የትዉልድ ቋጠሮ ዉል ቀመሩ፣
የቀጣይነት ማግ ድዉሩ፣
እናት አይደለች የክር እትብቱ፣
የትዉልድ ህላዌ ማህቶቱ።
በደሟ ሥር በእትብቷ፣
አንዳች ሳይቀር ስታካፍል ለትዉልዷ – አቤት አቤት ደግያነቷ፣
አይሰፈር አይለካ ሚስጥረ ኩን ዉበቷ።
አፏ ደርቆ አፍ አብሳ፣
እሷን እርቧት ልጇ እንዲጠግብ ምድር አስሳ፣
ለትዉልዷ ክብር ምድር ልሳ፣
ደስ ይላታል ልጇ ሲልቅ እሷ አንሳ።
እናትማ፣ የትዉልድ የእትብት ቋጠሮ፣
የትዉልድ የህላዌ ማሰሮ፣
የትዉልድ ዥረት ፍሰት አምባ- የርህራሄ ባላ፣
እያጠባች ታነባለች ልጄ ራበዉ ብላ።
የአገር እሴት እንዳወጀዉ ፍልስምና ፣
‹‹ወላድ በድባብ ትሂድ›› የትዉልድ ምንጭ ነችና።
እናትማ ያገር ማማ፣
ያገር ካስማ የትዉልደ ሸማ፣
ትወደስ ንሳ- ስሟ ሳይቀር ፍቅረ መዓዛማ፡፡
ሸንቁጥ አየለ
መታሰቢያነት፣ ለሁሉም እናቶች