Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፋሺስት ጣሊያን ለፈጸመው ግፍ ካሳ እንዲከፈል የቀጠለው ንቅናቄና በባዕድ እጅ የሚገኙ ቅርሶች

ፋሺስት ጣሊያን ለፈጸመው ግፍ ካሳ እንዲከፈል የቀጠለው ንቅናቄና በባዕድ እጅ የሚገኙ ቅርሶች

ቀን:

አቻምየለህ ደበላ (ፕሮፌሰር) ተወልደው ያደጉት፣ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ሲሆን፣ በዚሁ ከተማ  ባለው  የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በሥዕል ትምህርት ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ናይጄሪያ አህመዱጊሎ ዩኒቨርሲቲ በግሪፊክስና ፔይንቲንግ የቢኤዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ወደ አሜሪካ አቅንተውም ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዚሁ ሙያ ሦስት ማስተርሳቸውን እንዲሁም ከሆዋዩ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ግራፊክስና አርት ትምህርት ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኖርዝ ካሮሊና ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የዩኤስኤ አርት ሂስትሪና አናቶሚ ዲዛይን ቲንኪንግ መምህርና ዋና ተመራማሪ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያን ዲያሎግ ፎረም የቦርድ አባል ሲሆኑ በተለይ የግሎባል አሊያንስ ከመሥራቾች አንዱ ናቸው፡፡ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት የሆኑት አቻምየለህ ደበላ (ፕሮፌሰር)፣ በሥነ ጥበብ ዲዛይን ትምህርት ቤት የስብሰባ አዳራሽ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹ቅርሶቻችን በባዕድ አገር›› በሚል ርዕስ ዙሪያ እና ከቅርብ ቀን የአውሮፓ የሥራ ጉብኝት ገጠመኞቻቸው ጋር የተያያዘ ምክረ ሐሳባቸውን ለታዳሚዎች አጋርተዋል፡፡

እንደ አቻምየለህ (ፕሮፌሰር) አባባል ቅርስ ከቅድመ ትውልዶች የተወረሰ ንብረት ሲሆን ባህልን፣ እሴቶችንና ወጎችን ተረቶችን፣ አፈታሪኮችንና ትዝታዎችን ያቀፈ ነው፡፡ መጠበቅ ያለበትና ከዚህም ሌላ አሁን ለትውልድ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለሆነም ቅርስ ሲባል የሚጨበጥ፣ የሚዳሰሱ ጭምር ነው፡፡ ቅርስ ታሪክን ይወክላል፡፡ ወጎችን ለመመርመርና ግንዛቤ ለማዳበር ይረዳል፡፡

ከዚህም ሌላ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ሕንፃዎች፣ ሐውልቶች በሙዚየም ውስጥ ያሉት ማህደሮች፣ በተጨማሪም ተፈጥሮአዊ የውኃ ሀብቶች፣ ደኖች፣ የዱር እንስሳት፣ ነፍሳት፣ ተክሎች፣ ዛፎች ከአዕዋፋት ከሚዳሰሱ ቅርሶች መካከል ተጠቃሾች እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የራሳቸው አገር ያልሆነውን ቅርስ በመዝረፍ ወይም በመስረቅ ተጠምደው ከነበሩት የአውሮፓ አገሮች አንዱ ፋሺስት ጣሊያን እንደነበር፣ ይህንንም ያደረገው በቅኝ ግዛቱ ሥር ባሉት አገሮች ላይ ሲሆን፣ በዚህም የተጎዱት ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ፋሺስት ጣሊያን ብዙ ሕይወት ያጠፋውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ከቅርሱ ዘረፋው ባሻገር በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ የመርዝ ጢስ ተጠቅሞ ወደ 30,000 ኢትዮጵያውያንን ለሕልፈተ ሕይወት ዳርጓቸዋል፡፡ ሊቢያ ውስጥ ደግሞ የ2000 ሕዝብ ሕይወት አጥፋቷል፡፡ ሊቢያ ለተገደለባት ሰዎች የጣሊያን መንግሥት አምስት ቢሊዮን ዶላር ካሳ ከፍሏል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የሊቢያ መንግሥትና ምሁሮቿ ባደረጉት ጥረት ነው፡፡ በተሰጠውም የካሳ ገንዘብ የወደፊቱ ትውልድ መማሪያ የሚሆኑ ኢንስቲትዩቶችን በማቋቋም ለትውልድ የሚረዳ ነገር አድርገውለታል፡፡

ኢትዮጵያ ግን ከሊቢያ በስንት እጥፍ እንደተገደለባት፣ ከአፍሪካ የመጀመርያው የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንደነበረችና ይህ ሁሉ ተረስቶ ብዙ በደሎች እንደደረሱባትና በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቿ እንደተጨፈጨፈባት፣ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ተገቢው ካሳ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት እንደሌለ፣ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን እንድትሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ወገኖች በግድ መዘከር/መታሰብ እንዳለባቸው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ኪዳኔ ዓለማየሁ የተባሉ አገር ወዳድ የተሰዉ ወገኖቻች እንዲካሱ ለብዙ ዘመን ለብቻቸው ሲታገሉ እንደቆዩ፣ ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ወደ 80 ሺሕ የሚጠጉ ፊርማዎች ያሉበት ሰነድ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰነዱም ታሪክን እንደሚናገር፣ ምን ተደርገን ነው ካሳ የምንፈልገው? ለሚለው መልስ የሚሰጥ ሲሆን ፊርማ ማኖር የሚፈልግ ካለ ግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያንስ ድረገጽ መግባት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የተዘረፉት ልዩ ልዩ ቅርሶች በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በሚገኙ ሙዚየሞች ተቀምጠዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ በአግባቡ አይያዙም፡፡ ከዚህ ሁሉ ይልቅ እዚያው ባሉበት ቢቀመጡ ሁለት ጥቅሞች ያገኛሉ፡፡ አንደኛው በእንክብካቤና በአግባቡ ይያዛሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እዚያው ባሉበት ኢትዮጵያን ሊወክሉ ይችላሉ የሚል አስተያየት መኖሩን፣ ይሁን እንጂ ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ እንደሚባለው ሁሌ አንተ ራስህ በሌለህበት እነሱ ስላንተ የሚገልጹ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው›› ብለዋል፡፡

