በገለታ ገብረ ወልድ
በቅርቡ በጉምሩክ ኮሚሽን የተዘጋጀ የቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ለመመልከት ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ዶክመንተሪው የጉምሩክ ኮሚሽን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በቅልጥፍና፣ በደንበኞች እርካታና በገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች ካለፉት ዓመታት ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን ያትታል፡፡ ለዚህ ተግባሩም ከዓለም አቀፍና ከአገር ውስጥ ዕውቅና ሰጪ ተቋማት ጭምር የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማግኘቱን ጭምር አሳይቷል፡፡ ይኼ መሆኑ መልካም ነውና እሰየው ያስብላል፡፡
ዶክመንተሪውን እውነተኛና ከፕሮፓጋንዳ የፀዳ ሊያስብለው የሚችለው ነገር በቀዳሚነት ተገልጋዮች ሐሳባቸውን በነፃነት የሰጡበት ቢሆን ነበር (ሁሉም ተናጋሪዎች፣ የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ማለትም የመምርያ ኃላፊዎች፣ አለፍ ካለም የቡድን መሪዎች እንደነበሩ ታዝቢያለሁ)፡፡ የሕጋዊ ነጋዴዎች፣ የኮንትሮባንድ ክሶችና መሰል የክትትል ሥራ ላይ የተሳተፉ አጋር አካላት ሐሳብም ቢጨመርበት ነበር፡፡ ያ ባለመሆኑ ዶክመንተሪውን የተሟላ ነው እንዳይባል ያደርገዋል፡፡
በግሌ በዘርፉ መሻሻሎች እንዳሉ ብገምትም አሁንም ኮንትሮባንድና ተያያዥ ወንጀሎች ሙሉ በሙሉ ቀርቶ በከፊልም አልተወገዱም ከሚሉ ወገኖች ተርታ ነኝ፡፡ ማሳያዎቹም አሁንም እንደ የቁም ከብት፣ ወርቅ፣ እህል፣ ልዩ ልዩ የፋብሪካ ምርቶች፣ ወዘተ. በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ የመሆናቸውን የወንጀል ዜናዎች እየሰማን መሆኑ ነው፡፡
የቤትና የቢሮ አነስተኛ ዕቃዎች፣ ትምባሆ፣ ልዩ ልዩ ዕፆችና ልባሽ ጨርቆችን ጨምሮ በርካታ… የመዋቢያና የምግብ ምርቶች፣ ሌላው ቀርቶ ሽጉጦችና ጥይቶችን ጨምሮ የተለያዩ በርካታ የጦር መሣሪያዎች የአገር ውስጥ ገበያውን መቀላቀላቸው ይታወቃል፡፡ ምናልባት አሻጥረኛ የዘርፉ ሰዎች ቦታ ተቀያይረው ይሆናል እንጂ የረባ ለውጥ የለም የሚሉ ብዙ መሆናቸውን መዘንጋትም አይገባም፡፡
አውሮፕላን ማረፊያውን ጨምሮ በተለያዩ የፍተሻ ማዕከላት በቴክኖሎጂ የታገዘ የልየታ ሥርዓት መበጀቱ፣ ከጊዜም ሆነ ወንጀሉን ከመታገል አንፃር መሻሻል ያመጣ ቢሆንም፣ አንዳንድ ተገልጋዮች በአገልግሎት ሰጪዎች ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ማመነጫጨቅና ማንገላታትን ጨምሮ (ከጂቡቲ የሚመጡ አንዳንድ የጭነት አሽከርካሪዎችን ለቀሶና ምሬት ማየት ብቻ ይበቃል) ቀናነት በሌለው መንገድ ሁሉንም ተጓዥና አጓጓዥ በጥርጣሬ የማየት ፍርኃት ያለባቸው አዳዲስ ፈታሾች ስለመብዛታቸውም ነው የሚነገረው፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችንም በሚዛን ማየት ካልተቻለ ደግሞ ተሸነጋግሎ መተላለፍ ይከተላል፡፡
በመሠረቱ በማንኛውም አገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ለዕድገትና ለልማት የሚበጅ አንዳችም ፋይዳና አስተዋጽኦ የሌለው ዘርፍ ቢኖር የኮንትሮባንድ ንግድ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ የማይገባበት ቦታና የማያጠቃልለው የሸቀጥ ዓይነት የለም፡፡ ሁሉም ነገር ኮንትሮባንድ ይሆናል፡፡ ኮንትሮባንድ የሚባለው ያለ ሕጋዊ የመግቢያና የመውጫ ሰነድ ታክስ ሳይከፈልበት ድንበር ጥሶና ኬላ በጣጥሶ ከአገር አገር የሚዘዋወር፣ የሚገባና የሚወጣ ሕገወጥ ሸቀጥ በሙሉ ነው፡፡
