የማር ምርት ለአካባቢያዊና ለማኅበረሰብ መስተጋብር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ምርቱ ለሰው ልጆች ከቆዳ ጀምሮ እስከ ውስጣዊ ጤና ጭምር ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከአዲስ አበባና አካባቢዋ ንፁህ ማር ማግኘት ዘበት ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሆለታ የእንስሳት ምርምር ማዕከል የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በአዲስ አበባ በሱቆችና አዟሪዎች የሚሸጠው ማር ‹‹በአብዛኛው ጤንነቱ ያልተጠበቀ›› ነው፡፡ ጥናቱ የተደረገው በስምንት ክፍላተ ከተሞች ሲሆን፣ በሱቆች በሱፐር ማርኬቶችና በአዟሪ እጅ ከሚገኙት እስከ 80 በመቶ የሚሆኑ የማር ምርቶች ጤንነታቸው ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ከአዟሪዎች ጀምሮ እስከ ሱፐር ማርኬት ያለው ማር ጤንነቱ ያልተጠበቀ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለከፋ የጤና ጉዳት የሚዳርግ መሆኑ በጥናቱ ተቀምጧል፡፡ በጥናቱ መሠረት ከማር ምርት ጋር ከሚቀላቀሉ ባዕድ ነገሮች መካከል የተፈጨ ጠርሙስ፣ ሙዝ፣ ስኳር፣ ከረሜላዎችና የቢራ ፋብሪካ ተረፈ ምርቶች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ማርን ከንብ አናቢዎች ጀምሮ ጥምረት ፈጥሮ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው ድርጅት፣ ጥራት የሌለውን የአገር ውስጥ ማር አቅርቦትን ለመቀልበስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስታወቀው ግሪን ፌስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የማር ምርትን ከአገር ውጭ ለሚገኙ ደንበኞች በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማመንጨትና የአገርን ገጽታን በከፊል በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ንፁህ ማር ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ቅድመ ሁኔታዎች መጀመሩን አስታውቋል፡፡ የግሪን ፌስ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ጆን ግርማ ናቸው፡፡ በአቅርቦቱና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- የማር ምርት ላይ ባዕድ ነገሮች የሚቀላቀሉት ከገበሬው እጅ ከወጣ በኋላ ነው፡፡ ‹‹ማርደን›› የተሰኘው ምርታችሁ ከባዕድ ነገሮች አለመቀላቀሉን ደንበኞች በምን እርግጠኛ መሆን ይችላሉ?
አቶ ጆን፡- ‹‹ማርደን›› ማርን ከንብ አናቢዎችና ወጣቶችን አደራጅተን ግንዛቤአቸውን አሳድገን ወደ ዘርፉ እንዲገቡ በማድረግ እናሰባስባለን፡፡ በልዩነት የምንሠራው ምርት ነው፡፡ በቀጥታ ከንብ አናቢዎች የሚሰበሰብ በመሆኑ ጥራቱ ላይ ምንም ችግር አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ንብ አናቢዎች ባዕድ ነገሮችን ከቀላቀሉ ንቦች ሊሸሹባቸው አልያም ደግሞ ሊሞቱባቸው እንደሚችሉ ስለሚያውቁ በጥራት ጉዳይ አይደራደሩም፡፡ ማኅበሩ ንብ አናቢዎችን ከማደራጀት በተጨማሪ የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት በማሟላት በተሻለ ዋጋ ስለምንገዛቸው በጥራት በኩል ችግር የለብንም፡፡
ሪፖርተር፡- የአገር ውስጥ ገበያ የአቅርቦት መጠናችሁ ምን ያህል ነው?
አቶ ጆን፡- ጥናት እንዳደረግነው ከሆነ የንፁህ ማር ፍላጎት ሰፊ ነው፡፡ አሁን ባለን አቅም ሱፐር ማርኬቶችና በበይነ መረብ ሽያጭን ወይም ገበያን መሠረት አድርገን በአቅማችን ልክ ለማቅረብ እየሠራን ነው፡፡ ‹‹ማርደን›› የተሰኘውን ማር በፋብሪካ የማቀነባበር አቅማችን በቀን አንድ ቶን ነው፡፡ በዚህም ማሽኑ የሚችለውን ያህል ማር እያቀነባበርን ለማቅረብ ዝግጁ ነን፡፡ ፍላጎቱ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ በተለያዩ ገጠራማ ቦታዎች የምናሠለጥናቸውን አነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶችን እናሳትፋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ማር የተለያየ ቀለምና ጣዕም እንዳለው ይታወቃል፡፡ ‹‹ማር ደን›› ለአገር ውሰጥ ገበያ የሚያቀርባቸው የማር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ጆን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የማር ዓይነቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጥቁር አዝሙድ፣ የቡና፣ የአበባና ንቦቹ እንደሚቀስሙት የዕፅዋት ዓይነቶች የተለያየ የማር ዓይነቶች አሉ፡፡ ጥቁር አዝሙድ በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ላይ የጥቁር አዝሙድ ቃና ያለው ማር በስፋት ይገኛል፡፡ የጫቃ፣ የአደይ አበባ ማርና ሌሎችም የማር ዓይነቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ ባለን አቅምና በምንችለው ልክ ለገበያ ለማቅረብ እየሠራን እንገኛለን፡፡ አሁን ላይ የጫካ ማር ኦርጋኒኩን እያቀረብን ነው፡፡ የአደይ አበባና የጥቁር አዝሙድ ማር ደግሞ ለመድኃኒትነት ስለሚፈለግ በሰፊው እያቀረብን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ለውጭ ገበያ የምታቀርቡት ማር ምን ያህል ነው?
አቶ ጆን፡- ለውጭ አገር ገበያ ለመላክ እንደ ዕቅድ የያዝነው በዓመት 100 ቶን ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ መቶ ቶን አልሞላልንም፡፡ ለምንድነው ያነሰው ብንል አገር ውሰጥ ያለው የማር ዋጋ ውድ በመሆኑ ነው፡፡ ኤክስፖርት ከምናደርግበት ዋጋ ይበልጥ የአገር ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ችግር ለማስታረቅ ስለሚያስቸግር ንብ አናቢው ጋር ሄደን የምንሠራው ለዚህ ነው፡፡ ጥራቱን ማሟላት ስለሚገባ የአውሮፓን ደረጃ ለማሟላትና የአገር ገጽታ የሚገነባ ማር ለማቅረብ ሲባል ንብ አናቢዎች ጋር መሥራት የግድ ብሎናል፡፡
ሪፖርተር፡- በውጭ ገበያ የኢትዮጵያ የማር ገበያ ፍላጎት ምን ያህል ነው?
አቶ ጆን፡- እውነት ለመናገር በውጭ ገበያ የኢትዮጵያ ማር ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ ያለው የአገር ውስጥ ማር የምንገዛበት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ኤግዚብሽን ገዥዎች አስተያየት ሲሰጡን መግዛት የሚፈልጉበት ዋጋ እኛ ከምንገዛበት ዋጋ ያነሰ ነው፡፡ ከአርጀንቲናና ከብራዚል ከእኛ ባነሰ ዋጋ መግዛት ስለሚችሉ፣ ብዙዎች የሚያነሱት ጥያቄ የዋጋ ተመን ላይ ነው፡፡ በዘርፉ በደንብ ቢሠራና አንድ ኪሎ ማር እስከ ሦስት ዶላር ቢሸጥ በዓመት ብዙ ቶን መሸጥ እንችላለን፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማር ለውጭ ገበያ ሲያቀርቡ፣ ከገበሬ በአንድ ዶላር አንደሚገዙ ይነግሩናል፡፡ እኛ ደግሞ ከገበሬ በኪሎ የምንገዛበት ዋጋ ውድ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ቢስተካከልና ምርትና ምርታማናት ቢጨምር፣ የአገር ውስጥ ገበያን በማስተካከል ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡ እኛ የምናቀርበው የጫካ ማር ‹‹ሸፍሌራያ›› ከሚባል ዕፅዋት የሚቀስም ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች የማይገኝ በመሆኑ በውጭ ገበያ እጅግ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ ይህ ዕፅዋት በኢትዮጵያ ብቻ የሚበቅል በመሆኑ ከዚህ የሚዘጋጀውን ማር አውሮፓውያኑ በእጅጉ ይፈልጉታል፡፡
ሪፖርተር፡- የማር ምርቱን የምታገኙት ከየትኛው የኢትዮጵያ አካባቢ ነው?
አቶ ጆን፡- እኛ የምንሠራው በብዛት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ ነው፡፡ ከኢሊባቦር፣ ከከፋ፣ ከሸካና ሌሎችም ቦታዎች ውስጥ እየሠራን ነው፡፡ አካባቢው ላይ ገበሬው ኬሚካል ስለማይረጭና ማዳበሪያ ስለማይጠቀሙ የምናቀርባቸው የማር ዓይነቶች የውጭ ገበያ ፍላጎትን ያሟሉ ናቸው፡፡ በዋናነት ትልቁ ችግር ያለው ዋጋ ላይ ነው፡፡ እኛንም እየተገዳደረን ያለው የአገር ውስጥ የዋጋ ተመን ነው፡፡ ሌላኛው ችግር የማር ገበያ ላይ የቁጥጥር መዋቅሩ የተቀናጀ አለመሆኑ ነው፡፡ የማር ምርት ሲደርስ ሁሉም ሰው የማር ነጋዴ ይሆናል፡፡ ግማሹ በሬም ሸጦ ማር ውድ ሲሆን ለመሸጥ በርከት አድርጎ ይገዛል፡፡ ይህም ትልቅ ችግር ሆኖብናል፡፡ አሁን ላይ እኛ የያዝነው ገበሬው ጋር ሄደን የማሠልጠኛ ጣቢያ በመክፈት ማር እያመረትን እንገኛለን፡፡ በደንብ ቢሰፋና ምርትና ምርታማነት ቢጨምር ዋጋው መውረድ ይችላል፡፡ እኛም በደንብ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ለአገር ውስጥ የምታቀርቡት ማር ጥራቱ የተጠበቀ መሆኑን አስመልክቶ በማኅበረሰቡ አመኔታ ለማግኘት ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ጆን፡- በጣም ፈታኝና ከባድ ይሆንብናል፡፡ ነገር ግን እንደ ድርጅት ባጠናነው ጥናት መሠረት ችግሮች እንዳሉ አረጋግጠናል፡፡ በከፍተኛ መጠን የንፁህ የማር ፍላጎት እንዳለ ዓይተናል፡፡ ይህንን ነገር ለማስተካከል ከባዕድ ነገር ጋር የሚቀላቅሉት በፖሊስ አሳድዶ ለመያዝ አዳጋች ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማር ተጠቃሚዎችን አመለካከት መቀየርና ከየት እንደመጣና ንፁህ ማርን እንዴት ማወቅ እንደሚቻል በሚለው ዙሪያ በስፋት መሥራት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በስፋት እየሠራንበትም እንገኛለን፡፡ ልክ እንደ እኛ ንፁህ ማር ለገበያ የሚያቀርቡትን ማኅበራት ዕገዛ አድርገንላቸው ገበያውን ለማሸነፍና ለመቆጣጠር ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይህን ዕቅድ ዕውን ለማድረግም የማኅበረሰቡን፣ የመንግሥትንና የባድርሻ አካላትን ዕገዛ እንሻለን፡፡