የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ሦስት የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) አባላትን ከምክር ቤት አባልነት ማባረሩን አስታወቀ፡፡
በክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፈጤ ሰርሞሎ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የቁጫ ፓርቲ የክልሉ ምክር ቤት አባል የነበሩትን ጌዲዮን ጌታቸው (ዶ/ር)፣ መቶ አለቃ ማሳሞ ማደልቾ እና ወ/ሪት ሊዲያ በለጠን በጋሞ ዞን ቁጫ ምርጫ ክልል በድጋሚ ምርጫ ተካሂዶ ውጤቱ እስኪታወቅ፣ ከምክር ቤት አባልነት መሰረዛቸውን ገልጸው፣ የምክር ቤት አባልነት መታወቂያቸውን ለምክር ቤቱ እንዲመልሱ አሳስበዋል፡፡
የተሰረዙት የቁጫ ፓርቲ የክልል ምክር ቤት አባላት ለመሰረዝ ያበቃቸው ምክንያት፣ በብልፅግና ፓርቲ አመልካችነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ክርክር ሲካሄድ እንደቆየ በመጥቀስ፣ በመጨረሻም ሦስቱ የፓርቲ የምክር ቤት አባላት ሕግን ባልተከተለ መንገድ ምክር ቤቱ ውስጥ መግባታቸው ተረጋግጦ መወሰኑ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቁጫ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፖሊሲ ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ሳይንቲስቱ ሳባ እንደተናገሩት፣ የፍርድ ቤት ሒደቱ ባልተጠናቀቀቤትና ፓርቲያቸው አሁንም የሰበር መቃወሚያ እያቀረበ ባለበት ሁኔታ ውሳኔው መወሰኑ፣ ከጉዳዩ ጀርባ የፖለቲካ እጅ ያለቤት መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሳይንቲስቱ አክለውም፣ ጉዳዩ ከጅምሩ ወደ ፍርድ ቤት የሄደው ሕግን ተከትሎ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ አንድ የምክር ቤት አባል በፍርድ ቤት ውሳኔ ይነሳል የሚል ሕግ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስለጉዳዩ አሁንም አበክረው እንደሚከራከሩ ተናግረዋል፡፡