ኮንትሮባንድ የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተከሰተው እ.ኤ.አ. በ1529 ሲሆን፣ ከመካከለኛው ዘመን ፈረንሣይኛ ‹‹ኮንትሬባንዴ›› ከሚለው ቃል መንጭቶ ነው፡፡ ከላቲን ‹‹ኮንትራ›› (ከሕግ ተቃራኒ) ከሚለውና ሕገወጥነትን ከሚያመለክተው ቃል የመጣ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ከየትም ይምጣ ከየት በሕገወጥነቱ ላይ ከተስማማን የምንጩ የትነት ለተነሳንበት ጉዳይ ችግር አይፈጥርብንም፡፡
ዋናው ነገር ሕገወጥ ንግድ በማንኛውም ሁኔታ ጎጂ መሆኑ ላይ ነው፡፡ የአገርን ኢኮኖሚ ያናጋል፣ ማኅበራዊ ሕይወትን ያቃውሳል፣ ባህልን ያፈርሳል፣ የጤና ጉዳትን ያስከትላል፣ ለሱስና ለብልግና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገሮች ኮትሮባንድን/ሕገወጥ ንግድን ይቃወማሉ፡፡ ለማቆምና ለማስቆም በተናጠልና በጋራ ይሠራሉ፡፡ በእኛም አገር ጠንክሮ መሥራት የሚያስፈልገው ተግባሩ እንዲህ ቁልፍ በመሆኑ ነው፡፡
ኮንትሮባንድ ማለትም መንግሥት ከንግድ ዝውውሮች ለአገሪቱ ማስገኘት ያለበትን ጥቅም ሳያስገኝ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ዕቃዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በዋነኛነት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ሞባይሎችና ሜሞሪ ካርዶች፣ ልባሽና አዲስ አልባሳት፣ የሕፃናት ምግብና ወተት፣ ሽቶና የቅባት ዘሮች፣ መድኃኒቶች፣ ሱስ አስያዥ ዕፆች፣ ወሲብ ነክ ፊልሞችና ቁሶች፣ ክላሽ ሽጉጥ፣ ቦምብን ጨምሮ ድምፅ ያላቸውና የሌላቸው የጦር መሣሪያዎች በሕገወጥ መንገድ ይገባሉ፡፡
በኮንትሮባንድ ከአገር የሚወጡ ምርቶችም ዓይነት ብዙ ነው፡፡ በዋነኛነት ቡና፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ፣ የቁም ከብቶች (በግ፣ ፍየል፣ በሬ፣ ግመል…) ሌላው ቀርቶ እኛ ከውጭ የምናስመጣቸው እንደ ነዳጅ፣ ዘይት፣ ስኳርና ሌሎች ምርቶች እጥረት እያለብን በሕገወጥ መንገድ ለጥቂቶች ጥቅም ሲባል ከአገር ይወጣሉ፡፡ በዚህም የኑሮ ውድነት ይባባሳል፣ የመንግሥት የፋይናንስ አቅም ይዳከማል፡፡
ኮንትሮባንድ በአገሪቱ ያለውን ሥራ አጥነት ከሚያባብሱ ጉዳዮች ዋናው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሀብት በዕድሜ ዘመን ልፋት ያገኘውን ገንዘብ አምጥቶ ኢንቨስት አደረገ እንበል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ በተለይ የሞባይል ፋብሪካ ከፈተ ብለን እናስብ፡፡ ይህ ባለሀብት ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሞባይል አምርቶም ለገበያ አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ኮንትሮባንዲስቶች ደረጃቸው የወረደ ሞባይሎችን በሕገወጥ መንገድ አስገብተው ገበያውን ያጥለቀልቁታል፡፡
ኮንትሮባንዲስቶች የመንግሥትን ግብርና ቀረጥ የማይከፍሉ በመሆናቸው ዕቃቸውን በወረደ ዋጋ ይሸጣሉ፡፡ የገበያ ተወዳዳሪነትን መርህ ባልተከተለ ንግድ ሕጋዊውን ባለፋብሪካ ለኪሳራ ይዳርጉታል፡፡ ባለሀብቱ ትርፍ ካላገኘ ምርቱን ሊቀጥል አይችልም፡፡ በምርቱ ካልቀጠለ ደግሞ ሠራተኞችን ማሰናበት አለበት፡፡ ከየት አምጥቶ ይክፈላቸው? በዚህ የተነሳ የሥራ አጡ ቁጥር ያሻቅባል፡፡ ይህ ሁሉ የሕገወጥ ንግድ መዘዝ ነው፡፡ ታዲያ በአገራችን እንዲህ ያሉ ተፅዕኖዎች እየተፈጠሩ አይደሉም ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር የሚችል አለ እንዴ?
