተዳደር የመመሥረት ጥያቄ መነሳቱ እየተነገረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በርካታ የኦሮሞ ድርጅቶችን ወደ ድርድሩ በቀጣይ ዙር መጋበዙ ሊነሳ የሚችለውንም ጥያቄ በዚያው ልክ እንደሚያበዛው ነው የሚገመተው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ያግዛል ተብሎ መጀመሩ ሲነገርለት የከረመው የመንግሥትና የኦነሠ የሰላም ድርድር ጉዳይ ቀጣይነቱና ይገኝበታል ተብሎ የሚጠበቀው ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ የሒደቱ ምንነትም አጓጊ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በኦነሠ በኩል ለሰላም ቁርጠኛ ነን የሚል መግለጫ ቢሰጥም ድርድሩ እንደተባለውም፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ላለው የፀጥታ ችግር ዘላቂ የሰላም መፍትሔ ይሆናል ወይ ለሚለው ጥያቄ ከወዲሁ ማረጋገጫ ማግኘት አይቻልም፡፡
ጉዳዩ የኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ክልል ያለፈና አገራዊ ችግር ነው የሚሉ ወገኖች በበኩላቸው፣ በኦሮሚያ በኦነሠና በመንግሥት መካከል የሚፈጠረው ግጭት ከክልሉ ተሻግሮ አገር አቀፍ ቀውስ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ለዚህ አገራዊ ችግር አገር አቀፍ ምላሽ ነው የሚያስፈልገው የሚል ሐሳብም እያቀረቡ ነው፡፡
ጉዳዩን የመንግሥትና የኦነሠ ብቻ አድርጎ እንዲሁም ድርድሩን በድብብቆሽ ከማድረግ ይልቅ የድርድሩን ምንነት፣ ዝርዝር ሒደትና የሚካተቱ አጀንዳዎችንም በግልጽ ይፋ ማድረጉ ለዘለቂ ሰላም እንደሚበጅ እነዚህ ወገኖች እየተናገሩ ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም በድርድር ስም የተፈጸሙ ስህተቶችን የሚያስታውሱት እነዚህ ወገኖች ኦነግ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ሲደረግ የነበረውን ሁኔታ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ በጊዜው በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራ ቡድን አስመራ አምርቶ ከኦነግ ጋር ድርድር ተቀምጦ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
ይህ የድርድር ሒደት ለሕዝብ በይፋ እንዲገለጽ በጊዜው ጉትጎታ የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄው ወደ ጎን ተብሎ በቸልታ መታለፉንም ያወሳሉ፡፡ በሒደት ደግሞ ወደ አገር ቤት የገባው የኦነግ ኃይል ተከፍሎ ወታደራዊ ኃይሉ ትጥቅ አልፋታም ማለቱ፣ ወዲያው ኦነግ ሸኔ የተባለ የታጠቀ ቡድን ተፈጠረ መባሉ ሁሉ ግልጽነት የጎደለው ድርድር ውጤት መሆኑን በርካቶች ይተቻሉ፡፡
ይህን መሰሉ ስህተት በአሁኑ የድርድር ሒደት እንዳያጋጥምና ተስፋ ለተጣለበት ዘላቂ ሰላም መፈጠር እንቅፋት እንዳይሆን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ እያሳሰቡ ነው፡፡ በፖለቲካ ግልጽነት መጓደል የተነሳ ለኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሰላም ይበጃል ተብሎ የተጀመረውና በብዙዎች አዎንታዊ አስተያየት እየገጠመው ያለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦነሠ ጅምር ድርድር እንዳይደናቀፍ ጥንቃቄ የተሞላው አያያዝ እንደሚያስፈልግ ነው ከወዲሁ እየተጠቆመ ያለው፡፡