ቅርሶችን የሚቀመጡበት ቦታ ከጠበበ ሌላ አዲስ ሙዚየም ማሠራት እንደሚቻል፣ ይህም ዕውን እየሆነ መሆኑንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በቅርቡ ያቋቋሙት ዘመናዊ ሳይንስ ሙዚየም አንዱ ማሳያ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አሁን ደግሞ እንደ ድሮ ደሃ እንዳልሆንን፣ ይህም ማለት ድህነታችን የማቴሪያል ማጣት ካልሆነ በስተቀር በዕውቀት በትልቁ ዳብረናል ብለው እንደሚያስቡ፣ ለወደፊቱ ሊጠቅሙ የሚችሉ የሚያማምሩ ሕንፃዎች እየተገነቡ ስለሆነ ማስቀመጫ የለም ብሎ ራስን መጣል እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ እ.ኤ.አ. በ1996 ትሬስተይ በምትባል የጣሊያን ከተማ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ትውፊትና ሃይማኖታዊ ሥነ ጥበብን አስመልክቶ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ 38 ምሁራን የተሳተፉበት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሪቻርድ ፓንክረስትና አህመድ (ፕሮፌሰር) ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ የተወሰኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትም የአክሱም መመለስን የሚጠይቅ ወደ 15,000 ሰዎችን ያስፈረሙበትን ሰነድ ይዘው በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ በኪነ ጥበብ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች መዘከር አለባቸው ከሚል እምነታቸው ተነስተውም የሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታን ታሪክ በስብሰባው ላይ አቅርበዋል፡፡

ከዚህም በኋላ ከሪቻርድ ፓንክረስትና ከሌሎችም ጋር ተመካክረው የአክሱም ሐውልት ወደ አገሩ መመለስ ያለበትን ሰነድ አዘጋጅተው በማግስቱ ለስብሰባው አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ስኮላር በሰነዱ ላይ ፊርማዎቻቸውን እንዳስቀመጡ፣ ይህንንም ሰነድ በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር እንደቀረበላቸውና ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ የአክሱም ሐውልት ወደ አገሩ እንደተመለሰ ነው ያመለከቱት፡፡ ይህም ሆኖ ግን እሳቸውና አብረዋቸው የነበሩት ብቻ ያሰገኙት ውጤት ሳይሆን ለብዙ ጊዜ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የለፉበት ሥራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከስብሰባው በኋላ ወደ ሮም ማቅናታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ወደዚያ ያቀኑትም ፋሲሽት ከፓርላማ ዘርፎ/ሰርቆ የወሰዳቸውንና በኢትዮጵያ ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ የተሠሩ ሥዕሎች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማየት፣ ቢያንስ በፎቶግራፍ አንስተው በግለሰብ ደረጃ እንኳን እንዲያዙ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተዘርፈው ወደ ሮም ተወስደው በአንድ ሙዚያም ከተከማቹት ሥዕሎች መካከል አብዛኞቹ ባህላዊ ሥዕሎች፣ የተወሰኑት የፈጠራ ሥራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሆኖም የሙዚየሙ ኃላፊ የተለያየ ምክንያት በመስጠት ሥዕሎችን ሲያሳዩአቸው፣ ሊተባባሯቸው ፈቃደኛ ሊሆኑላቸው እንደማይችሉ ገልጸውላቸዋል፡፡ በዚህም ቅር ብሏቸው ከወጡ በኋላ በሙዚየሙ ሌላ ክፍል ውስጥ ሁለት ትልቅ የጢያ ትክል ድንጎዮች ቁጭ ብለውና የዓድዋ ጦርነትን የሚያሳይ በኢትዮጵያዊ ሠዓሊ የተሠራ ሥዕል እንዳገኙ፣ ሥዕሉም የአገኘሁ እንግዳ ሥራ ነው የሚል ጥርጣሬ አድሮባቸው እንደነበር፣ እነሱም ቢሆኑ የሱ ለመሆናቸው እርግጠኛ እንዳልሆኑ ነገር ግን ከፓርላማ እንደተወሰደ የነገሯቸው መሆኑን ከአቻምየለህ (ፕሮፌሰር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ በካርቶን የታሸጉ ልዩ ልዩ ሥዕሎችን ማየታቸውንና እነሱም ሁለት ዓይነት መሆናቸውን ገልጸው፣ አንደኛው ባህላዊው ክርስቲያናዊ ሥነ ጥበብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ፋሺስቶች በኢትዮጵያውያን ሠዓሊዎች ተጠቅመው ስለፋሺዝም ፕሮፖጋንዳ ወይም በወቅቱ የነበረውን የፋሺዝምን ዕሳቤ ለማስረፅ የተጠቀሙባቸው ሥዕሎች መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...