ኮንትሮባንድ በግል ባለሀብቱ ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ በአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ከፍተኛ ተግዳሮት አለ፡፡ ለምሳሌ ሕገወጥ ነጋዴዎች ለሚያስገቡትም ሆነ ለሚያስወጡት ዕቃ ታክስ አይከፍሉም፡፡ ታክስ ካልተከፈለ የአገሪቱ ገቢ ያሽቆለቁላል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት ለሕዝቡ ሊሠራቸው ያሰባቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለማስፈጸም የገንዘብ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ በታለመለት ጊዜ አይደርስም፡፡ እነዚህን የልማት ወጪዎች ለመሸፈን መንግሥት ከውስጥና ከውጭ ለመበደር ይገደዳል፡፡ ይህ ሁሉ ሕገወጦች ታክስ ባለመክፈላቸው የመጣ ጉዳት ነው፡፡
በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡ ምርቶችም ተመሳሳይ ወይም የባሰ ጉዳት የሚያስከትሉብን ናቸው፡፡ በቢሊዮን ዶላሮች የውጭ ምንዛሪ ልናገኝባቸው የምንችላቸው ምርቶች ለምሳሌ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የቁም ከብቶች፣ ጥሬ ወርቅ፣ ቆዳና ሌጦ የመሳሰሉት በኮንትሮባንድ የሚወጡ ከሆነ አገር ማግኘት ያለባትን ከፍተኛ ገቢ ታጣለች፡፡ በዚህ የተነሳ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ይጎዳል፡፡ ለዜጎች ሥራ የመፍጠር ጥረቷ ይጓተታል፡፡
በእርግጥ በርካታ የኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎችን ስትጠይቋቸው፣ ‹‹በሕገወጥ ንግድ ውስጥ የገባነው ሥራ አጥተን ነው…›› ይሏችኋል፡፡ ‹‹ምን ሠርተን እንብላም?›› ሲሉም አያፍሩም፡፡ ታክስ ሳይከፍሉ ከውጭ እያስገቡና ከአገር እያስወጡ የአገሪቱን ገቢ እያስቀሩ፣ ሥራው ከየት እንደሚገኝላቸው ብትጠይቋቸው ግን መልስ የላቸውም፡፡
የእነሱ ተግባር ሕጋዊ ግብር ከፋይ ነጋዴውን በኪሳራ ከገበያ እንዲወጣ በማድረግ የሥራ አጥነት ቁጥር በየጊዜው እንዲጨምር ማድረግ ሆኖ ሳለ፣ ባለሀብቶች የፈጠሩት የሥራ ዕድል በእነሱ ምክንያት እየተዘጋና ሠራተኛ የነበረው ዜጋ እየተፈናቀለ ሥራ አጥ ለመሆን ሲገደድ እያወቁ፣ ‹‹ምን ሠርተን እንብላ?›› ማለታቸው ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ይህ ሰበባቸው ተቀባይነት የለውም፡፡ መንግሥት በተለይም የሚመለከታቸው አካላት በትንሹ ሳይረኩ ለትግል መነሳት ያለባቸው ከዚህ ፈተና አንፃር ነው፡፡
የኮንትሮባንድ ነጋዴ ግብ በዋነኛነት ለመንግሥት መክፈል ያለበትን ታክስ ሳይከፍል በነፃ ለማሳለፍ፣ የገበያ ተወዳዳሪነትን መርህና የአገሪቱን ሕግ በመጣስ ትርፍ ማጋበስ ነው፡፡ የፍተሻ ኬላዎችን ጥሶ በማለፍ ዕቃውና ሰነዱ እንዳይመሳከር በማድረግ ከተጠያቂነት ማምለጥ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በምሥራቅ፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ኮንትሮባንድ የደራበት ምክንያት ምንድነው ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡
የፍተሻ ኬላዎች ተግባር የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎች በሕጉ መሠረት የተሟላ ሰነድ ያላቸው መሆኑንና የተጫኑትም በሕግ አግባብ እንደሆነ ማረጋገጥ ቢሆንም፣ በጥቅም ትስስር እየተደለሉ ነው አገር እየበደሉ ያሉት የሚሉ ወገኖች የማይደመጡትስ እስከ መቼ ነው? ፈታሾች በማንነት፣ በቋንቋ ወይም በጥቅም የቀረቧቸውን ቸል እያሉ የሚቀጥሉት እስከ መቼ ነው? ይህን ችግር ደጋግሞ መፈተሽና አሠራርን ደጋግሞ ማስተካከል ይበጃል እላለሁ፡፡
