Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ኢንቨስተሮች በቢሮክራሲና በሙስና ሳቢያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እየወጡ መሆናቸው ተነገረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ከአስፈጻሚው አካል በሚጠየቅ ያልተገባ የጉዳይ ማስፈጸሚያ ክፍያና በቢሮክራሲ ማነቆ በመማረራቸው፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ለቀው እየወጡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲገመግም ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን በገመገመበት ወቅት እንደስታወቀው፣ ቋሚ ኮሚቴው በኦሮሚያ ክልል ዱከም አካባቢ በሚገኘው በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ በተደረገ የመስክ ምልከታ፣ ከፓርኩ አስተዳደር አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት፣ ኢንቨስተሮች የሚጠይቋቸውን ከትንሽ እስከ ትልቅ አገልግሎቶች በገንዘብ እየገዙ መሆኑን መናገራቸውን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም የባለቤትነት ስሜት ባለመኖሩ ፓርኮች ውስጥ እየገቡ ዘረፋ በሚያካሂዱ አካላት የተማረሩ ባለሀብቶች መኖራቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል፡፡

በሌብነት፣ በዘረፋና በቢሮክራሲ ማነቆ የተነሳ ከኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 51 ባለሀብቶች ለቀው መውጣታቸውን በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡

ከፓርኩ የለቀቁ ባለሀብቶች ከአገር በመውጣት ወደ ኡጋንዳና ሌሎች ጎረቤት አገሮች፣ እንዲሁም ወደ ሌሎች አገር ውስጥ የሚገኙ ኢዱስትሪ ፓርኮች እየፈለሱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በመስክ ምልከታ አረጋገጥን እንዳሉት፣ ኢንቨስትሮች በመሬት አስተዳደርና በከተማ አስተዳደሮች ያለ እጅ መንሻ ገንዘብ የመሬትና የብድር አገልግሎት ለማግኘት ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የእጅ መንሻ ገንዘብ ተሰጥቶም በአግባቡ እንደማይስተናገዱ መረጃው ደርሶናል ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ይበል እንጂ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኢስተርን ኢንዱስትሪ ለቀዋል ተብሎ ስለተነገረው ጉዳይ መረጃው እንደሌለው አስታውቋል፡፡

  የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፣ ‹‹እኛ እስከምናውቀው ድረስ የወጣ ድርጅት የለም፡፡ ነገር ግን ከአምስት የማይበልጡ ባለሀብቶች አገር ውስጥ ወደ ሌሎች ፓርኮች ቀይረዋል፤›› ብለዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ኢንቨስተሮች ከአገር ሲወጡ ኮሚሽኑ አውቆትና ፈቃዳቸውን መልሰው ስለሚወጡ፣ የተጠቀሰው ቁጥርና መረጃ በተባለው ልክ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ የተቋማቸውን ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ በዘጠኝ ወራት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ ታቅዶ 2.67 ቢሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 61 በመቶ መሳብ ተችሏል ብለዋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ከመጡት ኢንቨስትመንቶች በአመዛኙ የግብርና፣ የአምራች፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንና፣ የቱሪዝምና የጤና ዘርፎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡  

ወደ አገር ውስጥ ከገቡት ኢንቨስተሮች መካከል ቻይና፣ ህንድና ኬንያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ አክለዋል፡፡

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች በዘጠኝ ወራት 118 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ወደ ውጭ መላኩን የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ ለ138 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 55.436 ብቻ ማሳከት ተችሏል ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎች በምርት ተቀባይ ማጣት፣ አዳዲስ ፓርኮች ወደ ሥራ አለመግባትና በሥራ ላይ ያሉት ፓርኮችም ሠራተኛ መቀነስ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አፈጻጸሙ ማነስ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች