የግብርና ሚኒስቴር የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ (Strategic Plan) አካል የሆነው፣ አሥር የምርት ዓይነቶችን በስፋት የማምረት ዕቅድ ውስጥ ከስንዴ በተጨማሪ፣ የቅባት እህሎችና ሩዝ የዕቅዱ አካልና ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑ አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ የአሥር ዓመታት ዕቅዱን ሲነድፍ ሦስቱን የምርት ዓይነቶች ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በማካተት አሥር የምርት ዓይነቶች በስፋት የማምረት ዕቅድ መንደፉን፣ በስንዴ የታየው ውጤታማነትም በቅባት እህሎችና በሩዝ ላይ እንዲደገም እንደሚሠራ ነው የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች የገለጹት፡፡
ኃላፊዎች ይህንን ያስታወቁት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በሚል መሪ ቃል በሚሊኒየም አዳራሽ እየተዘጋጀ ባለው ዓውደ ርዕይና የፓናል ውይይቶች አካል በሆነውና ማክሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡
‹‹የግብዓት ትስስር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች›› በሚል የተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኅብረት ሥራ ኮሚንሽና የተባበሩት መንግሥታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካዮች በመገኘት ሲሳተፉ፣ የግብርና ሚኒስትር ደኤታው መለስ መኮንን (ዶ/ር) ውይይቱን መርተዋል፡፡
ሚኒስትር ደኤታው አራት ዋና ዋና ዓላማዎችን ለማሳካት በማቀድ ምርቶቹን በስፋት ለማምረት እንደታቀደ ተናግረዋል፡፡ ምግብና ሥርዓተ ምግብን ማረጋገጥ፣ ወደ ውጭ የሚላኩትን በጥራትና ቁጥር ማሳደግ፣ የገቢ ምርቶችን ለአንዱስትሪዎች በማቅረብ መተካት፣ እንዲሁም የሥራ ዕድል መፍጠር ናቸው አራቱ ዋነኛ ዓላማዎች እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ፡፡
እነዚህን ዓላማዎች መሠረት አድርጎ አሥሩን ምርቶች በስፋት ማምረት ላይ የግብርና ሚኒስቴር እንደሚሠራ መለስ (ዶ/ር) ገልጸው፣ ተነሳሽነቱም ‹‹ግብርና ከማምረት በላይ ነው፤›› በሚል መሪ ቃል እየተመራ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
‹‹አንደኛውና ዋነኛው ትኩረት የሰጠነው በቅባት እህሎች ላይ ነው፡፡ አኩሪ አተር፣ ሰሊጥ፣ የሱፍ አበባና ለውዝ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው በቅባት እህሎች ላይ ሚኒስቴሩ ያቀደውን አብራርተዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶችና የአምራቾች ተወካዮች የግብዓት እጥረት እየፈተናቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት መለስ (ዶ/ር) በተለይ በዘይት ኢንዱስትሪ ላይ ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት ምርት የማስፋት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፓልምና የወይራ ዘይት ግብዓቶች በሰፊው ለማምረት ቀደም ብሎ የተጀመሩ ተነሳሽነቶችን አሻሽለንና አስፋፍተን መሄድ ሲገባ ቆመው ነው ያሉት፤›› ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሳቢነትም የፓልምና የወይራ ዘይት ላይ አሁን ሰፊ ሥራ ለማከናወን ዕቅድ አዘጋጅተው ሊገቡበት እንደሆነና ጅምር ሥራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