በኮንትሮባንዲስቶች ካባ ሥር ሆነው ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች በማስገባት ድርጊት የተሰማሩ በአገሪቱ ሰላም እንዳይኖር፣ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ጦር እንዲማዘዝ የሚፈልጉ ጥገኞች አይደሉም እንዴ ያስቸገሩት? ታዲያ ውጤቱን ከየት አምጥቶ ነው የዘርፉ ሰው ሲሸላለም የሚውለው? እዚህ ለአገራቸው የለፉ ሰዎች አይሸለሙ የሚል አቋም ፈፅሞ እንደሌለኝ ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡ የአገሪቱ የሰላም ገጽታ እንዲበላሽና ሰላም የሌለ በማስመሰል ኢንቨስተሮች እንዳይሰማሩ ሥጋት ለመፍጠር የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች አንዱ ተግባር እኮ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ነው፡፡
እርግጥነው የጉምሩክ ኮሚሽንና ሌሎች መንግሥታዊ አካላት ብቻ ችግሩን አይፈቱትም፡፡ ሕዝቡም ድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ አሁን በስፋት የሚታየው ግን ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ምክንያት የሆነው ዋናው ጉዳይ፣ ሸማቹ በኮንትሮባንድ የገቡ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚያሳየው ፍላጎት ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሸቀጦቹ በሕገወጥ መንገድ ታክስ ሳይከፈልባቸው የገቡ በመሆናቸው ዋጋቸው ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሕጋዊ ነጋዴውን አያበረታታም፡፡ ታክስ ከፋዩ ነጋዴ በሕገወጥ ነጋዴዎች የሚበለጥበትን ሁኔታም እያባባሰ ነው፡፡
በተደጋጋሚ እንደሚባለው ለወደፊቱም የታክስ ከፋዩን አምራችና ነጋዴ መብት ለማስከበር ጭምር፣ የኮንትሮባንድን እንቅስቃሴ መግታት ያስፈልጋል፡፡ ሕጋዊውን ግብር ከፋይ ብቻ እያሳደዱ ሕገወጡን ማደለብ ለማንም የሚበጅ አይደለም፡፡ ሥራው ደግሞ የመንግሥት ኃላፊነትንና የሕዝቡንም ብርቱ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
መንግሥት በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችና አካላት በኩል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የሚገቡትም ሆነ የሚወጡት በበርካታ የአገሪቱ የድንበር አካባቢዎች ነው፡፡ ኮንትሮባንድ በኬንያ፣ በጂቡቲ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳንና በኤርትራ በኩል ይገባል፡፡ ይህን ሰፊ የድንበር ክልል በፌዴራል ፖሊስና በጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ብቻ ማስከበር አይቻልም፡፡ ክልሎችም ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ኮንትሮባንድ የሚገባው ድንበር አሳብሮ በእንስሳትና በተለያዩ ዘዴዎች በመሆኑ ለቁጥጥር መክበዱ የታወቀ ነው፡፡ ኮንትሮባንዲስቶች የተለያዩ አማራጮችን መጠቀምም ይችላሉ፡፡ በኮንቴይነር ውስጥ ከሌሎች የተፈቀዱ ዕቃዎች ጋር ተደባልቀው የሚገቡ ሕገወጥ ሸቀጦችንና ዕቃዎችን ጭነው የሚያሳልፉ አሉ፡፡ ለነገሩ በአውሮፕላንም ሳይቀር ሥልጣንን በመጠቀም እንደሚገቡም ይነገራል፡፡
ዋናው ነገር ግን ኮንትሮባንዲስቶቹ ያመጡትን ሕገወጥ ዕቃ የሚረከቡና በመጋዘን የሚያኖሩላቸው፣ የሚያከፋፍሉላቸውና የሚሸጡላቸው ደንበኞች ሕዝቡ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ከንቃተ ህሊና አለመዳበርም ሆነ ከቸልተኝነት ተሳታፊው አለመበራከቱ እንጂ፣ ሕገወጦቹ የሚንቀሳቀሱት ሕዝቡ ውስጥ ተሸሽገው ስለሆነ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ጭምር ትግል ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ሕዝቡ ስለሕገወጥ ነጋዴዎች ጥቆማ እንዲያደርግ ያዝ ለቀቅ ሳይሆን፣ ወጥ የሆኑ የማበረታቻ ሥልቶችን ቀይሶ መተግበርም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡
እዚህ ላይ ኮንትሮባንድ ይህን ያህል ጉልበት ሲያወጣ ‹‹ሃይ›› የሚባልበት ሕግ የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ግልጽ ሆኖ የተቀመጠ ሕግ አለ፡፡ አዋጅ አለ፡፡ የበፊቱ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ይባላል፡፡ ከባድ አንቀጾችን የያዘ ነበር፡፡ በኋላም እጅግ በጣም ግልጽ የሆነውና በመመርያ ብዛት ለአፈጻጸም ችግር የነበረበትን አዋጅ ያሻሻለ ሌላ አዋጅ ወጣ፡፡ ከዓመታት በፊት (ኅዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም.) የወጣው የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2007 በመባል ይታወቃል፡፡
በዚህ አዋጅ መውጣት ሳቢያ የበፊቱ አዋጅ 622/2007 የተሻረ ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት ሲሠራበት የቆየ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ አዋጆቹን መሠረት አድርገን ስናይ ኮንትሮባንድ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ በኮንትሮባንድ የተገኘ ዕቃ (ንብረት) ይወረሳል፡፡ ኮንትሮባንዲስቱም መንግሥት ሊያገኝ ሲገባው ያጣውን የታክስና የቀረጥ መጠን ይከፍላል፡፡ የረጅም ዓመታት የእስራት ፍርድም አለበት፡፡ የጉምሩክ ሕጉን ተላልፎ ሕገወጥ መሆኑን እያወቀ ወይም ሊያውቅ ሲገባው ቀረጥና ታክስ ሳይከፍል ያስገባ፣ ወይም ያስወጣ፣ የተቀበለ፣ ያጓጓዘ፣ በድብቅ ያከማቸ፣ ያስተላለፈ፣ የሸጠ፣ የገዛ፣ ወዘተ ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንጀሉ የተፈጸመው በተደራጁ ቡድኖችና በኃይል ከሆነ ደግሞ የእስራቱ መጠን በጣም የከበደ ይሆናል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 168 ሥር ባሉት ሦስት ንዑስ አንቀጾች እንደተጠቀሰው፣ ኮንትሮባንድ ከ50 እስከ 250 ሺሕ ብር እና/ወይም ከአምስት እስከ አሥር ዓመታት ያስቀጣል፡፡ የተቀበለ፣ ያከማቸ፣ ለሽያጭ ያቀረበና የገዛ ከ50 እስከ 100 ሺሕ ብር ቅጣትና እስከ አምስት ዓመታት የሚደርስ እስራት፣ በቡድን የተደራጀ ሕገወጥ ንግድ ከሆነ ደግሞ ከ10 እስከ 15 ዓመታት እስር ያስቀጣል፡፡ ይህ ሁሉ ዕውን መሆን የሚችለው ግን፣ የሕግ የበላይነትና ቅንጅታዊ አሠራር ተቀናጅተው ተግባራዊ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡
በአጠቃላይ ኮንትሮባንድ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል፣ አገሪቱ የምታደርገውን ፀረ ድህነት ትግል የሚያደናቅፍ፣ የኢኮኖሚ ዕድገቷን የሚገዳደር፣ በሕፃናትና በታማሚዎች ላይ የጤና ጠንቅ የሚፈጠር፣ ባህልን የሚያበላሽ፣ በሱስ አስያዥ ዕፆች የወጣቱን ራዕይና ተስፋ የሚያመክን፣ ሰላምና ደኅንነትን የሚያናጋ፣ ወዘተ. እንደሆነ መዘንጋት አይገባም፡፡ እናም መንግሥትም ሆነ ሕዝብ፣ እንዲሁም ሌላው ለራሱ ጥቅምና ለአገር ህልውና ሲል ሊታገለው የሚገባ ነው፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ የገቡበት አካላትም እጃቸውን ሊሰበስቡ ይገባል፡፡ ‹‹የጉምሩክ ቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው›› ማለት ግን ከፊት ሰፋፊ ሥራዎችና ያልተነኩ ተግባራት እንዳሉ ቸል ማለት እንዳስከትል ይታሰብበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